Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከደርዘን በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በጀት ተከለከሉ

ከደርዘን በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በጀት ተከለከሉ

ቀን:

ከአትሌቲክስ ቀጥሎ ውጤታማ ስፖርቶች የውሳኔው አካል ተደርገዋል

ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የኦሊምፒክ ስፖርቶችን ጨምሮ 13 ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መንግሥት የሚያደርግላቸው የበጀት ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ውሳኔው በጥናት ላይ ያልተመሠረተ፣ ሕዝባዊ አካሉን ያላሳተፈ ከመሆኑ ባሻገር፣ የበጀት ክልከላው በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁ ስፖርቶችን አካቷል፡፡

ስፖርት ኮሚሽን በቀን 12/02/2012 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የበጀት ድጋፍ እንዲቋረጥባቸው የተደረጉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ዳርት ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ናቸው፡፡

ለበጀት ዕገዳው ምክንያት ተብሎ የቀረበው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ በስፖርት ዓይነቱ ተመዝግበው ከክልልና ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ አግኝተው የተቋቋሙ፣ ቢያንስ ከአምስት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፌዴሬሽኖች በአባልነት ሲኖሩና እያንዳንዳቸው በውድድር ያሉ አምስት ክለቦች መሆናቸው ሲረጋገጥ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ከተጠቀሱት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መካከል የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት፣ የኢትዮጵያ ቦክስ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽኖችና ሌሎችም፣ ስፖርቱን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የሚታይ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ከኃላፊዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ጳውሎስ ማባ ይጠቀሳሉ፡፡

ከደርዘን በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በጀት ተከለከሉ

እንደ ኃላፊው ከሆነ፣ ኮሚሽኑ እንደነዚህ የመሰሉ ውሳኔዎችን ከማሳለፉ አስቀድሞ፣ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ማወያየት ሲኖርበት ያንን አላደረገም፡፡ የኮሚሽኑ ውሳኔ  “የቦክሱን ጨምሮ ሌሎችም ብሔራዊ ተቋማት ምን እያደረጉ እንደሆነ በተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረተ አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ሲባል ደብዳቤው እንደደረሰን መጀመሪያ ያደረግነው የኮሚሽኑን ኃላፊዎች በጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጥያቄ ማቅረብ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን፣ የክለቦችን ቁጥርና የክልል ፌዴሬሽኖችን አወቃቀር ስንመለከት በሰባት ክልሎች በፌዴሬሽን ደረጃ ሲቋቋሙ፣ አራት ክልሎች ደግሞ በኮሚቴ ደረጃ ተዋቅረው የየክልሎቻቸውን ስፖርት እያስተዳደሩ ይገኛል፡፡ ክለቦች በሚመለከት ደግሞ በደቡብ ክልል አራት፣ በአማራ ክልል ሁለት፣ በአዲስ አበባ አምስት፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋና በጅግጅጋ አንድ አንድ ክለቦች አሉ፡፡ በዚህ አተያይ ኮሚሽኑ የትኛው ፌዴሬሽን በየትኛው ስፖርት ምን እያደረገ ነው? የሚለው በተጨባጭ የሚያውቀው አይመስለኝም፤” በማለት ነው የሚያስረዱት፡፡

ሌላው በዚሁ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ናቸው፡፡ ኃላፊው፣ “የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማሳደግ ምን እያደረገ ነው? ለሚለው በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቀጥሎ ወርልድ ቴኳንዶ ውጤታማ ለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህን ማወቅ የሚቻለው ግን ስፖርቱን ለሚከታተል አካል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ  የኮሚሽኑን ውሳኔ ሚዛን ላይ ሳስቀምጠው ጥያቄ ይጭርብኛል፤” ይላሉ፡፡

የተቋሙን ቀጣይ ውሳኔ በሚመለከት ኃላፊው፣ “በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈስባቸው ስፖርቶችን ጨምሮ ብዙዎቹ ከቶኪዮ 2020 ማጣሪያ ውጪ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ግን ለማጣሪያ የሚያደርገውን ዝግጅት የጀመረው ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡ ጥሩ የሚባል መነሳሳትም አለ፣ እንደ ሕዝባዊ ተቋም ስፖርቱን ለማሳደግ ጥረት በምናደርግበት በዚህ ወቅት ከመንግሥት የሚደረግላችሁ የበጀት ድጋፍ ተቋርጧል የሚል ነገር መስማት በግሌ እንደ ኃላፊ ይከብደኛል፡፡ ለማንኛውም የኮሚሽኑን ውሳኔ አስመልክቶ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና ውሳኔ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፤” ብለዋል፡፡

መንግሥት ለብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በዓመት የሚሰጣቸው የበጀት ድጋፍ ዝቅተኛው 80,000 ከፍተኛው ደግሞ 487,000 ብር እንደማይበልጥ የሚናገሩ አሉ፡፡ በኮሚሽኑ ውሳኔ የበጀት ድጋፍ ክልከላ ከተደረገባቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ውስጥ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ይጠቀሳል፡፡

ይህ ብሔራዊ ፌዴሬሽን በዋናነት በትግራይ፣ በአማራና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎችም ክልሎች ስፖርቱን ለማስፋፋት በከፍተኛ መነሳሳት ላይ እንደሚገኝና በተለይ የትግራይ ክልል ብስክሌት ፌዴሬሽን ከእግር ኳሱ ባልተናነሰ በጀት በጅቶ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካም አልፎ በአውሮፓ ደረጃ በሚታወቁ እንደ “ቱር ደ ፍራንስ” በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች በተሳትፎ ያስመሰከሩ ፅጋቡ ገብረማርያምና ሌሎችም አትሌቶችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የስፖርት ኮሚሽን ሙያተኞች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የትግራይ ክልል ብስክሌት ፌዴሬሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ብሔራዊ ተቋማቱ እንደ የስፖርቱ ዓይነትና ባህሪ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ አምስት አሠርታትና ከዚያም በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ መኖራቸውን የሚገልጹ የስፖርቱ ሙያተኞች በበኩላቸው፣ “ስፖርት ኮሚሽን በጀት ሰጪና ከልካይ ከመሆን ያለፈ ኃላፊነት ያለበት ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከሙያ ድጋፍ ጀምሮ ራሳቸውን ይችሉ ዘንድ ማገዝና ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ውሳኔዎችን ከማሳለፉ በፊት ከሕዝባዊ አካሉ ጋር ቁጭ ብሎ ለስፖርቱ ውጤታማነት ስትራቴጂዎችን በማውጣት የአስፈጻሚነት ሚናውን መወጣት ይኖርበታል፣” በማለት “ፍሬ አልባ ለሆኑ ስብሰባዎች፣ ለጥናትና ተያያዥ ጉዳዮች” በሚል በየምክንያቱ የሚወጣው አንጡራ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ በሚታወቅበት በዚህ ወቅት እየሆነ ያለውን የኮሚሽኑን አካሄድ ይተቻሉ፡፡

ኮሚሽኑ ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ምክንያት ምንድነው? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ በስፖርት ኮሚሽን የማኅበራት ማደራጃና ዕውቅና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ብርሃኑ የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “የበጀት ድጋፉን መታገድ በሚመለከት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ደብዳቤው እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይሁንና ኮሚሽኑ ዓርብ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በጉዳዩ ከመከረ በኋላ ውሳኔውን በማጠፍ ብሔራዊ ተቋማቱ የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን እያቀረቡ የበጀት ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ ስምምነት ላይ ደርሷል፤” ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ግን ከዕገዳው በቀር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ የደረሳቸው ምንም ነገር እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...