የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ለደንበኞቹ የሚሰጣቸው ሰነዶች በሐሰተኛ መንገድ እንዳይባዙ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን ለሪፖተር ገለጸ፡፡
ኤጀንሲው ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የሚሄዱለትን ሰነዶች ትክክለኛነት ከማረጋገጥና ከመመዝገብ ባሻገር የተለያዩ ሰነዶችን እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡
ከሚሰጣቸው ማስረጃዎች መካከል የውክልና፣ የሽያጭ፣ የስጦታና የኑዛዜ ሰነዶች ተጠቃሽ እንደሆኑ የሚናገሩት የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ረዳት ኃላፊ አቶ ዓለምእሸት መሸሻ ናቸው፡፡
የሐሰተኛ ማስረጃዎች ዝውውር ለወንጀል መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዓለምእሸት፣ ኤጀንሲው የሚሰጣቸው ማስረጃዎች በሕገወጥ መንገድ እንዳይባዙ ‹ትሮይ ሴኪዩሪቲ ሶሎውሽን› ከተባለ የአሜሪካ ድርጅት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የማስረጃዎች ተመሳሳይ ቅጂ ፈፅሞ መባዛት እንዳይችል የሚያደርግ ቴክኖሎጂ አለው የተባለው ድርጅቱ በኢትዮጵያ አጋር እንዳለው ታውቋል፡፡
ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ከ60 የበለጡ ሐሰተኛ ሰነዶችን መያዙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህኛው ሩብ ዓመት ውስጥም ስምንት ሐሰተኛ መታወቂያና አራት ያላገባ ማስረጃ ያቀረቡ ሕገወጦችን እንደደረሰባቸው ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሐሰተኛ መታወቂያ ያቀረቡ ሕገወጦች በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የኤጀንሲው ቅርንጫፎች የተያዙ መሆናቸውን፣ ሲነቃባቸውም መጥፋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ሐሰተኛ ያላገባ ማስረጃ ያቀረቡ ግለሰቦች ጉዳይም በሕግ እየታየ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳያቸው በሕግ እየታየላቸው ካሉ ሦስት ግለሰቦች መካከል ሁለቱ መኪና ለመሸጥ አላገባንም የሚል ሐሰተኛ ማስረጃ ያቀረቡና አንዱ ደግሞ ከኤጀንሲው ውክልና እንደተሰጠው አስመስሎ ሐሰተኛ መረጃ ለባንክ በማቅረቡ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ኤጀንሲው የሐሰተኛ ማስረጃዎችን ዝውውር ለመቆጣጠር ዲጂታል መታወቂያዎች በፍጥነት በሥራ ላይ መዋል አለባቸው ብሏል፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኤጀንሲው የተላኩ ማስረጃዎች ወደ መረጃ ቋቱ እንዲገቡ መደረጋቸውን፣ ይህም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው ባለፉት ሦስት ወራት 237,986 ጉዳዮችን እንዳስተናገደ ሪፖርት አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥም 155 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር 62.3 ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱንና 386,094 ዜጎችን ማገልገሉን አስታውቋል፡፡