Thursday, June 13, 2024

ኢትዮጵያ በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች አትታመስ!

ኢትዮጵያን ሁሌም ጭንቅ ውስጥ የሚከቷት፣ የንፁኃን ልጆቿን ሕይወት የሚያስገብሯትና ህልውናዋን የሚፈታተኑት አንዳችም ፋይዳ የሌላቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጣር የሚያበዙትና የሕዝቡን ተስፋ የሚያደበዝዙት፣ ለአገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ራስ ወዳዶች መሆናቸውም የታወቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘመናት ከተዘፈቀበት ድህነት ውስጥ ለማውጣት አቅሙም ሆነ ችሎታው የሌላቸው፣ ነገር ግን ሰቆቃውን ለማባባስና የሚወዳትን አገሩን ለማጎሳቆል የማይሰንፉ ከንቱዎች በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች አገር ያምሳሉ፡፡ ለእነሱ ሥልጣን፣ ጥቅም፣ ክብርና ዝና እስከተመቸ ድረስ ሰላም ይሰፍናል፡፡ እነሱ ትንሽ ሲነኩ ግን አገር የጦር ቀጣና ትሆናለች፡፡ የየዕለቱ አጀንዳቸው የሚቃኘው ከአገርና ከሕዝብ ፍላጎት አንፃር ሳይሆን፣ ከጠባብ ግላዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅም አኳያ ነው፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት የሚደረገው ትግል እየተቀለበሰና የመላው ሕዝብ የጋራ ፍላጎት ወደ ጎን እየተባለ፣ ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማ ጉልበተኞች በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች አገር ያምሳሉ፡፡ የእነሱን የዕብደት ፍላጎት ለማስፈጸም ሲባልም ንፁኃን በከንቱ ሕይወታቸውን ይገብራሉ፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ እየሆነ ያለው አሳዛኝ እውነት ይኸው ነው፡፡

ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታግለናል ሲሉ የነበሩ ስመ ነፃ አውጪዎች በሕዝብ ስም ምን ያህል እንደነገዱ ይታወቃል፡፡ ዴሞክራት ነን እያሉ ሲመፃደቁ የነበሩ በአምባገነንነት ያደረሱት በደል አይረሳም፡፡ ፍትሕ እናሰፍናለን ብለው ያጭበረበሩ አገሪቱን እስር ቤት ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ለሕዝብ ብልፅግና ለማምጣት በማለት ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን አበልፅገው አገር ያደኸዩም ይታወቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ ከራስ በፊት አገር ትቅደም ማለት ስላልተፈለገ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር እዚህ የደረሰውን ኢትዮጵያዊነት በመናድና ሕዝቡን በመከፋፈል የተሠራው ኃጢያት ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በተለይ በብሔርና በሃይማኖት ለመከፋፈል የተሞከረው አሳዛኝ ድርጊት፣ አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በአዲሱ ትውልድ ላይ የተዘራው ክፉ መንፈስ አዳዲስ ተረኞችን እየፈጠረ ነው፡፡ እነዚህም ለአገር የማይጠቅሙ አጀንዳዎችን እየፈበረኩ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እየተገዳደሩ ነው፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትመች የጋራ የሆነች አገር ከመፍጠር ይልቅ፣ ፋይዳ ቢስ አጀንዳዎችን እየፈበረኩ አገርን ለማፍረስ የሚጣደፉ ጉልበተኞች ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ሥጋት ውስጥ ወድቋል፡፡

