Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቢሮ ኪራይ ፈተና የሆነበት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ባለ21 ፎቅ ሕንፃ ሊያስገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤጀንሲው ለቢሮ ኪራይ በዓመት እስከ 37 ሚሊዮን ብር ይከፍላል

ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል ዘመናዊና ባለ21 ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጣ፡፡

ጨረታውን ይፋ ያደረገው በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሥር ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲያካሂድ የተቋቋመው የመንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ ሊገነባ የታሰበው ዘመናዊ ሕንፃም የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ያለበትን የቢሮዎች ኪራይ ወጪን የሚቀንስና በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ የተቀላጠፈና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ነው ተብሏል፡፡

የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ዓለምሸት መሸሻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ በአዲስ አበባ 14 ቅርንጫፎች እንዲሁም በድሬዳዋ አንድ ቅርንጫፍ አለው፡፡

ነገር ግን አብዛኞቹ ቅርንጫፎችን በኪራይ የሚጠቀምባቸው ሲሆኑ፣ በዓመት በድምሩ እስከ 37 ሚሊዮን ብር ይከፍልባቸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ለዋናው መሥሪያ ቤቱ ኪራይ ብቻ 11 ሚሊዮን ብር ይከፍላል፡፡

ምንም እንኳ ተቋሙ ለመንግሥት ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ ከሚያስገቡት ተቋማት መካከል በመጀመሪያው ረድፍ የሚመደብ ቢሆንም፣ የቢሮ የኪራይ ወጪ ለድርጅቱም ሆነ ለመንግሥት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን ግዙፍ ሕንፃ እንዲገነባ መወሰኑን ለሪፖርተር አቶ ዓለምሸት አስረድተዋል፡፡

ግዙፉ ሕንፃም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር በተገኘ 2,783 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ሜክሲኮ አካባቢ ከብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ አጠገብ እንደሚገነባ አቶ ዓለምሸት ገልጸዋል፡፡ ሕንፃውም በ1,900 ካሬ ሜትር ላይ ያርፋልም ብለዋል፡፡

ሕንፃውን ለመገንባት ፍላጎት ላላቸው ኮንትራክተሮች በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በኩል ዓለም አቀፍ ጨረታ በዚህ ሳምንት ክፍት ሆኗል፡፡ የሚገነባው ግዙፍ ሕንፃ ከመሬት በላይ ከሚኖሩት 21 ፎቆች በተጨማሪ ከመሬት በታች አራት ወለሎች (4B+G+21) እንደሆነ በሚኒስቴሩ የወጣው የጨረታ ሰነዱ ዝርዝር ማብራሪያ ያሳያል፡፡ ጨረታው ለ45 ቀናት እንደሚቆይም ከሰነዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዋናው መሥሪያ ቤት ግንባታ በተጨማሪ ሌላ መለስተኛ ሕንፃም ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንና በቅርቡም የመሬት ርክክብን ጨምሮ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እየሠሩ መሆኑን  አቶ ዓለምሸት ለሪፖርተር ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሕንፃዎቹ መገንባት ተቋሙ ለኪራይ የሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ፣ ገንዘቡ ለተለያዩ የመንግሥትና የኅብረተሰቡ የልማት ሥራዎች ላይ ይውላል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በአገሪቱ የኪራይ ሕግን በተመለከተ ክፍተት በመኖሩና ወጥነት ያለው የአከራይ ተከራይ ደረጃ ባለመኖሩ፣ ከግለሰብ ባለሀብቶች ሕንፃ ተከራይቶ መሥራቱ በዋጋ አተማመንና የኪራይ ጭማሪ በሚኖርበት ወቅት ለተቋማቸው ችግር እየፈጠረ መምጣቱን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንሲው ከአገልግሎት ዘርፉ ለመንግሥት ከሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ በተጨማሪ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጠፍና በአንፃራዊነት የተሻለ ስም እንዳለው ይነገርለታል፡፡

ተቋሙ የድሬዳዋውን ጨምሮ በ15ቱም ቅርንጫፎች 750 የሚሆኑ ሠራተኞች ሲኖሩት፣ ከጠቅላላው ሠራተኞቹ መካከል 519 ወይም 68 ከመቶው የሚሆኑት ሴት ሠራተኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከጠቅላላው ሴት ሠራተኞች 56 ከመቶ የሚሆኑት በኃላፊነትና ውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ያሉ ናቸው ያሉት አቶ ዓለምሸት፣ በተነፃፃሪነት ተቋሙ በጾታ እኩልነት የተሻለና ለሴት ሠራተኞች አመቺ መሥሪያ ቤት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት ውስጥ ከሰጠው አገልግሎት መካከል 75 ከመቶ የሚሸፍነውን ማንኛውንም ውክልና፣ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ለሦስተኛ ወገን ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ውል በኦንላይን አገልግሎት መስጠት መጀመሩና የክፍያ ሥርዓቱን በማዘመን በፖስ ማሽንና በሲቢኢ ብር የክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱ ተጠቃሽ ክንውን ነው።

በዚህ መሠረት የውክልና፣ የኑዛዜ የማረጋገጫና የመሻሪያ ሰነዶችን የማረጋገጥ ሥራ የፊርማ ናሙና፣ የጥብቅና ፈቃድና የዕግድ ሰነዶች የመመዝገብና የማረጋገጥ፣ የማኅበራት ሰነዶችን የማረጋገጥ እንዲሁም የተረጋገጡ ሰነዶችን የመመዝገብ፣ የማደራጀትና የማጣራት ተግባራት ማከናወኑን ኤጀንሲው በሩብ ዓመቱ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ በዚሁ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት 223,392 ጉዳዮችን ለማስተናገድ በዕቅድ ተይዞ፣ 237,986 ጉዳዮች በማስተናገድ የዕቅዱን 106.5 ከመቶ ማከናወኑን ይፋ አድረጓል፡፡

እንዲሁም ኤጀንሲው ለሚሰጠው የተለያዩ አገልግሎቶች 111.7 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ፣ 155.7 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል፡፡ ይህም የዕቅዱ 139 በመቶ ተከናውኗል፡፡ የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ 62.3 ሚሊዮን  ብር ብልጫ ማሳየቱን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በተቋሙ በሩብ ዓመቱ በሁሉም ቅርንጫፍ ሕፈት ቤቶች   386,094 ተገልጋዮች አገልግሎት አግኝተዋል ተብሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች