እነሆ መንገድ! ከቦሌ ወደ ሳሪስ ልንጓዝ ነው። የማጣትን ታሪክ ወሽመጡን ሊበጥስ ለኑሮ ትግል አቅሙ የደረሰ ሁሉ ከፍ ዝቅ ይላል። በድንቅ አብቃይ ምድር ኩርንችት ሲለቀም ዘግይቶ እየገባን ሲመሽ ያባባናል። በይሆናል ይዘው ያሳደሩት ጉዳይ ቀን እየቆጠረ የሚያስለቅሳቸው እንባቸው ጠብ ይላል። ጠብ ያለችውን ዘለላዋን ይዘው ፍሬዋን ቢቀምሱት ሰው ሆኖ መፈጠር ይብስ ያስቀይማል። በታሪክ ምንጣፍ ላይ በመታሸት ቀለም ያልጠቆረ የለም። መንገዱ ወደ ኋላ ትዝታ ብቻ ነው። ፍሬ ከለቀመው ዘር ዘርቶ የቀረው እጅጉን ብዙ ነው። ‘እህህ’ በማለት የመፈጠርን ኬላ ጥሶ ለፈጣሪ አቤቱታ የሚያሰማው እልፍ ነው። መጪውም ጎዳና በጭጋግ ተጋርዷል። ያም ሆኖ፣ በልጥ የታሰረ ርብራብ የእንጨት ድልድይ ላይ ያበጠው ይፈንዳ ብሎ የሚጓዘው ደግሞ ጥቂት አይባልም።
ፍጥረት እንደ ሰንበሌጥ ከወዲያ ወዲህ ሲወዛወዝ ቀልብ የለውም። ጎዳናው ግን ሚስጥሩ የተቋጠረው በአቅጣጫው ሳይሆን በመፈጠር ዕዳ መሀል ላይ ብቻ ይመስላል። በሮጡበት መስክ ሁሉ ደፈንኩት ያሉት ቀደዳ ጎህ ሳይቀድ አፍስሶ የሚያድርባት ዓለም ናትና። ይህችን የሕይወት ሽንቁር ማድጋ በውኃ ለመሙላት ዕድሜውን ሁሉ ወንዝ የሚመላለስ ትውልድ ይመጣል፣ ይሄዳል። አንዳንድ የዘመኑ ተራቃቂዎች ይህን ቅስም ሰባሪ ወለምታ ‘‘መተካካት’’ ይሉታል። ትውልድ ይመጣል፣ ትውልድ ይሄዳል! ፀሐይና ጨረቃ ይተካካሉ፣ ሌትና ቀን፣ በልግ፣ ሃጋይ፣ ፀደይና ክረምት ይፈራረቃሉ። ‘መላ ያጣ ነገር ቅጡ እየተዛባ፣ ሲዞር ሲዞር ኖሮ ልቤ ገደል ገባ’ ሲያሰኘው አንዳንዱን፣ ሌላውን ዙሩ ምንም ሳያደክመው ስንፍናውንና ግዴለሽነቱን ጠግቦ ይሸኛል። የሁለቱም ዕጣ አንድ አፈር ይሰኛል። አፈሩን ያቅልልንና!
ታክሲ ውስጥ ገብተናል። ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹አይ ዛሬ ቀን! አይ ዕድሌ!›› ያጉተመትማል አንድ ጎልማሳ። ‹‹ምንድነው እሱ? ምንድነው የምትለው?›› ወያላው እሱን መስሎት ይጮህበታል። ‹‹ኧረ እባክህ አንተ ሰውዬ ተወኝ ወዲህ ነው። ኧረ! ኧረ! ምን አደረግኩህ?›› ወደ ላይ አንጋጦ የዛቻ ያህል ከምስቅልቅሉ መነሻ ጋር በሐሳብ ይፋጠጣል። ‹‹ምን እህህ እያልክ ብቻህን ታምጠዋለህ? የሆንከውን ንገረንና መፍትሔ እንፈልግ! ካልሆነ ዝም በል፤›› አለው ከአጠገቡ የተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ። ቀጠለና ደግሞ፣ ‹‹ከዚህ የበለጠ በሽታ አለ ግን? ሲሞላልንና ሲሳካልን የምንደነፋውን ያህል ባይሆን እንኳ ምነው ሲያመን ብንናገር? ሁሉን በሆዳችን ይዘን ሁሉን በሆዳችን ሰፍረን እንችላለን እንዴ?›› ይላል። ጋቢና የተሰየመች መለሎ፣ ‹‹ቆይ አንተ የሆድ ሐኪም ነህ? ወይስ ጆሮ ጠቢ? ምነው ይኼን ያህል የሰው ቁስል አሳከከህ?›› ትለዋለች ሳይሰማት። ይኼኔ ሰውዬው ችግሩን ማውራት ይጀምራል።
‹‹እኔ አላመመኝም! ምን ሊለኝ ነው እናንተ! እኔ ‘ዲግሪ’ ያለኝ ሰው ነኝ። ሥራ ልወዳደር ከክልል ነበር የመጣሁት። እዚህ ስደርስ ያመጣኝ ‘አይሱዙ’ የመጣህበትን ክፈለኝ ብሎ የዲግሪ ምስክር ወረቀቴን ወሰደብኝ። መላው ጠፍቶብኝ ነው እባካችሁ? እኔ ልመና አልችልበትም፤›› አለና ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ ‹‹እባካችሁ እኔ ለአገሩ እንግዳ ነኝ። መሳፈሪያዬ 350 ብር ስለሆነ ብታወጡልኝና አገሬ ብገባ? እንዲያው ሌላ አላስቸግርም፤›› ብሎ አረፈው። ይኼኔ የሰማውን ሰምቶ አላስችል ያለው (ያላመነው) መተረብ ጀመረ። ‹‹ዝም አትበሉ እንጂ እሳት አደጋ ጥሩ! የፀሐይዋ ቃጠሎ ሳያንሰን ደግሞ በባለዲግሪ እንቃጠል? ወይ ዘመን?›› ሲል ከአጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ከፊታችን ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አዛውንት ቀበል አድርገው፣ ‹‹እንደ እኔ አስተያየት እንደ ዘንድሮ የአለማመን ሥልት መራቀቅ ከሆነ ለመረዳዳት የምናዋጣው ገንዘብ ሳይቀር በ‘ሳይበር አታክ’ እንዳይዘረፍ ነው፤›› አሉ። ወዲያው ለቀልድና ለተረብ ይራኮት የነበረው ተሳፋሪ ሁሉ፣ በአዛውንቷ አስተያየት ከማግጠጥ ተቆጥቦ እንደ መደንገጥ ሲል ይታያል። ‹‹መንገድ ለመንገድ አልችለው ብለናል ልመና ጭራሽ በቴክኖሎጂ ሊታገዝ? የለንማ!›› የሚለው ብቻውን ይስቃል፡፡ ዘመኑ እንዲህ ሆኖ ይረፈው?
