Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊአፍሪካውያን ሕፃናት በውትድርና

አፍሪካውያን ሕፃናት በውትድርና

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች አህጉር ነች፡፡ ሀብት የለገሳት ብትሆንም፣ ሀብቷን ለመጠቀም አልታደለችም፡፡ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች አንዴ በቸነፈር ሲመቱ አንዴ በጦርነት ሲታመሱ ዓመታትን ዘልቀዋል፡፡ የጤና ቀውስም የቀጣናው መለያ ነው፡፡ ከዚህ እኩል በየአገሮቹ የሚነሱ ግጭቶች አፍሪካ ከድህነት አረንቋ እንዳትወጣ ምክንያት ሆነዋል፡፡

አፍሪካ ምን አጣች? ሲባል መሠረተ ልማት፣ መልካም አስተዳደር፣ አገር ወዳድ መሪ ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በሚፈጠረው ግጭት ሕፃናት ሳይቀሩ ጦር የሚታጠቁባት አህጉርም ናት፡፡

- Advertisement -

በአፍሪካ ይበልጥ ችግሩ የሚበዛው ደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ኒጀር፣ ሶማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ ነው፡፡

በእነዚህ ችግሩ ይበልጥ ይባባስ እንጂ በተለያዩ የሕዝብ ተቃውሞዎችም በርካታ ሕፃናትና ታዳጊዎች በአመፅ እየተሳተፉና ፅንፍ ለያዙ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እየሆኑ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ ግጭቶች በተነሱ ጊዜ በመንግሥትና በሌሎች አማፅያን ቡድኖችም ሕፃናት ለወታደርነት ይመለመላሉ፡፡

ችግሩም ሥር ሰዶ ለአህጉሪቱ ራስ ምታት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመምጣታቸው በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ግጭት ባለባቸው የአፍሪካ አገሮች ምግብ፣ ውኃና መጠለያ ቀርቶ በሕይወት መኖር የዕድል ጉዳይ ሆኗል፡፡ በተለይ ሕፃናትና ሴቶች ይበልጥ ለችግሩ ተጋላጭ ሆነዋል፡፡

የማሊ ተወላጇ ፋቲ የ14 ዓመት ታዳጊ ናት፡፡ ግጭት ባለባቸው ቦታዎች እንደ እርሷ የሚኖሩ ሕፃናት ኑሯቸው አስቸጋሪ መሆኑን ሰሞኑን በአፍሪካ ቻይልድ ፖሊስ ፎረም በተካሄደው መድረክ ላይ አውስታለች፡፡

ፋቲ ‹‹በማሊና በሌሎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናትና ታዳጊዎች ዘላቂነት ያለው ትምህርት፣ ደኅንነት፣ ወደፊት ትልቅ ቦታ የመድረስ ተስፋን አጥተዋል፡፡ ግጭት ባለበት አካባቢ የምናድግ ሕፃናት፣ በየአካባቢው ባለው ውጥረት ሳቢያ እንቅልፍ እንኳን መተኛት ለእኛ ከባድ ነው፤›› ብላለች፡፡

በአፍሪካ አሁንም ድረስ ሕፃናት አሳታፊ ጦርነት እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ጥናቶችና መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም፣ መሪዎቿና የታጠቁ አማፂያን ግን  ሕፃናትን ከመታደግ፣ አህጉሪቱን የሰላም ቀጣና ከማድረግ ይልቅ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በሚያደርጉት ትርምስ ችግሩ እልባት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እ.ኤ.አ. በ2015  ባወጣው ሪፖርት፣ በደቡብ ሱዳን ሕፃናት ከመጠን ያለፈ በደል እንደሚደርስባቸው አስፍሯል፡፡ ‹‹በሕፃናት ላይ የተከፈተው ጦርነት ይቁም፤›› በሚል ባወጣው ሪፖርትም 420 ሚሊዮን ሕፃናት በጦርነት ቀጣና ውስጥ እንደሚኖሩ አስፍሯል፡፡

