Tuesday, July 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ የተሰማራው የፈረንሣይ ብቅል አምራች ኩባንያ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ተፈቀደለት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩባንያው የ50 ሚሊዮን ዶላር ፋብሪካ እንደሚገነባ ይጠበቃል

የዓለም ባንክ ግሩፕ አካል የሆነው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) በኢትዮጵያ 110 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብቅል በዓመት እንደሚያመርት ለሚጠበቀው ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ፣ የ20 ሚሊዮን ዩሮ ብድር መፍቀዱን አስታወቀ፡፡

አይኤፍሲ ይፋ እንዳደረገው ሱፍሌ የሚያገኘው ብድር የዓለም የግብርናና የምግብ ዋስትና የተሰኘው ሌላኛው የዓለም ባንክ ተቋምና አይኤፍሲ፣ እያንዳንዳቸው አሥር ሚሊዮን ዩሮ በማዋጣት እንደሚያበድሩት ይጠበቃል፡፡

ምንም እንኳ ሱፍሌ ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የራሱን የብቅል ፋብሪካ ገንብቶ በዚህ ዓመት ሥራ እንደሚያስጀምር ቢጠበቅም፣ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ የቻለው ግን ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ነበር፡፡ የሱፍሌ መምጣት የብቅል አቅርቦትን በማሻሻል የቢራ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በተመረተ ብቅል እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ምንም እንኳ አንጋፋውን አሰላ ብቅል ፋብሪካን ጨምሮ በጎንደርና በደብረ ብርሃን አዳዲስ የብቅል ፋብሪካዎች ቢገነቡም፣ በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የቢራ ፋሪካዎች የሚጠቀሙበት ብቅል ከውጭ እንደሚመጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሱፍሌ ከ40 ሺሕ አነስተኛ ገበሬዎች ለብቅል የሚያውለውን ገብስ በመረከብ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን በማስመልከት ባለፈው ዓመት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት በፈጸመበት ወቅት ለመነሻ ያህል በዓመት 60 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብቅል በማምረት እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር፡፡ ለዚህም እስከ 25 ሺሕ አነስተኛ ገበሬዎች እንደሚያስፈልጉትም ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ሆኖም የፕሮጀክቱን አካሄድ ካጓተቱት ምክንያቶች አንዱ ለግንባታ የሚሆነውን መሬት በቶሎ ለማግኘት አለመቻሉ እንደነበር የሱፍሌ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ክሩስቶፍ ፓሲፓንዴ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አምና ይፋ በተደረገው መሠረት ኩባንያው 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ሱፍሌ በ22 አገሮች ውስጥ 27 የብቅል ማምረቻዎችን ጨምሮ የሩዝ፣ የስንዴና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪዎችን የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ የቤተሰብ ኩባንያ ነው፡፡ በአውሮፓ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሰፊው ይንቀሳቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገነባው ፋብሪካም ከሰሃራ በታች አፍሪካ የመጀመርያው እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባሻገር አሰላ ብቅል ፋብሪካ ከ20 ሺሕ አነስተኛ አምራቾች ለብቅል ማምረቻ ገብስ ይረከባል፡፡ እንደ ዲያጆና ሃይኒከን ያሉ ቢራ አምራቾችም ከገበሬዎች የቢራ ገብስ በመግዛት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ካቻምና ቡርማልት የተሰኘው የቤልጂየም ኩባንያ ከደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ 15 ሔክታር መሬት በመረከብ፣ በ60 ሚሊዮን ዶላር የብቅል ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ ስምምነት መፈጸሙን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ሰፊ የገበያ ድርሻ ባለው በቢራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ግብዓቶችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ከማድረግ በተጨማሪ ከ2,000 በላይ ኩባንያዎችንም በፋይናንስ በማገዝ ላይ የሚገኘው አይኤፍሲ፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ብቻ ከ19 ቢሊዮን ዶላር በላይ የረጅም ጊዜ ብድር በታዳጊ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ የግል ኩባንያዎች ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያም በማማከርና ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ላይ የሚገኘው አይኤፍሲ፣ ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ አጋርነት የማማከር ሥራ 40 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን፣ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላርም ለሌሎች ፕሮጀክቶች መመደቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች