Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጣባቂዎች አሳሰቡ

መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጣባቂዎች አሳሰቡ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት የአክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎችን ከማንሳት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ውዝግብ፣ በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች በንፁኃን ላይ በደረሰ ጥቃት ሕይወታቸው ካለፈው ወገኖች በተጨማሪ በሌሎች ላይ ሊደርስ የሚችል የሥጋት ምልክቶች ስላሉ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂዎች አሳሰቡ፡፡

ሰባት የሃይማኖት ተቋማት የመሠረቱት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂዎች ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቁት፣ በክልሉ በተፈጠረው ጥፋት ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷቸዋል፡፡ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ላይ የሚገኙ ወገኖች ፈጣን መረጋጋት እንዲገጥማቸው ተመኝተው፣ በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለውን አለመረጋጋትና በድጋሚ ጥፋት የመፈጸም አዝማሚያ ተወግዶ ሰላም እንዲመለስ፣ ጥፋትን ከሚያባብሱ ሐሳቦችና ድርጊቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

ታች ያለው ሕዝብ በሙሉ በሰላም፣ በአንድነት፣ በአብሮ መኖር ልጆቹ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱና አገር ሰላም እንድትሆን እንደሚፈልግ እየተናገረ መሆኑን ያስታውቁት የጉባዔው የበላይ ጠባቂና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ይኼንን የንፁኃን ጥያቄ ሁሉም ሊቀበለው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

- Advertisement -

መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት መጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት፣ ሕዝብ ማስተዳደር አጥፊን መቅጣትና አልሚን መሸለም ኃላፊነቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት በእኩልነት፣ በግልጽነት፣ በታማኝነትና በኃላፊነት ሊያስተዳደር ሥልጣን ላይ መቀመጡንም አክለዋል፡፡ ‹‹ችግር እንዳለ እንረዳለን፡፡ ምንም ቢሆን ግን ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ልባችን ስለተከፋፈለ እንጂ አንድ ከሆንን መድኃኒት አለው፡፡ በመጀመርያ ነገር የመንግሥት ኃላፊዎች መከፋፈል ነው ሕዝቡን እንዲህ እያዋጋ ያለው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች አንድ ሁኑ፡፡ ልባችሁ አንድ ይሁን፡፡ አዕምሯችሁን ሰብስቡ፡፡ አንድ ላይ ተሠለፉ፡፡ ለሕዝባችሁ፣ ለአገራችሁና ለወገናችሁ አስቡ፤›› በማለት፣ መንግሥትንና የመንግሥት ኃላፊዎችን አስገንዝበዋል፡፡   

የሃይማኖት አባቶች የእግዚአብሔር ባለአደራዎች በመሆናቸው አደራቸውን መናገር ግዴታ እንዳለባቸው የገለጹት ፓትርያርኩ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች ደግሞ ሕግን ጠብቀው በሕግ እንዲያስተዳድሩና በሰላም ሕዝባቸውን መምራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡

ሰው ክቡር ፍጡር በመሆኑ ሳይበድልና ሳያጠፋ ሕይወቱን ማጥፋት በሰማያዊው መንግሥትም ሆነ በምድራዊው መንግሥት ወንጀል፣ ኃጢያትና የተወገዘ መሆኑን ፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡ ቃየል የወንድሙን ደም አፍስሶ በመግደሉ የወንድሙ ደም በእግዚአብሔር ፊት ሲከስ መኖሩን ጠቁመው፣ ‹‹የሰው ደም በጣም ከባድ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ይጮኻል፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር አዕምሮ ሰጥቷችሁ ወደ ትክክለኛ መስመራችሁ እንድትመለሱ እንማፀናለን፤›› በማለት፣ በአሁኑ ወቅት እኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ለምነዋል፡፡ ‹‹ሰው ሰውን፣ ወንድም ወንድሙን ለምን ይገድላል? ይኼ በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው፤›› ብለው ሁሉም ወደ አዕምሮው እንዲመለስ ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

