በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከጥቅምት 8 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. አምስተኛውን ዓለም አቀፍ ዓውደ ጥናቱን «የኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀት ዳሰሳ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ማሳለጫ አማራጭ ሥልት» በሚል መሪ ሐሳብ አካሂዷል፡፡ በአገራችን ያሉ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግሥት አግባብ ያላቸው የሚኒስቴር ከፍተኛ ተጠሪዎች ወይም ተወካዮች፣ የተጋበዙ ጽሑፍ አቅራቢ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ልዩ ልዩ ኃላፊዎችና መምህራን በዓውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ ዓውደ ጥናቱ የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ባቀረበው የወሎን ሕዝብ ቱባ የባህል ለዛ በሚያንፀባርቅ ደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከፍቶ በሚያምር ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የአብነትና መድረሳ ትምህርት ቤቶች የተጋበዙ ተሳታፊዎችም በዓውደ ጥናቱ ላይ ተካፍለዋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እነዚህ አገር በቀል ተቋማት ለአገር በቀል ትምህርት ወደ ዘመናዊ ትምህርት ሽግግር ማድረግ የነበራቸውን የማይተካ ሚና በተመለከተ «የትምህርት ፍኖተ ካርታው የመንጠላጠያ ድንጋዮች» በሚል ርዕስ የጻፈ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ስለዚህ የአገር በቀል ዕውቀት ተቋማቱ ተወካዮች በዓውደ ጥናቱ እንዲሳተፉ በማድረጉ ወሎ ዩኒቨርሲቲን ከልብ ያመሠግናል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር)፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በተጀመረው የዓውደ ጥናቱ የመድረክ ሥነ ሥርዓት፣ አግባብነት ያላቸው ሚኒስቴሮችና የሃይማኖት ተቋማት ተጠሪዎች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የፍልስፍናና የሃይማኖት ምሁራን በየተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ቁልፍ ንግግሮችንና መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
አገር በቀል ዕውቀት ሲዳሰስ
የአገር በቀል ዕውቀት አስፈላጊነት የቅንጦት አይደለም፡፡ አንዳንድ አገሮች ለአገር በቀል ዕውቀት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዕውቀት ዘርፉ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ የአገር በቀል ዕውቀትን የሚመለከት አንቀጽ አካትተዋል፡፡ በአገራችን ስለአገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ በሕገ መንግሥታችን የተቀመጠ አንቀጽ ባይኖርም እንኳ በአዋጅ ቁጥር 482/2006 የተጠቀሰ ሐሳብ አለ፡፡ በተጨማሪም አገራችን የፈረመችውን ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ስምምነት (Biodiversity Convention, 1992) መሠረት በማድረግ በተዘጋጀው ብሔራዊ የብዝኃ ሕይወት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ስለአገር በቀል ዕውቀት ጉዳይ ተጠቅሷል፡፡
ለመሆኑ የአገር በቀል ዕውቀት ምንድነው? የሚለው ጥያቄ በቡድን ውይይት ወቅት ቀርቧል፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የአንድ ማኅበረሰብ መለያ የሆነ፣ የተካበተ የነገሮችና ሁኔታዎች ዕይታ፣ የአስተሳሰብና የግንዛቤ ችሎታ ዘርፈ ብዙ የባህላዊ አሠራር ሥርዓትና ልማድ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂና ክህሎትን ሁሉ ይመለከታል፡፡ እንደ ዘርፉ ተመራማሪዎች ከሆነ የአገር በቀል ዕውቀት በሁለት ምድቦች ይመደባል፡፡ አንደኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት (Tacit) ይባላል፡፡ ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ከማኅበረሰቡ ትዕይንተ ዓለም (World View) የሚመነጭ፣ በማኅበረሰቡ የእርስ በርስ ግንኙነትና ከተፈጥሮ ጋር ባለው መስተጋብር ውጤት ላይ የተመሠረተ፣ የማኅበረሰቡን የጋራ ማንነት ገላጭ የሆነና ማንኛውም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ሁሉ ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ሥነ ቃል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ አፈ ታሪክ፣ ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ ሞራል፣ ዘርፈ ብዙ የማይዳሰስ ባህል፣ የአሠራር ሥርዓታት (የቅራኔ አፈታት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና ልማት፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአለባበስ፣ የዳኝነት፣ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ወዘተ) ሁሉ በዚህ የአገር በቀል ዕውቀት ምድብ ይካተታል፡፡ ይህ የአገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ ከማኅበረሰቡ የጋራ ሥነ ልቦናና ታሪክ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ የዕውቀቱ መጥፋት ወይም መዳከም የማኅበረሰቡ ማንነት መዳከም ወይም መጥፋት አመልካች ነው፡፡ ዕውቀቱ እንደ ማኅበረሰቡ የዕድገት ደረጃ በሥነ ቃል ወይም በሥነ ጽሑፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ሁለተኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት በጠበብት ወይም የአካባቢ ባለሙያዎች የተያዘ ዕውቀት (Explicit) ሲሆን፣ የዕውቀቱ ባለቤቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ታቅፈው የሚኖሩ በመሆኑ በግል የያዙት ዕውቀት የማኅበረሰብ ዕውቀት አካል ነው፡፡ ይህ ዕውቀት የአካባቢውን ማኅበረሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ አያያዝና ጥበቃ ሥርዓት የሚጠቁም ሲሆን፣ ዕውቀቱ በብዙኃኑ ሲሰርፅና ሲስፋፋ ወደ ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀት የመሸጋገር ዕድል አለው፡፡ ማኅበረሰቡ ዕውቀቱን ቀስ በቀስ የጋራ ዕውቀት (Common knowledge) ስለሚያደርገው በአንድ የአካባቢ ጠበብት ብቻ የተያዘ ዕውቀት ሆኖ አይቀርም፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የይዞታ ባለቤትነት (Patent Right) የሌለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እያንዳንዱ የጠበብት ዕውቀት ማለትም የሥር ማሽ ሕክምና፣ ሽመና፣ ሸክላ ሥራ፣ አናጢነት፣ ግንበኝነት፣ አንጥረኝነት፣ ፋቂነት፣ የአካባቢ ባህላዊ ግብርና ዘዴ (ጥምር ግብርና፣ ቅይጥ ግብርና) ወዘተ ልዩ ዕውቀት ባካበቱ የማኅበረሰቡ አባላት መንጭቶ ቀስ በቀስ በመዳበር ወደ ሌላው የማኅበረሰቡ አባል በልምድ ቅስሞሽ ሲተላለፍና በስፋት ሲሠራጭ ተቋማዊ ዕውቀት ሊሆን የሚችል የአካባቢ ማኅበረሰብ ዕውቀት ይሆናል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ የብሔረሰቦችን ሥርጭት መሠረት ያደረጉ በርካታ የአገር በቀል ዕውቀቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ86 በላይ ብሔረሰቦች የሚጋሯቸውና አንዱ ከሌላው የሚለዩባቸው የአገር በቀል ዕውቀቶች አሏቸው፡፡ ይሁን እንጂ የአገራችን የዘመናት ተጨባጭ ሁኔታ በፈጠረው ዕድል በባህል ውርርስና ልውውጥ ምክንያት የአገራችን ብሔረሰቦች የበርካታ አገር በቀል ዕውቀቶች የጋራ ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ በዚህ የተነሳም በአገራችን ይህ ዕውቀት የዚያኛው ብሔረሰብ ልዩ ዕውቀት ነው፣ ያኛው የዚያኛው ብሔረሰብ ነው ብሎ በውል ለመለየት አያስደፍርም፡፡ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ አገር በቀል ዕውቀት ባለቤት ሆነናል ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የረዥም ዘመን አብሮነት የጋራ አገር በቀል ዕውቀት ተጋሪነትን የፈጠረ ይሁን እንጂ የአገር በቀል ዕውቀቱ በዘላቂነት ለማደግና መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ የተጓዘው መንገድ ምቹ አልነበረም፡፡ ሁለቱም የአገር በቀል ዕውቀት ምድቦች ዕድገታቸውን ከሚያቀጭጭ እንቅፋት ነፃ ሆነው አያውቁም፡፡ በአገራችን የአገር በቀል ዕውቀቶች እንቅፋቶች ሲተካኩ የነበሩት ሥርዓተ መንግሥታትና በቅርቡ ብቅ ብቅ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ተገቢውን ዕውቅና አለመስጠት፣ ማጣጣልና ማራከስ፣ ማደብዘዝ፣ ታሪክ ጠልነት፣ የቱባ ባህል ሽሚያ፣ ጭፍን ጥላቻ የመሳሰሉት ችግሮች ከገዥ መደብ የሚመነጩ የተቋማዊ ማኅበረሰብ ዕውቀት፣ ህልውናና ዕድገት እንቅፋቶች ወይም ፀሮች ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜ የዚህ ችግር መገለጫ ብቻ ብንመለከት የሥርዓቱ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ይሉት ከነበረው በጥቂቱ፣ «ወሎ ንግርቱን ይጠብቅ»፣ «የአማራ ተረት»፣ «የአማራ ትምክህት»፣ ወዘተ የዚህ ተቋማዊ ዕውቀት ባለቤት የሆነውን ማኅበረሰብ ዝቅ ለማድረግና ከሌላው ጋር ለማቆራረጥ የገዥ መደቡ የተጠቀመበትን የአገዛዝ ሥልት ያሳያል፡፡
በጠበብት የሚያዝ የማኅበረሰብ ዕውቀት እንዲሁ ከመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቃት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ ቀደም ባለው ዘመን የከበርቴው ሥርዓት ዕውቀት ጠል ስለነበረ የልዩ ሙያ ባለቤት የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የከፈሉት ዋጋ ቀላል አልነበረም፡፡ ሸማ ሠሪውን «ቁጢት በጣሽ»፣ ነጋዴውን «መጫኛ ነካሽ»፣ አንጥረኛውን «ቀጥቃጭ»፣ የቆዳ ባለሙያውን «ፋቂ»፣ ወዘተ በማለት ሙያቸውን ዝቅ በማድረግ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት እንዲሁ ዝቅ እንዲል ሲደረግ መኖሩ ይታወሳል፡፡ የገዥ መደቦች ዓላማ ማንኛውንም ድንጋይ በመፈንቀል ለቡድን ጥቅም የሚውል ጥሪት ማከማቻ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ በመሆኑ የአገር በቀል ዕውቀት አጀንዳቸው ሆኖ አያውቅም፡፡ በአፍ ከሚወተውቱ በስተቀር መቼም ቢሆን ለአገር በቀል ዕውቀት መቀጠልና መዋቅራዊ ዕድገት ማግኘት አይጨነቁም፡፡ በአገራችን የጠበብት አገር በቀል ዕውቀት በቅድሚያ ለባህል ብረዛ (Acculturation) እና ለቴክኖሎጂ ተፅዕኖ (Technology Pressure) ተጋላጭነት ከተዳረገ በኋላ ቀስ በቀስ እየደበዘዘና እየጠፋ ይሄዳል፡፡ የገዥ መደብ የሚመለከተው የአጭር ጊዜ የቡድኑን ስትራቴጅካዊ ጥቅም እንጂ የረዥሙን ጊዜ የአገር ዕድገትና ክብር አይደለም፡፡
ይህን አባባል ለመደገፍ በአገራችን ከተከሰቱ ችግሮች መካከል በአስረጂነት አንድ አንድ እየመረጡ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከቻይና ጋር የተፈጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ብንመለከት ከላይ ለተጠቀሰው አባባል ድጋፍ የሚሆን ጉልህ ማስረጃ እናገኛለን፡፡ ቻይና በአገራችን የመንገድ ሥራና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተቋራጭ በመሆን የአገሯን ዜጎች ባህላዊ ልብሳቸውን አልብሳ ስታሰማራ የአገራችን ወጣቶች የባህል ልብሳቸውን አውልቀው በመጣል ከመቀመጫ አካላቸው በታች ቻይና ሠራሽ የተቀዳደደ አዲስ ሱሪ ገዝተው በማጥለቅ በመንገድ ላይ ሲንገላወዱ የአገር በቀል ዕውቀታችንን እያከሰመች መሆኗን፣ ከንግዱ ተጠቃሚ ያልሆነውን ሕዝባችንን እየጎዳች ስለመሆኑ፣ ሴቶቻችንን ቻይና ሠራሽ ጥበብ ቀሚስና ነጠላ እንዲለብሱ በማድረግ በዚህ ረቂቅ ተፅዕኖ የተነሳ የአገራችን የጥበብ ሥራ አገር በቀል ዕውቀት ቀስ በቀስ ተዳክሞ በዘርፉ የተሰማሩ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ምርት ገዥ አጥቶ ሥራ አጥ እንዲሆኑ፣ ሙያውም እንዲረሳ እያደረግን መሆኑን ቁብ ሳንል የቻይና ቅርብ ወዳጅ መሆናችንን ለመመስከር የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመስጠት ስንጣደፍ እንታያለን፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ለግዕዝ ቋንቋና ለቻይና ቋንቋ የተሰጠውን ክብደት በንፅፅር ማየት ይቻላል፡፡
የገዥ መደብ የአገር በቀል ዕውቀት እንቅፋትነትን የሚያስረዱ በርካታ መገለጫዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ «አራቢነት ወይም ፋቂነት» በአገራችን በበርካታ ማኅበረሰቦች መሠረት ያለው በጠበብት የተያዘ ቆዳና ሌጦ የሚጠቀም የአገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡ የገዥ መደቡ ቆዳና ሌጦ ከማኅበረሰቡ ገበያ ተሻምቶ ዘላቂነት በሌለው ጥገኛ የንግድና ኢንዱስትሪ መዋቅር ውስጥ በማስገባት የግል ወይም የቡድን ጥቅም ለማፍራት ከሚደረግ እንቅስቃሴ በስተቀር ለጥሬ ሀብቱ መታወቂያ ለሆነው የአገር በቀል ዕውቀት ዕድገት፣ እንዲሁም ለጥሬ ሀብቱ በዘላቂነት ጥቅም ላይ መዋል የሚደረግ ጥረት አይታይም፡፡ ቀደም ሲል አገራችን ኢትዮጵያ አባቶቻችን በገነቡት የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም አገር በቀል ዕውቀት ወይም ሥርዓት የተነሳ የከፍተኛ የቀንድ ከብት ባለቤት ለመሆን በመቻሏ ለአፍሪካ አኅጉር የእንስሳት ሀብት ክምችት የመጠሪያ ስም እንዳልሆነች ሁሉ ዛሬ ያንን የአገር በቀል ዕውቀት ማስቀጠል ባለመቻላችን በአባቶቻችን ወቅት የነበረውን የቀንድ ከብት አኃዝ (ስታትስቲክስ) የከፍታ ጣራ ስንጠራ አናፍርም፡፡ አባቶቻችን የቀንድ ከብት ሀብት ክምችታችን በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ባህላዊ የአሠራር ሥርዓት ነበራቸው፡፡ ሴት ከብት (ካልመሰነች ላም በስተቀር)፣ ጥጆች፣ ወይፈንና ጊደር ለገበያ እንዳይቀርብ የሚያግድ አገር በቀል የከብት ሀብት አጠቃቀምና ልማት ሥርዓት ነበረን፡፡ ዛሬ «የቆዳ ቴክኖሎጂ የላቀ ከፍታ አገኘ» በተባለበት አገር የከብት ቆዳ ዋጋ አጥቶ በከንቱ ተጥሎ ወድቆ የሚቀርበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የአገር በቀል ዕውቀት የሆነውን «ፋቂነት» አጎልብቶ በማስቀጠል የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀማችንን ማሳደግ ሲገባን የጥገኛ ኢንዱስትሪው ድቀት ሰለባ በመሆን የተፈጥሮ ሀብታችንም፣ ተዛማጅ የአገር በቀል ዕውቀቱም ሁለቱም ተያይዘው እንዲጠፉ አደረግን፡፡ ዛሬ በአገራችን ሆኖ በማይታወቅ ደረጃ ለጉዳይ ማውጫ በየመንደሩ የቀንድ ከብቶች ሲታረዱ ጎን ለጎን ቆዳው የሚቀበርበት ጉድጓድ ይቆፈራል፡፡ ስንቱ ኢትዮጵያዊ ይህንን ችግር ያውቅ ይሆን?
