በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ
አገራችን ኢትዮጵያ የቱንም ያህል በኢኮኖሚ ኋላ ቀር ብትሆን ዘመናትን የተሻገረ የፖለቲካ ነፃነት ባለቤት መሆኗ ለእኛ ኩራታችን ነው፡፡ ለባዕዳን ወራሪዎች ተንበርክኮ የማያውቀው ታላቁና ኩሩው ሕዝባችን በራሱ የሚተማመንና ለማንነቱ ግድ የሚሰጠው ነው፡፡ ‹‹አበው ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› ይሉናል፡፡ ‹‹የፉክክር በራፍ ሳይዘጋ ያድራል›› እንዲሉ እርስ በርስ ስንራኮት ውድ አገራችንን ከእነ ጭራሹ እንዳናጣት ክፉኛ ያሠጋል፡፡ በጠበበ ብሔርተኝነት ምርቃና አቅላቸውን የሳቱ ህሊና ቢስ ጽንፈኞች በኦዴፓ ውስጥ አድረው እየሠሩ ያለውን ሰይጣናዊ ተግባር እየታዘብን ነው፡፡
ሉዓላዊነቷ በተረጋገጠ በአንዲት አገር ውስጥ የፖሊስና የመከላከያ ኃይልን በአደራ ጠባቂነት የማደራጀት፣ የመምራትና ለብዙኃኑ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ጥቅም ላይ ይውል ዘንድ፣ በተገቢው ሥፍራና ጊዜ የማሰማራት ሕጋዊ መብትና ሥልጣን ያለውና በማዕከል ከተዘረጋው ሥርዓት አፈንጋጮች ሆነው በተገኙት ላይ ደግሞ አስፈላጊ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ በብቸኝነት የተፈቀደለት መንግሥት ብቻ ነው፡፡
ከዚህ ተቋም ውጪ ራሳቸውን አደራጅተውና ቀላልም ሆነ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቀው በኅብረተሰቡ ውስጥ በህቡዕም ሆነ በገሃድ የሚንቀሳቀሱ አካላት (Vigilante Groups)፣ መንግሥታዊ ሥልጣንን እንደሚገዳደሩ ታውቆ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ እንግዲህ በሥራ ላይ ከሚገኘው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 አቀራረብ በውል ለመረዳት የምንችለው ይህንኑ እውነታ ነው፡፡
የተጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ለማናቸውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ፤›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ተጠቃሹ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በትክክል እየሠራ ያለ መርህ አይመስልም፡፡ ራሱ ‘ዋልታ ረገጥ’ ሲል የሚጠራቸውን አሸባሪ ድርጅቶች አስመልክቶ ቸርነቱ ያለ ቅጥ የበዛው መንግሥታችንም ቢሆን በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌው የጣለበትን ግዴታ በጥብቅ ተጠያቂነት መንፈስ ለመወጣት ከመሞከር ይልቅ፣ እንደ ቀዳሚ የሚቆጠረውን ኃላፊነቱን ጨርሶ የዘነጋና የተወው እስኪመስል ድረስ ፍፁም ለዘብተኝነት አይሉት ዳተኝነት ክፉኛ ተጫጭኖት ነው የምናየው፡፡
ልጅና የእንጀራ ልጅ
እኛ ዜጎቿ ‘ውስጡን ለቄስ’ እንደሆነ ብናውቀውም ድኅረ ደርግ ኢትዮጵያ፣ ‹‹ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩልና የማይበላለጡ ናቸው፤›› እየተባለ ሲቀነቀንባት የቆየች አገር ናት፡፡ በእርግጥ ይህንን ወርቃማ ዶክትሪን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ድንጋጌ ውስጥ መሰንቀሩ ብቻውን ለዜጎች እኩልነት መረጋገጥ አንዳች ጠብ የሚል ትሩፋት እንደሌለው አያሌ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለእዚህ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን በአንድ በኩል ለታዋቂው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ለእስክንድር ነጋና ለተከታዮቹ ያለ በቂና ሕጋዊ ምክንያት የተነፈገውን በሰላም የመቃወም መብት አፈና በታዘብን በጥቂት ቀናት ልዩነት፣ በዜናና መረጃዎች አሠራጭነት ተግባር ተጠልሎ አገር የማፍረስ ፈቃድ የተሰጠው እስኪመስል ድረስ አንደኛውን ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም ቋንቋ ከሌላው እየለየ ሲያራክስ ወይም ሲያወድስ ውሎ የሚያድረውን የኦሮሚያ ሚዲያ መረብና የዚሁ ተቋም ቁንጮ የሆነውን የጃዋር መሐመድን ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴና ከመንግሥት በኩል የሚደረግለትን ልዩ እንክብካቤ መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡
‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች›› እንዲሉ፣ በዜግነት አሜሪካዊ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ አፄ በጉልበቱ የሆነ ሞገደኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የለውጡን ወጀብ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶ፣ በግሉም ሆነ በሚዲያ መረቡ አማካይነት ያሻውን ሲተፋ መሽቶ ቢነጋ አንዳች ጠያቂና ተቆጪ የለውም፡፡ እንዲያውም የማናህሎኝነቱ ደረጃ ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም፡፡ እንደ አንድ የለውጥ አራማጅ ተቆጥሮና በአጋርነት ተደፋፍሮ እንዲገባና ራሱን በነፃነት እንዲሸጥ የተፈቀደለት ቢሆንም፣ ሌላው ቀርቶ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሟሎቻቸው እንኳ ቅንጣት ታህል አክብሮት ሲያሳያቸው አናስተውልም፡፡
ለግብረ ገብነት ፍፁም እንግዳ የሆነው ፀያፍና ያልተገራ አንደበቱ አንዱን ሲዘልፍና ሌላውን ሲለክፍ ራሱን በዕብሪት እንዳሳበጠና ሌሎችን የጎሪጥ እንደተመለከተ በማናለብኝነት ዕርምጃው ቀጥሎበታል፡፡ እነሆ ሰውየው ከሕግና ከሥርዓት በላይ መሆኑን ያለ ጥርጥር እያሳየን ነው፡፡ በሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግደው ጃዋር መሐመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው ካሰሙት ዲስኩር ጋር በተገናኘ፣ በውጭ አገር ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ ሚዲያዎችን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ የሰነዘሩት መረር ያለ ማስጠንቀቂያ ብዙም የተመቸው አይመስልም፡፡ ሁላችንም እንደ ተከታተልነው ወደ ሩሲያ ከማቅናታቸው በፊት ዶ/ር ዓብይ በዚያ ዲስኩራቸው የተባለውን ማስጠንቀቂያ ያሰሙት በጅምላ ነበር፡፡
ሆኖም “ምንትስ ያለበት ዝላይ አይችልም”ና አጅሬው በተለይ ለእኔና ለኦሮሚያ ሚዲያ መረብ የተሰነዘረ ነው ብሎ አረፈው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ነበር “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” በማለት ከተሳለቀ በኋላ፣ በውድቅት ሌሊት አንድ ጊዜ ‹‹መንግሥት ሲሰጠኝ የነበረውን የግል ደኅንነት ጥበቃ ሽፋን እኔን ሳያማክር ሊያነሳብኝ ነው››፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ “የግድያ ሙከራ ተፈጸመብኝ” ላፕቶፑን ድንገት ብድግ አድርጎ የድረሱልኝ ጥሪውን እንደተለመደው ለቄሮዎች በፌስቡክ ያስተላለፈው፡፡
ከዚያ በኋላማ ምኑ ቅጡ?
ጀግናቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ የመንፈቀ ሌሊት ጥሪው በፌስቡክ የተላለፈላቸው ወጣቶች በስሜት ገንፍለው ዱላና ገጀራቸውን እየያዙ ወደ ጃዋር መኖሪያ ቤት ተመሙ፡፡ አድራጎቱ በዚህ የሚገታም አልነበረም፡፡ የአዲስ አበባን ዙሪያ አካባቢዎች ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በሐረርና በድሬዳዋ ከተሞች መንገዶች ተዘግተዋል፣ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል፣ መኖሪያ ቤቶች በእሳት ጋይተዋል፣ የንግድ መደብሮች ተዘርፈዋል፡፡ ንፁኃን ዜጎች በብሔርና በሃይማኖታቸው ብቻ እየተለዩ አረመኔያዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፣ በአሰቃቂ ሁኔታም ተጨፍጭፈዋል፣ ሕይወታቸውን እንዲያጡና አካላቸው እንዲጎዳ ተደርጓል፡፡
የኦሮሚያ ፖሊስ እንደነገረን በሁከቱ የተገደሉት ሰዎች 67 የደረሱ ሲሆን፣ 213 የሚሆኑ ወገኖች የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል፡፡ የወደመውን የመንግሥትና የግል ሀብትማ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ መሪር ፍዳና መከራ በአገርና በሕዝብ ላይ ሊደርስ የቻለው፣ ራሱን በኦሮሞ የመብት ትግል ዘዋሪነት የሰየመውና በመንግሥት እየተጠበቀና መንግሥትን በድፍረት የሚገዳደረው ጃዋር በፌስቡክ ባስተላለፈው የክተት ጥሪ መሆኑን እንደ ገና መልሶ ልብ ይሏል፡፡
ለመሆኑ ጃዋር መሐመድ ተይዞ ለፍርድ እስኪቀርብና እስኪቀጣ ድረስ ምን ያህል ንፁኃን ዜጎች መሞትና መቁሰል አለባቸው? ምን ያህል የመንግሥት፣ የሕዝብና የግል ሀብትስ በእሳት መጋየትና መውደም ይኖርበት ይሆን? እውነቱን ለመናገር ብዙዎቻችን ሰሚ ጆሮ ተነፍጎን እንጂ ጉሮሯችን እስኪነቃ ብዙ ጮኸናል፣ ወትውተናል፣ ብዕራችን እስኪዶለዱም ድረስ ጦምረናል፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል? ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት መቸ ይሰማል››? ለነገሩ አንድ ጥሬ ሀቅ አስረግጠን ማወቅ ይገባናል፡፡ ‹‹የቱንም ያህል ጊዜ ወንዝ ውስጥ ቢቀመጥ ድንጋይ የውኃ ዋና ሊማር ወይም ሊለምድ አይችልም፤›› ይባላል፡፡
እንደ ጉራማይሌ ሊቆጠር በሚችል አድራጎት ከራሱ ከመንግሥት በኩል ከፍተኛ እንክብካቤ የሚደረግለት ይህ ግለሰብ፣ በጠቅላይ አዛዥነት የሚያንቀሳቅሰው የቄሮ ሠራዊት ጠዋትና ማታ በፌስቡክ እየታዘዘ አገሪቱን በጠቅላላውና ኦሮሚያን በተለይ ማመስና ዜጎቻችንን ቁም ስቅል ማሳጣት ከጀመረ እኮ ውሎ አድሯል፡፡ ታዲያ ሰሞኑን በመዲናችን ከመሬት ወረራ ባለፈ እንደ ለመደው መንገዶችን በድንጋይና በግንዲላ በማዘጋትና ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰትን በማስተጓጎል ተግባሩ እንደ ገና መጠመዱን ብናይና ብንሰማ ለምንድነው ያን ያህል የሚገርመን? ቀድሞ ነገር ‹‹በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል››?
በአነታራኪው የፌስቡክ ኡኡታ ማንን እንመን?
ጃዋር ‹‹በህቡዕ ተጠቃሁ፣ የግድያ ወንጀል ተፈጸመብኝ›› ሲል ያሰማውንና ቄሮዎችን አወናብዶበታል የተባለውን ስሞታ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራሉ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው እንዳጣጣሉት ዓይተናል፣ ሰምተናል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው እሳቸው እንደ ነገሩን ከሆነ እንደ ሌሎች ከስደት እንደ ተመለሱ ታዋቂ ግለሰቦችና በውጭ ሆነው ሥርዓቱን ሲታገሉ የቆዩ አማፅያን ድርጅቶች፣ መሪዎች ሁሉ የጥበቃ ኃይሎችን የማንሳቱን ሥራ መጀመሩ ብቻ እውነት ነው፡፡
እዚህ ላይ አስደማሚው ጉዳይ አስቀድሞ በሠራው ፈርጀ ብዙ ወንጀል ተይዞ በቁጥጥር ሥር ውሎ እንዲመረመርና ለፍርድ ቀርቦ እንዲቀጣ ባልተለያየ ድምፅ ደጋግመን ዳኝነት የምንጠይቅበትና የምንወተውትበት ግለሰብ፣ በራሱ በመንግሥት በኩል የተንበሸበሸ መስተንግዶና እንክብካቤ የሚደረግለትና ከአንድ የካቢኔ ሚኒስትር በላይ የሆነ የልዩ ጥበቃ ሽፋን ሲሰጠው የቆየ የበኩር ልጅ መሆኑን ከአገሪቱ የሕግ አስከባሪ ቁንጮ አንደበት ያለ ኃፍረት ማዳመጣችን ነው፡፡
ውድ ወገኖቼ! የተባለው ጥቃት በእውነት ተሞክሮ ወይም የታቀደው የግል ደኅንነት ጥበቃ ኃይሎችን የማንሳቱ ተግባር በመንግሥት ተከናውኖ ቢሆንስ ኖሮ፣ ለአንድ ለጃዋር ደኅንነት ሲባል በምን ሒሳብ ነው የኦሮሚያ ወጣቶች ጭዳ እንዲሆኑ በደረቅ ሌሊት የሚፈረድባቸው? ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራሉ መግለጫ በተቃራኒ የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ‘ወንድማችን’ እያሉ ያለ ይሉኝታ አብዝተው በሚያንቆለጳጵሱት በጃዋር መሐመድ ላይ የተፈጸመው ልዩ የጥበቃ ኃይሎችን ድንገት የማንሳት ዕርምጃ ስህተት እንደነበር ተናግረው፣ ለግለሰቡ ሲደረግለት የቆየው ጥበቃ ቀድሞውኑ በመንግሥት ታምኖበት የተጀመረ በመሆኑ እንደ ወትሮው ይቀጥላልና ተረጋጉ ሲሉ ዱላና ገጀራ ታጥቀው በመውጣት በአመፅ ተግባር ለተሰማሩትና ፊት ለፊት ባገኙት ሕይወትና ንብረት ላይ ሁሉ ነውረኛና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት በማድረስ ላይ ለተሰማሩት ደመ ሞቃት ቄሮዎች ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
በእርግጥ ይህ ጉዳይ ከመነሻው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን የሚመለከት ሆኖ ