Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየእሸት በዓል ከደቡብ እስከ ሰሜን

የእሸት በዓል ከደቡብ እስከ ሰሜን

ቀን:

አዲሱ ዓመት ከገባ ዛሬ ላይ 53ኛ ቀን ላይ እንገኛለን፡፡ ከክረምት ወደ መፀው ከተሸጋገርን አራት ሳምንታት አልፈዋል፡፡ አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣ እንቡጥና ፍሬ ማሳየት እንደሆነም ይነገራል፡፡ “እህልን በጥቅምት ልጅን በጡት” የሚለው ብሂል በወርኃ ጥቅምት አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው የሚነሱበት የሚበቅሉበት፣ የሚለመልሙበት ብሎም የሚሰበሰቡበት ነው፡፡  እንደ ስሙ የጥቅም መጀመርያ በሆነው ጥቅምት ወር በተለያዩ አካባቢዎች በደቡብም ሆነ በሰሜን እሸቱ ሲሰሰሰብና ሲቀመስ ኅብረተሰቡ እንደየባህሉ ሥርዓታዊ ከበራ አለው፡፡

እዚህ ላይ ከደቡብ የጎፋ፣ የቤንችና የሸኮ ከሰሜን የወሎን ትውፊት ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነውን አቅርበነዋል፡፡

ጎፋ

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ሰነዱ ላይ እንደተጻፈው፣ የጎፋ ብሔረሰብ ቀደም ሲል የደረሰ እሸት የመቅመስ ሥርዓት አለው፡፡ እሸት ለመቅመስ በቅድሚያ ቡና ይፈላል፣ ቀጥሎም በቆሎው ይጠበስና ለአባወራው ይሰጠዋል፡፡ ከተሰጠው በቆሎ የተወሰነ ፈልፍሎ ከረጨ በኋላ አንድ አንድ ፍሬ ለሚስቱና ለልጆቹ ያቀምሳቸዋል፡፡ እማወራዋም ‹‹እንኳን አደረሰን›› በማለት መሬቱን ትስማለች፡፡ ቀጥሎ ቡናውን ጠጥተው የእሸት መቅመሱ ሥርዓት ይጠናቀቃል፡፡ ከዛ በኋላ እሸት እየተቆረጠ በማንኛውም ጊዜ ይበላል፡፡ የክርስትናን እምነት የተቀበሉት የብሔረሰቡ አባላት እሸቱ እንደደረሰ ቆርጠው ባሉበት አጥቢያ ለሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡ ከዛ በኋላ እሸቱን መብላት ይጀምራሉ፣ በመቀጠል በቆሎው እንደተሰበሰበ በአስራት መልክ ለቤተክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡

ቤንች

የቤንች ብሔረሰብ አባላት የእሸት ወራትን ጠብቀው ምርት ከሰበሰቡ በኋላ በአዛውንቶች ወይም ቃልቻ ቤት በመሰብሰብ የሚያቀርቡት የምስጋና ወይም የምርቃት በዓል ጨባል ይባላል፡፡ ከምስጋና ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ባስና ናይኬስ የሚባሉ የክራር (ሸንጎ) ጨዋታዎችን በቀን ያከናውናሉ፡፡ በምሽት በቶሪ፣ ቶህ፣ ዛክ፣ ፍረግን በሚባሉ የድምፅና የትንፋሽ መሣሪያዎች በመታጀብ ናሪ፣ ኪያርኪያም፣ ባባ፣ ኖጲ የተባሉ ዘፈኖችን (ጨዋታዎችን) ሴቶችም ወንዶችም በአንድነት ይጫወታሉ፡፡

ሸኮ

የሸኮ ብሔረሰብ የትከሻ በዓል አዝመራ ሲደርስ ምርቱ ከአውሬና ካልታሰበ ዝናብ ተጠብቆ በሰላም እንዲገባ ለመጸለይ የሚከናወን ባህላዊ የእምነት በዓል ነው፡፡ በባህሉ የበቆሎና የማሽላ እሸት ሲደርስ ወዲያውኑ አይመገቡም፤ ከደረሰው የሰብል ዓይነት ተቆርጦ ምግብ ተዘጋጅቶና ቦርዬ ተጠምቆ በየአካባቢው ባሉ የጎሳ መሪዎች ጋር ሕዝቡ ይሰበሰባል፡፡ ሁሉም በቤቱ ያዘጋጀውን ምግብና ቦርዴ ለበዓሉ ካቀረበ በኋላ በየአካባቢው የጎሳ መሪ በዓሉን ባርኮ ምግቡ እንዲቀመስ የአካባቢውን የሃይማኖት መሪ (ቡርዣብን) ያዛል፡፡ ቡርዣቡ ‹‹አምላክ ነፋሱን ጠብቅ፣ አውሬውን ጠብቅ በሽታ ወደኛ አይምጣ ሩቅ አገር ይሄድ›› በማለት የመጀመርውን ቦርዴ ከቀመሰ በኋላ ጥቂት ወደ መሬት ያፈሳል፤ ከዚህ በኋላ እንደየማኅበራዊ ደረጃው መጀመርያ የጎሳ መሪው በመቀጠል የአገር ሽማግሌዎችና ጎልማሳዎች ከቀመሱ በኋላ ወጣቶች ቀምሰው በይፋ የምግብ የመጠጡ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ እስከ አራት ቀን ድረስ ባህላዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ያሳልፋሉ፡፡ ይህ በዓል በአሁኑ ጊዜ በተለያየ የሃይማኖት ተፅዕኖ ምክንያት የሚከናወነው አልፎ አልፎ ባሉት ገጠራማ የሸኮ ቦታዎች ነው፡፡