ዘመን ተሻጋሪ ኢፍትሐዊ የመንግሥት አስተዳደር፣ የጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ከበርቴዎች የሆኑ የአዕምሮ ደሃ ፖለቲከኞች፣ የተዛባ ትርክት አቀንቃኝ ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ አክቲቪስት ነን ባዮች የተቋማዊ አገር በቀል ዕውቀት እንቅፋቶች ናቸው፡፡ ተቋማቱን በማፍረስ/በማዳከም ወይም ቀስ በቀስ በማደብዘዝ አገር በቀል ዕውቀቶችንና በዕውቀቱ አማካይነት የተገነባውን የማኅበረሰቡን ትስስርና አንድነት ይፍቃሉ፡፡ በጠበብት የተያዙ አገር በቀል ዕውቀቶችም ከፈተናው አላመለጡም፡፡ በአገራችን የተለየ ዕውቀት ወይም አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸው ዜጎች ለገዥ መደቦች ህልውና መቀጠል በከንቱ ፍዳ ሲሆኑ ኖረዋል ወይም ያለ ፍላጎታቸው የገዥ መደብ አገልጋይ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ የገዥ መደቡ አባላት ግብረ በላዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን የተሻሉ ሰዎች በማኮላሸት፣ በማግለልና በመግደል፣ እንዲሁም የዕውቀቱን ባለቤቶች ከውጤቱ ተጠቃሚ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር አጋጭቶ ሰላም በማናጋትና ዕውቀቱን በማቀጨጭ እንዳይጎለብት ብሎም ወደ አገራዊ ኢንዱስትሪ ዕድገት እንዳይሸጋገር ማድረግን የህልውናቸው መሠረት አድርገው ይመለከታሉ፡፡
የአገር በቀል ዕውቀትን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ማሳለጫ አማራጭ ሥልት አድርጎ ለመጠቀም ከዚህ ቀደም በአገራችን ሥር ሰድደው የቆዩ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ካዘጋጀው የኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀት ዳሰሳ ዓውደ ጥናት የሚጠበቀውም ውጤት ይኼ መሆን አለበት፡፡ በዓውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ አካላት ሁሉ የዓውደ ጥናቱን ተሞክሮ በየፊናቸው ለማባዛት ለሚያደርጉት ጥረት ሊጠይቁት ይገባ የነበሩ ሁለት ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ጥያቄ ከዓውደ ጥናቱ ዓላማ ጋር የሚሳለጠው የአገር በቀል ዕውቀት የትኛው ምድብ ዕውቀት ነው? ማለትም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ ለባህል ግንባታና ልማትን ለማፋጠን በማዋል የምናጎለብተው የአገር በቀል ዕውቀት የቱ የቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ የትኛው ምድብ የአገር በቀል ዕውቀት የትኛውን የወቅቱ የአገራችን ችግር ለመፍታት ይውላል?
