የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ ከሚያከናውናቸው ውድድሮች አንዱ እሑድ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማድረግ አቅዶት የነበረው 6ኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ነው፡፡ ውድድሩ አሁን ላይ በአገሪቱ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ‹‹ይካሄዳል አይካሄድም›› የሚለው ማረጋገጫ ማግኘት እንዳልተቻለ የሚገልጹ አሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ከክልሉ ማረጋገጫ አላገኘሁም ይላል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል በላከው መግለጫ ዓመታዊ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ጥቅምት 23 ቀን በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚደረግ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ውድድሩ ቢሸፍቱ ላይ አልያም በተለዋጭ ከተማ ይደረጋል አይደረግም የሚለውን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ዝምታ መርጧል፡፡ ለውድድሩ ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ አትሌቶች ፕሮግራሙ ስለመኖሩ ቢጠይቁም መልስ ማግኘት እንዳልቻሉ ለሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው፣ ለአስተናጋጁ የኦሮሚያ ደብዳቤ እንደተጻፈለት፣ ይሁንና ይህን መግለጫ እስከሰጡበት ድረስ ክልሉ ማስተናገድ ‹‹እችላለሁ አልችልም›› የሚል መልስ አለመስጠቱን ነው ያስረዱት፡፡ በዚህም ክለቦችን ጨምሮ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚያሳትፏቸውን አትሌቶች ዝርዝር ማሳወቅ እንዳልቻሉ ጭምር አስታውቀዋል፡፡