ለአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ ኅዳር 1 ማደጋስካርን ይገጥማሉ
ከሳምንታት በፊት ከአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) መሰናበቱን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርገው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ዝግጅት ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ልምምድ እንደሚጀምር የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ ገለጹ፡፡ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ከሁሉም አካል እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ለዓመታት በውጤት ዕጦት ሲዳክር ኖሯል፡፡ ለዚህም ምክንያት ተደርጎ ሲነገር የሚደመጠው፣ በሙያተኞች ችሎታ ማነስና የዘፈቀደ አሠራር እንዲሁም የስፖርቱን ባህሪ በውልና በአግባቡ ተረድቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት የአመራር ክህሎት ዕጦት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ አብርሃም ግን፣ ቡድኑን ከተረከቡ ጀምሮ በተጨዋቾቻቸው ላይ ለውጥ እየተመለከቱ እንደሆነና ከዚህም የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችሉ ዘንድ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡
ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ሒደት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አሠልጣኝ አብርሃም፣ ‹‹በሁሉም አገሮች የምንመለከታቸው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖች በአንድ ቀን ጀምበር የተገነቡ አይደሉም፡፡ ከፋይናንስ ጀምሮ ጊዜ ተወስዶ ብዙ ዝግጅት የተደረገባቸው ብቻ ሳይሆኑ አንድ የኦሊምፒክ ዘመን የሚሰጣቸው ናቸው፤›› በማለት ተሞክሮው በኢትዮጵያ ሊለመድ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2005 ዓ.ም. ማለትም ቡድኑ ከ31 ዓመት በኋላ ለአህጉራዊ መድረክ ሲበቃ፣ በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከሁለት ዓመት በላይ ከቡድኑ ጋር እንዲቆዩ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ብሔራዊ የቡድኑን ኃላፊነት የተረከቡ አሠልጣኞች እንዲህ እንደ አሁኑ የተረጋጋ ጊዜ እንዳልነበራቸው በመጥቀስ፣ አሠልጣኝ አብርሃም የሚያበረታታ ውጤት እንደሌላቸው የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል አሠልጣኙ ከተሰጣቸው ጊዜና ካስመዘገቧቸው ውጤቶች አንጻር በማነጻጸር ጥያቄ ቀርቦላቸውም ነበር፡፡
ውጤቱ ከተሰጠው ጊዜ አኳያ በሚለው እንደማይስማሙ የሚናገሩት ዋና አሠልጣኙ፣ ‹‹ተጨዋቾቼ ሜዳ ላይ ከነበራቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴና ብልጫ በመነሳት የተገኘው ውጤት በእርግጥም የሚያስቆጭ ነበር፣›› ብለው፣ ለዚህ ደግሞ ዘጠና በመቶ ወጣት የሆነን ቡድን ከመገንባት ጎን ለጎን ተያያዥና መሠረታዊ ሥራዎች ከሆኑት አንዱ ከጨዋታ ብልጫ ጋር የሚገኝ የጎል ዕድል መጠቀም አለመቻል እንደሆነ፣ አሁንም ቢሆን እንዲህ የመሰሉ ክፍተቶች ሊታረሙ የሚችሉት በጊዜ ሒደት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ ከፊት ለፊቱ ይጠብቀዋል፡፡ ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያ ኅዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሜዳው ውጪ ወደ ማዳጋስካር አቅንቶ አንታናናሪቮ ላይ ይጫወታል፡፡ ብዙም የማገገሚያ ጊዜ ሳይኖረው በሜዳውና በደጋፊው ፊት ለጊዜው የሚጫወትበት ሜዳ ባህር ዳር ይሁን መቐለ ስታዲየም መሆን አለመሆኑ በፌዴሬሽኑ ባይገለጽም፣ ኅዳር 9 ቀን ከአይቮሪኮስት ጋር እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ አሠልጣኝ አብርሃም፣ ቡድናቸው ከማዳጋስካሩ ጨዋታ በፊት ቢቻል በአካባቢው ከሚገኙ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ከአንዳቸው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እያመቻቹ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቡድናቸው በነበረው የዝግጅት ሒደት፣ ምንም እንኳ ውጤቱ የስፖርት ቤተሰቡ የሚፈልገውን ያህል ባይሆንም፣ በእሳቸው እምነት መሻሻል የሚስተዋልበት እንደመሆኑ መጠን በምድብ ማጣሪያው የተሻለ ነገር ለመሥራት ዕቅድ ያላቸው ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሙያተኞች በበኩላቸው፣ የሥልጠናው ክፍተትና የተጨዋቾች የብቃት ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጠቅላላው የስፖርቱ ዘርፍ መሠረተ ሰፊ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየባሰባቸው በመጡበት በዚህ ወቅት፣ የግጭትና የፖለቲካ ግርግር መናኸሪያ መሆን የጀመሩት ማዘውተሪያዎች ለብሔራዊ ቡድኑ የኋልዮሽ ጉዞ አንድ ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ጋር በመሆን ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲስተዋሉ የነበሩ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልና ግርግር እንዲሁም ሁከት ከስፖርቱ ማዘውተሪያዎች አካባቢ እንዲወገድ ካልተደረገ፣ የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት መሻሻል ቀርቶ አሁን ያለበትን ደረጃ ማስቀጠል እንደሚከብድ ሥጋት አላቸው፡፡