ሰላምን ማረጋገጥ በተመለከተ አገራችንን የገጠማት የወቅቱ የሰላም ዕጦት ፈተና መንስዔው አንድና አንድ ነው፡፡ በአገራችን ዳብሮ የቆየውን የአብሮ መኖር እሴት ሆን ብሎ በማዳከም ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ላይ የተመሠረተ የኑሮ ሥልት የሚከተል አካል የፈጠረው ችግር በመሆኑ «አውቆ የተኛ ሰው ቢቀሰቅሱት አይሰማም» እንዲሉ ችግሩ ከአባቶች በወረስነው አገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓት ሊፈታ አይችልም፡፡ የሰላም መደፍረስ መንስዔ የሆነው ችግር መነሻው ተፈጥሯዊ ያልሆነ የጠባብ ቡድናዊነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር ስለሆነ መፍትሔው በግልጽ የሚታወቅ አንድና አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ይኼውም የግትር ኪራይ ሰብሳቢ የመንደር ፖለቲከኞችንና የፖለቲካ አክቲቪስቶችን የመሽከርከሪያ ጎማ ማስተንፈስ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሔ ዕውን መሆን ሁሉም ዜጋ በተለይም አገሩን የሚወድ ወጣት ትውልድ በችግሩ ዙሪያ አንድ የጋራ አስተሳሰብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የአገር በቀል ዕውቀትና ሥርዓታችን ሁሉ በኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲከኞችና ድጋፍ ሰጪ አክቲቪስቶች ልክፍት የተለከፈ መሆኑን ተረድቶ አገሩን ከጥፋት ለማዳን ዳር እስከ ዳር መነሳት ይኖርበታል፡፡
ዴሞክራሲንና ልማትን በተመለከተ ተቋማዊ የአገር በቀል ዕውቀቶችን በዝርዝር ለይቶ በማወቅ እንገነባለን የምንለውን የዴሞክራሲ ባህል፣ እናፋጥናለን የምንለውን የአገር ልማት፣ በአገር በቀል ሥርዓቶቻችን ላይ በመመሥረት ማጎልበት፣ የዘመናዊ ዕውቀትን ለአገር በቀል ዕውቀት ማበልፀጊያነት መጠቀም፣ ሁለቱንም አመጣጥኖ መጓዝ ይገባል፡፡ የሕዝቡ አንድነትና አብሮነት የተገነባባቸውን እሴቶች ትክክለኛ መሠረት ምን እንደነበር በመገንዘብ ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት ለሚፈጠሩ ግጭቶች ማስወገጃ መጠቀም፣ ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ሰው ሠራሽ ችግሮችንም በሰው ሠራሽ መንገድ ፈጣን መፍትሔ እየሰጡ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡
ተቋማዊ የማኅበረሰብ ዕውቀትን ወደ ዘመናዊ ትምህርት በቀላሉ ከማሸጋገር አንፃር የአብነትና መድረሳ ትምህርት ቤቶች የሕፃናት ትምህርት አማራጭ መነሻ ተቋማት ተደርገው ቢደራጁ ችግራችንን እያረምን ለመሄድ ይጠቅመናል፡፡ በመሆኑም ለአብነትና መድረሳ ትምህርት ቤቶች ማበብ ተገቢውን የፖሊሲ ድጋፍ መስጠት የተሰበረውን የአገር በቀል ዕውቀት ማሸጋገሪያ ድልድይ ለመጠገን ያስችላል፡፡ የቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ልማት መሠረት የሆነውን በጠበብት የተያዘ የአገር በቀል ዕውቀት ወደ ዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ የማስገባት ኃላፊነት ወደ ጎን የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚሁ ተፈጻሚነት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የትምህርት ተቋማት በፖሊሲ የተደገፈ የአገር በቀል ዕውቀት ልማት ስትራቴጂክስ ዕቅድ በማዘጋጀትና በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት በአገራችን ላይ የሚካሄደውን ልማት ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር) በማጠቃለያ የቡድን ውይይቱ ላይ ያስተላለፉት መልዕክትም ያስገነዘበው ይህንኑ ምክረ ሐሳብ ነው፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ዓውደ ጥናቱን ሲያዘጋጅ ያለው እሳቤ ከዚህ ፍሬ ላይ ለመድረስ እንጂ፣ ዓውደ ጥናቱ በአፈራ ዋርካ ሥር የተበላ የጨረባ ተስካር ሆኖ እንዲቀር በማሰብ አይደለም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