Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በተግባር ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እየቀረበለት ነው

መንግሥት በተግባር ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እየቀረበለት ነው

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ከ350 በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ባጋጠሙ ጥቃቶችና ግጭቶች የ67 ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ሰሞኑን አንፃራዊ መረጋጋት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ቃል ከመግባት ባለፈ በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥያቄ እየቀረበለት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና አጥፊዎች በሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ሁሉ እንዲያገኙ ያለማወላወል እንሠራለን፤›› ካሉ በኋላ፣ በርካቶች የመንግሥትን ዕርምጃ እየጠበቁ ነው፡፡

መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ጥያቄ ካቀረቡለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ በተካሄደ ውይይት፣ ከተለያዩ የእምነት ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ሰላም በሚያደፈርሱ አካላት ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያሉት ሕግ ባለመከበሩ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የተለያዩ ሃይማኖቶችን በመወከል የተገኙ አባቶች ብሔርና ሃይማኖትን በመከለል በነዋሪዎች መካከል ለዓመታት የተገነባውን የመቻቻልና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚንዱ አካላት፣ በአስቸኳይ በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ሰላምና መረጋጋት እንዲኖርና በተለያዩ የእምነት ተከታዮች መካከልም በሰላም አብሮ መኖር እንዲቻል፣ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸው፣ መንግሥት ደግሞ ሕግ የሚጥሱትን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ይህንን ጥያቄያቸውንም መንግሥት በፍጥነት እንዲመልስላቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አርዲን በድሪ በበኩላቸው ሃይማኖትንና ብሔርን በመከለል ሃይማኖታዊ ግጭት ሲቀሰቅሱ የነበሩ አካላት እንዳሉ አስታውቀው፣ የሃይማኖት መሪዎች የእነሱ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማሳሰባቸውን፣ የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሐረሪ፣ በድሬዳዋና በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መኖሩ የታወቀ ሲሆን፣ ለበርካቶች ሕልፈትና ለንብረት ውድመት የዳረጉ ጥቃቶች ካሁን በኋላ እንዳይፈጸሙ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከደረሰው ጥፋት ተምሮ ሕግ ማስከበር ካልቻለ ሌላ ዙር ጥቃቶች ላለመፈጸማቸው ማረጋገጫ የለም ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲና በባሌ ዞንም አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለይ በዶዶላ፣ በባሌ ሮቤና በተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለው በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ በአካባቢዎቹ አንፃራዊ ሰላም ከተፈጠረ በኋላ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ለመንግሥት ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ዋስትና እንደሌላቸው የጥቃት ዒላማ የነበሩ ወገኖች አሳስበዋል፡፡

ሪፖርተር ከባሌ ሮቤ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ጊዜ አንፃራዊ መረጋጋት በመፈጠሩ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ቀበሌዎች ውይይት እያደረገ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው መንግሥት ሕግ ማስከበር እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በፍጥነት ተቋቁመው ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡

በሮቤ ከተማ ተዘግተው የነበሩ የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎችና ባንኮች ተከፍተው ሥራ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጥቃቶቹ ወቅት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ ዘረፋዎችንና የንብረት ውድመቶችን የሚያጣሩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ሥራ እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከአካባቢው ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክልል ተወካዮች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ውይይት፣ መንግሥት ሕግ ማስከበር እንዳለበት ጥያቄ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡ በተለይ ሐሰተኛ መረጃዎች በማሠራጨት ችግር እየተፈጠረ መሆኑ ተገልጾ፣ ለአገር ደኅንነት የሚቆረቆሩ ካሉ ሕግ ማስከበር ተቀዳሚ መሆን አለበት መባሉ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር እየጠየቁ ነው፡፡ ሕግ ካልተከበረ በሰላም ወጥቶ መግባት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ህልውናም ለአደጋ እንደሚዳረግ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በአብያተ ክርስቲያናትና በሌሎች ሥፍራዎች የተጠለሉ ወገኖች፣ መንግሥት በተጨባጭ ሕጋዊ ዕርምጃ ካልወሰደ ለሕይወታቸው እንደሚፈሩ እየተናገሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት ሕግ ያስከብራል ማለታቸውን በማስታወስ፣ በተግባር እንዲያሳዩዋቸውም ጠይቀዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በክልሉ ውስጥ አጋጥመው በነበሩ ጥቃቶችና ግጭቶች ሳቢያ 359 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ማንነት በዝርዝር አልተገለጸም፡፡ ነገር ግን በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሰሞኑን ግጭቶችና ጥቃቶች የነበሩባቸው ሥፍራዎች ሰላም ወደነበረበት መመለሱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...