አንድ ጊዜ ሃይማኖት፣ ሌላ ጊዜ ፖለቲካ ምክንያት እየተደረገ የሰውን ሕይወት ማጥፋትና አገር እንድትበጠበጥ ማድረግ ኃጢያትና በደል በመሆኑ፣ በተለይ ወጣቶች የሴረኞች መጠቀሚያ ከመሆን ራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡ ወጣቶች ‹‹አገር ተረካቢ ብትሆኑም ‹‹የትኛውን አገር ነው የምትረከቡት? እየተበጠበጠች ያለች አገር? በዘር፣ በጎሳ፣ በልዩ ልዩ ጥላቻ የተበከለች አገር? ይኼንን አንመኝላችሁም፤›› ብለው፣ ሰላማዊ ኢትዮጵያን ለመረከብ አዕምሯቸውን ወደ ሰላምና አንድነት እንዲያዞሩ ጠይቀዋል፡፡ በኃጢያት ምክንያት አገር ስለምትረገም እግዚአብሔር እንደሚቀጣ ጠቁመው ሁሉም ለአገሩ፣ ለወገኑና ለራሱ በማሰብ እስካሁን ይኖር እንደነበረው በአንድ ላይ እንዲኖር ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ካስተላለፉት መልዕክት ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የተናገሩት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የጉባዔው የበላይ ጠባቂ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ፣ የአገር መሪ በመሪነት ተግባሩ ላይ፣ ፖሊስ በፖሊስ ሥራው፣ ደኅንነቱ በተመደበበት ሥራ፣ ጦር ሠራዊቱ በአገር ጥበቃ ሥራ፣ ሁሉም በተሰማራበት ተግባር ላይ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ሥራው ምንድነው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አስተማሪ፣ አባትና እናት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡና ታናናሾች ታላላቆቻቸውን ካላከበሩ፣ ተመሪ መሪውን ካላከበረ አገር አገር ሆኖ እንደማይቀጥል አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መሪ፣ ባለሥልጣንና የሃይማኖት አባቶች የሚሰደቡበት ወቅት መሆኑን የገለጹት የበላይ ጠባቂው፣ ‹‹ግን እንደዚህ ዓይነት ሥርዓት ከየት ነው የመጣው? ከውስጥ ነው ወይስ የውጭ ጠላት ነው ያመጣብን?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን እንዴት እርስ በርሳችን እንገዳደላለን? እናፈናቅላለን? ሰውን ሰው እንዴት ያርዳል?›› በማለት ጥያቄያቸውን አክለው፣ ይኼ የሰው ሳይሆን የአውሬ ፀባይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዝም ብሎ ያየውን የሚበላ፣ ያገኘው ነገር ላይ የሚወጣና ዝም ብሎ የሚከተል እንስሳ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የሰው ልጅ አዕምሮ የተሰጠው ጥቅምና ጉዳቱን ለይቶ ማወቂያ በመሆኑ፣ እንደ ሰው በአዕምሮ ማሰብ ተገቢ መሆኑን በማስታወቅ በክልሉ የተደረገውን ጥቃት አውግዘዋል፡፡

‹‹አመራሮቻችን ምንድናቸው? አገር ጠባቂውና ኃላፊው ራሱ አጥፊ ከሆነ አገርን ማነው የሚጠብቀው?›› በማለት የጠየቁት ሐጂ ዑመር፣ ዛሬ ሕዝብን የሚመራው ሥልጣንና ገንዘብ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ገንዘብና ሥልጣን የሚገኘው ወይም የሚፈለገው በውንብድና ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አላህ ሀብታምም፣ ደሃም፣ መሪም መፍጠሩን ጠቁመው ፈጣሪ ካልቀደመለት ግን ደሃ፣ ሀብታም መሆን እንደማይችልና መሪም መሪ ሊሆን እንደማይችል ልብ ሊባል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹እርስ በርስ ስንተራረድ መሪዎች ዝም ማለታቸው ተቀባይነት የሌለውና የሰው አዕምሮም የሚቀበለው አይደለም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉን በተመለከተ፣ ‹‹ለምን ችግሩ ከመድረሱ በፊት አልተጠበቀም? አስተዳደሩስ ያለው የት ነው? ጠባቂዎች ራሳቸው ወነበዱ ማለት ነው? ታዲያ አገርን የሚጠብቀው ማነው?›› የሚሉ ጥቄዎችን አንስተው፣ ንግግር ተግባር ላይ ካልዋለ ምንም እንደማይጠቅም በመግለጽ፣ ሁሉም ሥራውን አውቆ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

ሃይማኖቶችና ዕውቀት የስድብ፣ የተንኮል፣ የሸርና የክፋት ምንጭ ሲሆኑ እየታዩ መሆኑን ጠቁመው፣ የቀድሞ መሪዎች ግን አገር በጥሩ ሁኔታ መርተውና አስረክበው ማለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሁሉም ወደ አዕምሮው እንዲመለስና በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንዲኖር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ተማፅነዋል፡፡

ሌሎችም የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ ጉባዔው ለሁሉም ኢትዮጵውያን ባለ ሰባት ነጥብ የሰላም መልዕክት አስተላልፏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...