አዛውንቷ ሳያስቡት የፈጠሩት ድንጋጤ ሰውዬው ላይ ከማሾፍ ይልቅ ቁጣ ፈጥሯል። ‹‹አንተ መጀመርያም መሳፈሪያ ሳይኖርህ ነው ሰው መኪና ላይ የምትወጣው?›› ሲል መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት ያፋጥጠዋል። ይኼን ሰምቶ ወያላው ሒሳብ ብሎ ቀድሞ ራሱኑ ጠየቀው። ‹‹ተቸግሬ እያየኸኝ ጭራሽ አንተም ሒሳብ ትለኛለህ? እኔ እየዋሸሁ አይደለም። እመብርሃንን! ነገርኳችሁ እኮ! ያመጣኝ የአይሱዙ ሾፌር ዲግሪዬን ይዞብኝ ጠፋ። እሺ በምን ሥራ ልወዳደር? እባካችሁ የሰው አገር ሰው ነኝ፤›› ተሳፋሪውን ለማሳመን ሲረባረብ ታክሲያችን ቆማለች። ፊቱን በደንብ ያለየነው ጋቢና የተሳፈረ ጎልማሳ፣ ‹‹ቆይ ግን ዲግሪው በግዥ ነው ወይስ የምር ቀልመሽ ነው? ዘንድሮ ዲግሪና ድርጊቱ አመራማሪ ሆኗል አሉ፤›› ብሎ ሳይጨርስ ሾፌሩ፣ ‹‹አስወርደው ይኼን ቀጣፊ!›› ብሎ ጮኸ። ወያላው በክብር ከተቀመጠበት ሦስተኛው ረድፍ ጎትቶ ሰውዬን አስወረደው። ከመውረዱ የእርግማን ዶፍ ያዘንብብን ጀመር።
በቆመበት ጥለነው ጉዟችንን ስንቀጥል፣ ‹‹ይህን ሰውዬ እዚህ አውላላ ሜዳ ላይ አውርደነው ኋላ ባቡር ሐዲዱ ላይ ሄዶ ራሱን ቢያጠፋ የለሁበትም፤›› ይለኛል ጠጋ ብሎ አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ። ‹‹እንዴ ካልጠፋ የቀለበት መንገድ? ባቡራችን ላይ ማሟረት ምንድነው? ሰው እንደሆነ መኪናና ፈጣሪን እንደሚዳፈረው በጠራራ ፀሐይ መብቱን የሚጋፉትን ሰዎች አይዳፈርም፤›› ብላ ሂጃብ የጠመጠመች ከኋላችን የተቀመጠች ሴት ተናገረች። መጨረሻ ወንበር ደግሞ፣ ‹‹በቃ እኛ አዲስ መንገድ የምንመርቀው በአደጋ ብቻ ሆነ? ምን ይሻለናል ግን?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ ጥሎብን ነዋ! ጥሎብን!›› ትለዋለች ነገር ነገር የሚላት ካጠገቡ ያለች ሴት። በላይ በላይ ሳይበስሉ የሚከስሉብን ነገሮች ሳያንሱ አሁን እስኪ በትንሽ ትልቁ ነገር ትን ሲለን ምን ይባላል እናንተ? ወይስ እንደምትለው ጥሎብን ይሆን? ቅጥ ያጣ ጎዳና!
ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው፣ ‹‹ጫፍ ላይ ወራጅ አለ? ባይኖርም የኢንሹራንስ መብቴን ብነፈግ ነው፤›› እያለ ከምንጊዜው 12 የነበርነውን 18 እንዳደረሰን አይታወቅም። አንዳንዶች የወያላውን ጮሌነት ሲያዳንቁና ሲተቹ አንዳንዶች፣ ‹‹እቅጩን የሚነግረን ሰው ስላጣን ነው እንጂ ቁጥራችን 100 ሚሊዮን አልፏል ወይስ አላለፈም?›› እያሉ ባልተያዘ ነገር ነገር ይማዘዛሉ። ‹‹በቃ እኔ ላስታርቃችሁ የመኪና አደጋ በየቀኑ የሚቀንሰውን ሕዝብ ካሰባችሁት ነው እንጂ 100 ሚሊዮንማ ምን አላት?›› ሲሉ አዛውንቷ ጣልቃ ገቡ። ከረር ያለው ጨዋታ ባለወግ በሆኑት አዛውንት ሰበብ መለዘብ ሲጀምር፣ ‹‹እውነትዎን እኮ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከኢቦላና ከኤችአይቪ/ኤድስ ከመሳሰለው በሽታ ልቤ የምትበረግገው ለትራፊክ አደጋ ሆኗል። በተለይ ‘ሲኖትራክ’ የሚሏቸው መኪኖችን ሳይ በቃ ሞት በጥሩ ዋጋ ተከራይቶ የሚሠራባቸው እስኪመስሉኝ ድረስ ቶሎ ብዬ ንሰሐ እንደገባሁ ነው፤›› ብላ ጋቢና ያለችው ተናገረች።
አጠገቧ ያለው ተቀበለና ደግሞ፣ ‹‹ምን ይደረግ መንጃ ፈቃድ እንደ ቀበሌ መታወቂያ ያለ ማሽከርከር ብቃት አንስተው ያድሉዋቸዋል፡፡ 70 እና 100 ኩንታል ጭነው እንደ ንፋስ ሲበሩ እንደ አውቶሞቢል በአንድ እርግጫ ፍሬን የሚቆሙ ይመስላቸዋል። መቼም እኛ ሆነን አሥር ሲሞትብን መቶ ሺሕ እያረገዝን ባንወልድ ኖሮ ምድሪቷ በግሪሳና በቁራዎች ‘ፓርቲ’ አትደምቅም ነበር፤›› ይላል። የዕለት እንጀራውን ማግኘት ማጣቱ የወዘወዘው ተሳፈሪ በበኩሉ፣ ‹‹ተው ሳበው ሳበው መሸብኝ፣ የጆቢራ ራት ግብር አለብኝ፤››ን በኤፍ ኤም የሚጋብዝ ይመስል አሥር ጊዜ ስልኩን ይነካካል። አንዳንዱ ፍጥነትን ከድህነት ማምለጫ መሣሪያው አርጎ ሲቆጥር፣ ሌላው በአጭር እየቀረ መንገድ ይቀራል፡፡ አያድርስ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። እንደ ግምጃ ቤት ሰው በሰው ላይ አነባብሮ አሳፍሮ ማመላለስ ከመለመዱ የተነሳ፣ ሕጋዊ አድርገን ማሰብ መጀመራችንን ያወቅነው የትራፊክ ፖሊስ ሲያስቆመን ነው። ሾፌራችን መንጃ ፈቃድ እንዲያሳይ ሲጠየቅ እየተቅለሰለሰ ከመኪና ወርዶ ይለማመጥ ጀመር። ‹‹እንዲህ ተነባብረንም አልቀለለልን እንኳን በ‘ቪአይፒ’ በምቾት ተጓጉዘን፤›› ሲል አንዱ ጨዋታ ጀመረ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በሁለት ቢያጆ ያገኛታል ለምን ይለማመጠዋል?›› ይላል። የትራንስፖርት እንግልቱ ሕግና ሕጋዊነትን ያስረሳን ይመስላል። የትራፊክ ፖሊሱ መንጃ ፈቃድ የማያሳየው ከሆነ ታርጋ እንደሚፈታና መኪናዋን እንደሚያስራት በትህትና ለሾፌራችን ደጋግሞ ሲነግረው፣ የቅጣት ወረቀት ከኪሱ አውጥቶ አሳየ። የትራፊክ ፖሊሱ ሌላ የቅጣት ወረቀት ሲጽፍ፣ ወበቁ መፈጠሩን ያስጠላው በትዕግሥት ተቀምጦ ሲጠባበቅ፣ ያላስቻለው እየወረደ ቀሪውን መንገድ በእግሩ ተያያዘው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሕግና ሕጋዊነት በሁለት ጽንፍ ሊያባላን ደርሷል። ገሚሱ ከግል ጥቁሙ አንፃር ብቻ፣ ‹‹ሕግ ተለዋዋጭና አመዛዛኝ ካልሆነ ምን ዋጋ አለው?›› ይላል። በዚህ የማይያዝ የማይጨበጥ ሐሳብ አንጀታቸው ካረሩት ተሳፋሪዎች አንዱ አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ ነው። ‹‹እኮ እንዳንተ አባባል ከሆነ ‘ዴሞክራሲን’ በመልካቸውና በአቋማቸው ልክ ሰፍተው የሚለብሱም አይፈረድባቸውም፤›› ይለዋል። ‹‹ኧረ እኛ ማንኛችሁንም አንመርጥም! የምን ላም ባልዋለበት ኩበት መልቀም ነው? ምነው ፆም ገና ከመግባቱና የሳምንቱ መጀመርያ አጋማሽ ላይ ሙግት መግጠም?›› ስትል ከጋቢና አዛውንቷ ተቀብለው፣ ‹‹ተይኝማ ልጄ ቅበላን አታንሽብኝ። እኛ ድሮ ስናውቅ ቅበላ የንስሐ መግቢያ ፆም ማሟሻ ነበረ። ዛሬ ይኼው የሥጋን ሥራ ሁሉ በአንድ ቀን በአንድ ሌሊት መፈጸሚያ ሆኖ ይውል ጀመር። ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት የሚሆነው ነገር እንዲያው አልበዛባችሁም ግን?›› ብለው ሁላችንንም ተራ በተራ ሲያዩን ወያላው ድንገት መጥቶ፣ ‹‹በቃ መጨረሻ ነው በእግራችሁ ቆስቁሱት!›› ብሎን አረፈው። ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት የሚሠራ ሥራ ሁሉ እንዲህ በየመንገዱ ዋጋ እያስከፈለን እንዴት እንደምንዛለቅ ማን በነገረን? እንደማንዛለቅማ ከሰሞኑ ሁኔታችን ማየት ይቻላል፡፡ መልካም ጉዞ!