ሪፖርቱ፣ በዓለም ለሕፃናት በጣም አስከፊና በግጭት ከታመሱ ቀዳሚ አሥር አገሮች ስድስቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ ያመለክታል፡፡ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ ከመጀመርያዎቹ የግጭት አገሮች ተርታ ሰፍረዋል፡፡

ደቡብ ሱዳናውያኑ የ16 ዓመቱ ታዳጊ ጉድፌርና እህቱ ኡጋንዳ ቢዲቢዲ የስደተኞች መጠለያ ይኖራሉ፡፡ ጉድፌር ‹‹አባቴ የተገደለው በታጠቁ ኃይሎች ነው፡፡ እየመጣ ሳለ የተኩስ ልውውጥ ተጀመረና እርሱም መተኮስ ቀጠለ፡፡ ለመንግሥት ይሠራ የነበረው አባቴ በተኩስ ልውውጡ ተገደለ፤›› ይላል፡፡

ጉድፌር ከደቡብ ሱዳን እርሱና እርጉዝ እህቱን ይዞ ይወጣል፡፡ ይሁን እንጂ እህቱ በወሊድ ጊዜ በገጠማት ሕመም ልጇ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ‹‹ውኃና ምግብ የለም›› የሚለው ታዳጊው፣ በመጠለያው ከገቡ በኋላ በሕፃናት አድን ድርጅት በጎ ፈቃደኛ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ልክ እንደ ታዳጊው ጉድፌር በአፍሪካ የተለያዩ እንግልትና ከአቅም በላይ የቤተሰብ ኃላፊነት የተሸከሙ ሕፃናት እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ አሁንም ወደ ትግል የሚገቡ አሉ፡፡

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እ.ኤ.አ. በ2013 ከ132 ሺሕ በላይ ሕፃናት በጦርነት ሳቢያ ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል፡፡ 99 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናትም በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን ፕላን ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ. በ2017 ባወጣው መረጃ አስፍሯል፡፡

በፖለቲካ፣ በሽብርተኝነትና በሌሎች ግጭቶች ሳቢያ በኬንያ፣ በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲ፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ግጭት ተከስተው ያውቃሉ፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ሶማሊያ የተረጋጋ ሰላም የለም፡፡

አሁን ላይ በርካቶቹ ወደ መኖሪያቸው ቢመለሱም፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ሦስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሶማሊያ የሕፃናት ጠለፋ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ለጦርነት ብሎ ታዳጊ ሕፃናትን መመልመል በከፍተኛ ደረጃ ይከናወናል፡፡

የአፍሪካ ቻይልድ ፖሊስ ፎረም ዳይሬክተር አሰፋ በቀለ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ሕፃናት ላይ አሳታፊ ጦርነት አለ ለማለት ጥናት ያስፈልጋል ቢሉም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለው ግጭት በዚሁ ከቀጠለ ልጆችን ወደ አሳታፊ ጦርነት ሊገባ ይችላል ብለዋል፡፡

ባለፉት አሠርታት በአፍሪካ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ወታደር ሆነው መሞታቸውን አንዳንድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2004 የተሠራ ጥናት፣ በአፍሪካ 100‚000 ሕፃናት ለወታደርነት መሠለፋቸውን፣ በ2008 የተሠራ ጥናት ደግሞ 120‚000 ሕፃናት ወታደር መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ይህ ቁጥር በዓለም ካሉ ሕፃናት ወታደሮች 40 በመቶውን ይይዛል፡፡

በርካታ የሕፃናት ወታደሮች ያሏት አገር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናት፡፡ በአፍሪካ በርካታ ሕፃናት ወላጅ የሚያጡትም ሆነ ለከፋ ድህነት የሚጋለጡት በጦርነት ምክንያት ነው፡፡ ወላጆች ደግሞ ድህነትን ለማራገፍ ሕፃናት ልጆቻቸውን በውትድርና ያስቀጥራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም አማፅያንም ሆኑ በግጭት ውስጥ ያሉ መንግሥታት ሕፃናትን ለጦርነት ይጠቀማሉ፡፡

ሕፃናት ቤተሰቦቻቸውን በማየት ውትድርናን ከልጅነት የሚጀምሩበት አጋጣሚም በተለይ ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ አፍሪካን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...