የትከሻ በዓል ከመከበሩ ቀደም ብሎ በብሔረሰቡ የተጣላ ይታረቃል አለመግባባቶች በሽማግሌዎች አማካይነት ስለሚወገዱ በዓሉ ሰላም ያሰፍናል፡፡ ከባህላዊ እምነቱ አኳያ በዓሉን ካከበሩና ከተመራረቁ ሰብል በሰላም ያሰባስባል፤ በሽታም አይመጣም ተብሎ ይታመናል፡፡

ወሎ

ለዚህ የእሸት ወቅት ያደረስከን ተመስገን! አዝመራውን ለጎተራ አብቃልን! ከርሞም ከዚህ የተሻለ አዝመራ ስጠን!” ተብሎ የሚመረቀው፣ ጸሎትም የሚካሄደው በደቡብ ወሎ ነው::

የእሸት በዓሉ ባዲገዝ ተብሎ ይታወቃል፡፡ የአብመድ ባልደረባው መሠረት አስማረ እንደጻፈው፣ ባዲገዝ ማለትባዕድ ይገዝ [ያግዝ]፤ ዘመድ ያልሆነም ይርዳማለት ሲሆን በዓሉ በተሁለደሬ፣ ወረባቦ፣ ቃሉ፣አካባቢ የሚከበር ነው::

“የአካባቢው አዝመራ ተሰብስቦ ሰውም ከየአካባቢው መጥቶ አንድ ቦታ ላይ በመገናኘት በጋራ የሚበሉበት ባህል ነው፤ በዓሉ ለሳምንት የሚከበር ሲሆን እሸት ያለው እሸት፣ ወተት ያለው ወተት፣ ጥንቅሽ ያለው ጥንቅሽ፣ እንጀራ፣ ቂጣእያመጣ የሚሰባሰቡበት በዓል ነው::”

ሌላኛ ስያሜውዲልበትይባላል:: አዝመራው ቃሪያ፣ ጥንቅሽ፣ በቆሎ፣ሊሆን ይችላል:: ባዲገዝ ማሳ የሌላቸውና ያላረሱ ሰዎች ሁሉ እሸት የሚቀምሱበት፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘንና የመዋደድ በዓል ነው:: ከየማሳው ያለው የእሸት ዓይነት ሁሉ ቀርቦ እየተበላ እስከ ምሽት ድረስ ጨዋታና ምርቃቱ ይቀጥላል፡፡

አዛውንቶች ስለአካባቢውና ስለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለባህልና መረዳዳት፣ ፖለቲካና የሕዝብ አስተዳደር በእሸት በዓላቸው ባዲገዝ ላይ ያስተምሩበታል የሚለው መጣጥፉ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙት የአካባቢው ሽማግሌዎችተላይ አልጋውን ከታች ለጋውን  ጠብቅልን! አዝመራውን አብዛልን!” እያሉ በዝማሬ ጭምር ይጸልያሉ፤አልጋየሚሉት መንግሥትን ሲሆን፣ለጋየሚሉት ደግሞ ሕዝቡን ነው::

ይኸው ዓመታዊው የባዲገዝ በዓል መሰንበቻውን በኮምቦልቻ ከተማ እየተከበረ መሆኑን አብመድ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው የእሸት በዓል (ባዲገዝ) 1979 .ም. ጀምሮ በተጠናከረ መልኩ መከበር እንደጀመረ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ በበዓሉ የአካባቢ ነዋሪዎች መሬት ያበቀላቻቸውን የእህል ዘሮች ሁሉ እሸት ይዘው በአንድ ቦታ በመቅረብ በጋራ ይበላሉ፤ የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችም የበዓሉ አካል ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...