የአገር ጉዳይ ሲነሳ ሁሉንም ነገር ትናንት ተፈጽመዋል ከሚባሉ በጎና ክፉ ትርክቶች አኳያ በመተንተን ትንቅንቅ ከመፍጠር፣ ከእነዚህ ሁነቶች ምን መማር አለብን የሚለውን አለማስቀደም አላስፈላጊ መስዋዕትነቶች እያስከፈለ ነው፡፡ ወደኋላ በመሄድ ታሪክ መመርመር የግድ ቢሆንም፣ በሚገኙት ውጤቶች ላይ መግባባት አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ታሪክን መመርመር የሚቻለው በባለሙያዎች ዕገዛ ስለሆነና የዘመኑ ትውልድ ደግሞ በሚገኘው ጭብጥ ላይ በመመርኮዝ መልካሙን በመውሰድና ክፉውን ባለመድገም፣ የወደፊቱን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ መጣር አለበት፡፡ ትውልዱ በራሱ ዘመን የረባ ነገር ሳይሠራ በጥንቱ ድርጊት ላይ የሚተናነቅ ከሆነ፣ መጪው ትውልድ ከመታዘብ አልፎ የታሪክ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ዘመን ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በመባባልና ለዘመናት አብሮ የኖረው ሕዝባችንን ‹‹የጋራ ታሪክ የለውም›› በሚል አጉል ትርክት በመጨቃጨቅ፣ ለሕዝቡም ሆነ ለአገሪቱ ጠብ የሚል ነገር ማመንጨት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን በሚገባ ያደራጁ ኃይሎች የግልና የቡድን መጠቀሚያ በመሆን እርስ በርስ መጨፋጨፍ ነው የሚከተለው፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ለሥልጣንና ለጥቅም የሚንገበገቡ ኃይሎች ለአገር የሚጠቅም አንዳችም ተግባር ሳይሠሩ፣ በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች አገር የሚያተራምሱት እንዲህ ዓይነት ሞኝነት ስለበዛ ነው፡፡ እነሱ እንደሆነ አጀንዳ ተሸካሚ የዋሆችን ማብዛት እንጂ፣ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ እንዲኖር አይፈልጉም፡፡ ሞጋች ትውልድ እኮ ለጥፋት የሚሆን ድንጋይ የሚያነሳ ሳይሆን፣ የማያፈናፍን ሐሳብ ወይም ጥያቄ የሚያነሳ ነው፡፡ ይህ ግን እየሆነ አይደለም፡፡ አሁን በብዛት እየታያ ያለው በሐሳብ የሚሞግት ሳይሆን፣ የተነገረውን የሚፈጽም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች ምን ያህል ትውልዱን እየመረዙት እንደሆነ ማወቅ የሚቻለው፣ በማኅበራዊ የመገናኛ ትስስሮች ውስጥ የሚተላለፉ መልዕክቶችን በማየት ነው፡፡ ወጣቱን ትውልድ በትምህርትና በሥነ ምግባር ለማነፅ የሚተጋው የትኛው አክቲቪስት ነው? አለኝ ከሚለው ዕውቀቱ የሚያቋድሰው የትኛው ምሁር ነው? በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የንቃተ ህሊና ማጎልበቻ የሚሰጠው የትኛው ፖለቲከኛ ነው? ለሐሳብ የበላይነት ልዕልናና ለመብቶች መከበር በፅናት መቆምን የሚሰብከው የትኛው የመብት ተከራካሪ ነው? በአጠቃላይ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የመታገልን አስፈላጊነት የሚሰብከው የትኛው አንቂ ነው? በሚያሳዝን ሁኔታ በማኅበራዊ መገናኛ  ትስስሩም ሆነ በሌላው የመገኛኛ ዘዴ ከሚሳተፉት አብዛኞቹ ትውልድ ምረዛ ላይ ነው የተሰማሩት፡፡ ትውልዱን እንዳልተገራ ፈረስ በመጋለብ ያሻቸውን መፈጸም የሚፈልጉ በሙሉ ጥላቻ፣ ቂም፣ ጥርጣሬና አለመተማመን እየሰበኩ ወጣቱን አገር አጥፊ እያደረጉት ነው፡፡ አገሩን የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የነፃነትና የብልፅግና ምድር ማድረግ የሚችል ትውልድ በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች ሲጠለፍ ለምን ዝም ይባላል? ዝምታው እስከ መቼ ይቀጥላል? አገር ወደ ቀውስ እየተንደረደረች እንዴት ዳር ላይ መቆም ይቻላል?

ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ማውጣት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፏቸው ሲገደብ ኢትዮጵያ ትጎዳለች፡፡ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ እናት አገር ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ ጎራ ለይቶ በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ክፉ መነጋገርም ሆነ ግጭት ውስጥ መግባት ለማንም አይጠቅምም፡፡ የትናንቱን ለትናንት ትቶ የነገውን መልካም ጊዜ ለማምጣት በጋራ መነሳት የግድ ነው፡፡ በጥቂቶች ፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች ተጠልፎ እርስ በርስ መካሰስ፣ መጋጨት፣ መጋደልና የአገር ሀብት ማውደም ይዋል ይደር እንጂ ወደ ባሰ ቀውስ ነው የሚወስደው፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ራሳቸውን ላገዘፉ ጉልበተኞችም ሆነ መሰሪዎች ሲባል የሕዝብን ተስፋ ማምከን ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሩም፣ አገርን በጋራ ማሳደግ ግን የሁሉም አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ልዩነትን ይዞ ለአገር በአንድነት መቆም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ከራሳቸው ፍላጎት በፊት አገርን የማያስቀድሙ ወፈፌዎች ይህንን አንድነት አይፈልጉም፡፡ እነዚህን ወደ ጎን በማለት አገርን ማስቀደም የግድ ሊሆን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ምድር እንድትሆን በጋራ መሥራት የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ከወደቀችበት መነሳት ይኖርባታል፡፡ በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎች መታመስ የለባትም!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...