Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሎጂስቲክስ ዘርፉ መፍትሔ ያመላከተው ውይይት

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ ተግዳሮቶችና ዕድሎች›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀውና የሎጂስቲክስ ዘርፍ ችግሮች ላይ ባተኮረው የውይይት መድረክ ላይ ዘርፉ የሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስም በዘርፉ በሚታዩ ችግሮች ጥናት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶች መደረጋቸው የሎጂስቲክስ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዙ ገልጸዋል፡፡ ኢኮኖሚው በዘርፉ ጥገኛ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ዘርፉን ለማሳደግ መሥሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ብሔራዊ የሎጂስቲክ ስትራቴጂ እያረቀቀ እንደሚገኝና በዘርፉ ላይ ከተካሄደው ውይይት የሚገኙ የመፍትሔ ሐሳቦችም ለስትራቴጂው ትግበራ እንደሚያግዙ ወ/ሮ ዳግማዊት አክለዋል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በተዘጋጀው የሎጂስቲክስ ዘርፉ አገር አቀፍ ውይይት መድረክ ላይ የጂቡቲ ወደብ አስተዳደር፣ የጂቡቲ ጉምሩክ ባለሥልጣን ሌሎችም የኢትዮጵያና የጂቡቲ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሎጂስቲክ ማኅበረሰብ፣ የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስና የአቅርቦት ሰንሰለት ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር እንዲሁም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በመተባበር ያዘጋጁት ውይይት በአራት ዋና ዋና ርዕሶች ላይ አተኩሮ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ሎጂስቲክስ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው፣ በኢትዮ ጂቡቲ ኮሪደር የሎጂስቲክስ ኦፕሬሽን ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው፣ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ለሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለው ድርሻ ፈተናዎቹና መፍትሔዎቹ እንዲሁም የከተማ ሎጂስቲክስ ፈተናዎችና መፍትሔዎቹ የሚሉ ነበሩ፡፡

በውይይት መድረኩ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ከዓለም አቀፍ አሠራሮችና አፈጻጸሞች አንፃር ሲመዘን በጣም የተጓተተና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የተጠቀሰው የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የትራንስፖርት፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የወደብና ኮሪደር አጠቃቀም፣ የጉምሩክ አሠራር መጓተትና በዘርፉ ብቁ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ነው፡፡

በኮንፍረንሱ ላይ በሎጂስቲክ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር የቦርድ አባል አቶ አንተነህ ዓለሙ ሲሆኑ፣ ጥናታቸውን በኢትዮ ጂቡቲ ሎጂስቲክ ኦፕሬሽን ችግሮች ላይ አቅርበዋል፡፡

አቶ አንተነህ እንደ ችግር ሦስት ነጥቦችን ያነሱ ሲሆን፣ እነዚህ ችግሮችም የሕግ ክፍተት፣ ሰፊ የመሠረተ ልማት ችግር እንዲሁም የዕውቀት ችግር በዘርፉ በሰፊው የሚስተዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሕግ ክፍተቱን ሲያስረዱ አጓጓዦች ለሚደርስባቸው መዘግየት አስመጪና ላኪዎች፣ የጥራት ተቆጣጣሪዎች እንዲሁም ጉምሩክ ተጠያቂ መሆን አለባቸው የሚል አዋጅ እንዳለ አውስተው፣ አጓጓዦች በሚያዘገዩበት ወቅት በሁለቱ መሀል በስምምነት ይፈታ የሚል የሕግ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ ያነሱት ሁለቱንም በአንድ ማዕቀፍ አምጥቶ ሊያስታርቅ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ነው፡፡ ‹‹አንዱን አግዞ አንዱን ችላ ብሎ መሆን የለበትም›› ብለዋል፡፡

ከዕውቀት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ይኼ ነው የሚባል እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ከፍተኛ የዕውቀት ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ዓለም አቀፍ ገበያ ሎጂስቲክስን በአግባቡ እየተጠቀመ ያለበት ሁኔታ እንዳለ በመግለጽ፣ በዓለም አቀፍ ገበያው አንፃር የአገሪቱ ሎጂስቲክ አጠቃቀም 70 በመቶ አካባቢ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ማለት ከዓለም ገበያ ጋር እኩል መሮጥ የሚያስችል ዕውቀት አለን ለማለት እንደማያስዳፍር ተናግረዋል፡፡

አቶ አንተነህ ‹‹የሚመለከታቸው አካላቶች በመገኘታቸው እኛ እንደ ችግር ያነሳናቸውን ክፍተቶችና የመፍትሔ ሐሳቦችን ወስደው ብሔራዊ ሎጂስቲክ ስትራቴጂ በማለት እየተራቀቀ ባለው የሎጂስቲክ የአሠራር ማዕቀፍ ላይ በማካተት የተሻለ ነገር ለነገ ይኖረናል፤›› በማለት ከዚህ ኮንፍረንስ ለነገ የተሻለ ነገር እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ሐሳባቸውን ያጋሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚ መምህር የሆኑት ቡሻ ተመስገን/ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ መምህሩ በቅድሚያ ያነሱት የትራንስፖርት ችግሩን ሲሆን ከመኪና፣ ከመንገድ እንዲሁም ወደብ አካባቢ ማነቆ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ያነሱት ችግር ከሕግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ገቢና ወጪ ዕቃዎች ሲነሱ ብዙ የሚመለከታቸው አካላት እንዳሉ ገልጸው፣ እንደምሳሌ ዕፅዋትና እንስሳት አካባቢ ግብርና ሚኒስቴርን፣ ጤና ነክ ሲሆን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን፣ እንዲሁም ከፍቃድ ጋር በተገናኘ ንግድ ሚኒስቴርን በማንሳት ‹‹እነዚህ የተለያዩ አካላቶች በየዘርፋቸው የሚያወጧቸው ሕጎች አሉ ነገር ግን የሕጎቹ አለመግባባት ወይም አለመናበብ በርካታ ችግሮችን አምጥተዋል፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባድ መኪኖችን አስመልክቶ የወጣውን ሕግ እንደምሳሌ በማንሳት፣ ‹‹ሕጉን ተከትሎ አበባ ላኪዎች ምርታቸውን ከእርሻ ቦታ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ማምጣት አልቻሉም፡፡ አበባ ደግሞ በባህሪው የሚበላሽ በመሆኑ ለመጉላላት ተዳርገው ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲገልጹ ሕጉን የሚያወጣው አካል ያልተናበበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ጊዜ ገንዘብ ነው›› የሚሉት እኚህ መምህር፣ አንድ ዕቃ ለተጨማሪ ቀን በተቀመጠ ቁጥር ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚወጣና መጨረሻ ላይ ጫናው ተጠቃሚው ላይ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

‹‹አንድ ሰው ጤናውን ቶሎ የሚያጣው ትራንስፖርት ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ ነው፤›› በማለት ከአሽከርካሪ ማሰማራት ጀምሮ ነዳጅ፣ እንዲሁም የመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ የማጭበርበር ሥራዎች በሰፊው እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የተነሱትን ሐሳቦች ከግምት በመክተት ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች ይፈታሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የሎጂስቲክ ሥርዓት ማለት በአንድ በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ዕቃን ከምንጩ ተጠቃሚው ጋር በትክክለኛው ጊዜና ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ ማድረስ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የዕቃ፣ የመረጃ እንዲሁም የገንዘብ ፍሰት ያለበትና እነዚህን ሁሉ ደግሞ በትክክለኛው የንግድ ሥርዓት ለዕቃዎቹና ለአገልግሎቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄና ጥበቃ በማድረግ መምራትን ያካትታል፡፡

የዓለም ባንክ የአገሮችን የሎጂስቲክ አፈጻጸም መለኪያ የሚያወጣ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ኢትዮጵያ ከ160 አገሮች 126ኛ ደረጃ ላይ ነበረች፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በተገኘ መረጃ በሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ላይ አመርቂ ሥራዎች ባለመሠራታቸው ደረጃዋ በአምስት ዝቅ ብሎ 131ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

ይህንንም ከግምት በመክተት ሥርዓት ተኮር የሆኑ እልባቶችን ለመስጠት ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ (ከ2011 እስከ 2020 ዓ.ም.) አዘጋጅታ አፅድቃለች፡፡

በዚህም መሠረት ጭነትን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የባንክ ፍቃድ ከመጠየቅ ጀምሮ ዕቃው በአገር ውስጥ እስከ መረከብ የሚወስደውን ጊዜ ከ123 ቀናት ወደ 40 ቀናት መቀነስ፣ ገቢ ዕቃዎች ከመረከብ ከተራገፈበት ቀን ጀምሮ በአገር ውስጥ ለመረከብ የሚወስደውን ጊዜ ከ46 ቀናት ወደ ሰባት ቀናት መቀነስ፣ ወጪ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በኮንቴይነር አሽጎ የመላክ አፈጻጸምን ከደረሰበት 33 በመቶ ወደ 90 በመቶ ማሳደግና የመሳሰሉትን ግቦች አስቀምጣለች፡፡

በቀጣይ የሎጂስቲክ ዘርፉን እምርታዊ ለውጥ ዕውን ለማድረግ በኦፕሬሽንና በቁጥጥሩ የሚመለከታቸው አካላት በትብብር አብረው እንዲሠሩ በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች