በቅድመ ሰው መገኛ ኢትዮጵያ የሚገኙትን መንፈሳዊና ቁሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ፣ ተፈጥሮዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶች ለመጠበቅ የሚያስችል ዓላማን የሰነቀ “ሂውማን ኦሪጂን ሙዚየም ፋውንዴሽን” [የጥንተ ሰብ ሙዚየም ፋውንዴሽን] አዲስ አበባ ውስጥ ተመሠረተ፡፡
አራት መሥራች አባላቱን እና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ 13 የቦርድ አባላትን ይዞ የተመሠረተው ፋውንዴሽኑ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ በሙዚየም ግንባታና ቅርሶችን በማደራጀት፣ የዕውቀትና የቴክኒክ የፋይናንስ ድጋፍም በማሰባሰብ ሥራውን ያከናውናል ተብሏል።
ከሲሺል ማኅበራት ኤጀንሲ ፈቃድና እውቅና ያገኘው ፋውንዴሽን የበላይ ጠባቂ ሆነው የተሰየሙት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡
*********
“የሕይወት መንገድ”
በማኅበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የሕይወት መንገድ” የወግና የግጥም መጽሐፍ መሰንበቻውን ለንባብ አደባባይ ላይ ውሏል፡፡ በብርሃኑ ደጀኔ የተዘጋጀው መጽሐፍ በመጀመርያ ክፍሉ ወጎችን ሲይዝ በክፍል ሁለት 31 ግጥሞችን አካቷል፡፡ በብር 89.90 ይገበያል፡፡