Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር የሚያፈርሱ የጥፋት እጆች ይሰብሰቡ!

ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያሳስባል፡፡ ከታሪካዊ ስህተቶች መማር ባለመቻል ወይም ባለመፈለግ ቀውስ ውስጥ መዘፈቅ ልማድ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያን ከመገንባት ይልቅ ለማፍረስ የሚክለፈለፉ እጆች እየበዙ ነው፡፡ ‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም› እንደሚባለው፣ በስህተት ጎዳና ላይ መመላለስ የዘወትር ተግባር ሆኗል፡፡ ከሰከነና በዕውቀት ላይ ከተመሠረተ ምክንያታዊነት በመጣላት፣ በደመነፍስ የሚመራ ስሜታዊነት የአገርን ተስፋ እያጨለመ ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም የጋራ ጉዳይ አድርጎ መፍትሔ ከማመንጨት ይልቅ፣ ለችግሩ ሰበብና ባለቤት ፍለጋ በሚደረገው ግብግብ ብሔርና ሃይማኖት ውስጥ መወሸቅ ክፉኛ የተጠናወተ ልማድ እየሆነ ነው፡፡ አገርን ማዕከል አድርጎ የጋራ አማካይ መፈለግ እየተቻለ፣ ልዩነትን በማጦዝ ከሰብዓዊነት የወረደ ድርጊት ውስጥ መዘፈቅ ተለምዷል፡፡ ኢትዮጵያን የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት አገር ለማድረግ በጋራ መሥራት ሲቻል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨትና ደም ማቃባት የዘወትር ተግባር እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የራሱን አንፀባራቂ ታሪክ መሥራት የተሳነው ትውልድ፣ በቀደሙ ትውልዶች ተፈጽመዋል በሚባሉ ድርጊቶች ውዳሴዎችና ነቀፋዎች ውስጥ ተጠምዷል፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የማይመጥኑ ትርክቶች ኢትዮጵያዊያንን ማጋደል ነበረባቸው? ለዘመናት ክፉና ደጉን አብረው በማሳለፍ ይታወቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የልጅ ልጆች የጋራ እሴቶችን መናድ ነበረባቸው? መልሱ በፍፁም መሞከር አልነበረባቸውም መሆን ነበረበት፡፡ ምክንያቱም አገር ከማፍረስ ውጪ ፋዳይ ስለሌላቸው፡፡ አገር ሲፈርስ ዝም አይባልም፡፡

እስኪ የሩቁን ዘመን ትተን የቅርቡን እንነጋገርበት፡፡ ለሦስት ዓመታት መስዋዕትነት ተከፍሎበት የለውጡ ጎዳና ከተጀመረ በኋላ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ለምን በድንገት ተበታተኑ? ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ ሥልጣን ከጨበጡበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ የቆየው የአብሮነት የት ሄደ? እነዚያ ተስፋ  ሰጪ የለውጥ ጅማሬዎች ለምን መከኑ? ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተጀመሩ ውጥኖች ተረስተው መከፋፈል ለምን አስፈለገ? መልሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ከሚሠሩ እጆች ይልቅ ማፍረስ የሚቀናቸው እየበዙ ስለሆነ ነው፡፡ በርካታ አመርቂ ተግባራት በተከናወኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በየቦታው ጥቃቶች እየተፈጸሙ ኢትዮጵያዊያን ተገደሉ፣ ተፈናቀሉ፣ ሀብትና ንብረታቸውን ተዘረፉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊነት ተዳረጉ፡፡ ሕግ ማስከበር የሚገባው መንግሥት እጁን አጥጣፎ ታየ፡፡ ጉልበተኞች ጠያቂ በማጣታቸው ሥርዓተ አልበኝነት ሰፈነ፡፡ መንግሥት ሕግ አስከብር ሲባል ወገቤን አለ፡፡ በተሰጠው ሕጋዊ ኃላፊነት ተጠቅሞ ሕገወጥነትን አደብ ማስገዛት ሲያቅተው ብዙዎች አኮረፉ፡፡ ከኩርፊያ አልፈው የአፀፋ ጥቃት ውስጥ የገቡ አሉ፡፡ በዚህ መሀል ማን ተጎዳ መልሱ አገር ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ መሀል የግጭት ነጋዴዎች አትራፊ ሲሆኑና ሕዝብ ሲከፋፍሉ ለድጋፍ የወጣው አንድነት ተበተነ፡፡ ከቀውስ ወደ ቀውስ የሚደረገው ሽግግር እየተጠናከረ አገር ሊያፈርስ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ሰሞኑን የታየው አደገኛ ምልክትም ይኸው ነው፡፡

በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ደግሞ ለአገር የማያስቡ ደንታ ቢሶችን መብዛት በግልጽ አሳይቷል፡፡ ‹እኔ ከሌለሁ አገር ትፈርሳለች› ከሚሉ ግብዞች ጀምሮ፣ የአገር ህልውና ምንም የማያሳስባቸው ራስ ወዳዶች በሚገባ ታይተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሹመት ከበፊት ጀምሮ በብቃት ላይ ሳይሆን በኮታ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ብቃትና አቅም የሌላቸው በየቦታው ተሹመው አገር መከራዋን ታያለች፡፡ ችግር ሲያጋጥም መቋቋም እያቃታቸው ብሔር ውስጥ የሚደበቁ ብቃት አልባ ሹማምንት፣ ይህ አልበቃ ብሏቸው ሃይማኖቶች ውስጥ ጭምር እየተነከሩ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሥር እየተርመጠመጡ፣ መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት አቅቷቸዋል፡፡ በመርህ ሳይሆን በገጠመኝ እየተመሩ አሸናፊ ከመሰላቸው ጋር ይሞዳሞዳሉ፡፡ የእነሱ ዋና ፍላጎት አድርባይነትና አስመሳይነት ስለሆነ፣ የአገር መጎዳትና የሕዝብ ለሥቃይ መዳረግ አያሳስባቸውም፡፡ በተሾሙባቸው መዋቅሮችም ሆነ በተጓዳኝ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች፣  ኃይል አለው ብለው ከሚያስቡት ጋር ማጨብጨብ ሥራቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቁ፣ ሲገደሉ፣ ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉና የድረሱልኝ ጥሪ ሲያሰሙ ሰሚ የማያገኙት እንዲህ ዓይነት ሹማምንት ስለበዙ ነው፡፡ አገር ለመፍረስ ቋፍ ላይ ያለችውም በዚህና በመሰል ምክንያቶች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህም በፍጥነት መልክ መያዝ አለበት፡፡

ሌላው የአገር ችግር ለወጣቶች ሥራ መፍጠር አለመቻል ነው፡፡ ለሥራ ፈጠራ ተብሎ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቢመደብም፣ በጥናት ላይ ባልተመሠረተ የዘፈቀደ አሠራር በመበተን መጫወቻ ተደርጓል፡፡ ለወጣቶች በዕውቀት ላይ የተመሠረተና በጥናት የታገዘ የሥራ ፈጠራ ያስፈልጋል፡፡ ለጊዜው ጩኸታቸውን ለማብረድ ወይም በአጉል ወገንተኝነት ገንዘብ እያባከኑ የበለጠ ችግር  መፍጠር መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ወጣቶች ተምረው ሥራ ሲያጡ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ተስፋ ሲቆርጡ ደግሞ ገንዘብ ለሚያቀርብላቸው ኃይል ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትልቅ ትኩረት ይስጥ ሲባል፣ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ደካማ አሠራሮች ይስፈኑ ማለት አይደለም፡፡ የሥራ ፈጠራው ከአድልኦና ከመድልኦ ነፃ ሆኖ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት አለበት፡፡ መንግሥት ገንዘብ በገፍ እያተመ ኢኮኖሚው ውስጥ ከሚረጭ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ያሳተፈ ሥራ ቢፈጥር አገር ትጠቀማለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሥራ ያጡ ወጣቶች የጥፋት ዓላማ መጠቀሚያ ሲሆኑ በማየት ከማዘን አልፎ፣ ለአገር ህልውና ጠንቅ መሆናቸውን ማሰብ ይበጃል፡፡ ወጣቶችን በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሥራ ፈጠራዎች ሲኖሩ፣ ለክፉ ዓላማ ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጉ ኃይሎች ምንጫቸው ይደርቃል፡፡ አለበለዚያ የአገር መፃኢ ዕድል አሳሳቢ ይሆናል፡፡ የማይሠሩ እጆች አገር እንደሚያፈርሱ መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህም ምልክቱ ታይቷል፡፡

የመንግሥት ዋነኛ ተቀዳሚ ኃላፊነት የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም መጠበቅ፣ እንዲሁም የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ በየትም አገር ያለ መንግሥት ሕጋዊ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር አለበት ሲባል፣ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ማለት ነው፡፡ ከሕግ በላይ እንሁን የሚሉ ሥርዓተ አልበኞችን ከሕግ በታች የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ሲሳነው ዜጎች የማስገደድ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መንግሥት እርስ በርሱ መናበብ አቅቶት ሕገወጦች የበላይነቱን ሲይዙ፣ በሕግ አምላክ የማለት መብት ያላቸው ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ ሕግ ይከበር ማለት መግደል ወይም በዘፈቀደ ማሰር ሳይሆን፣ ያጠፋው ማንም ይሁን ማን ሕግ ፊት ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አቅቶት ዜጎች ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲዘረፉና የአገር ሀብት ሲወድም ሕግ አውጪው ፓርላማ ጭምር የመጠየቅ ሕጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ በፍፁም መዘንጋት የለበትም፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎችም ሕግና ሥርዓት እንዲከበር መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ሕዝቡን እርስ በርሱ የሚያጋጩ፣ ባልታረሙ ቃላት የሚሳደቡ፣ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚፈጽሙ፣ ሃይማኖትና ብሔር ውስጥ እየተደበቁ አገር ለማፍረስ የሚሯሯጡና ከሕግ በላይ እንሁን የሚሉትን በሙሉ ሥርዓት ማስያዝ የግድ ይላል፡፡ ላጋጠሙ ችግሮች በሙሉ መፍትሔው በሕዝብ ውስጥ ያሉ የዘመናት የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች በመሆናቸው፣ አገር የሚያፈርሱ የጥፋት እጆች መሰብሰብ አለባቸው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...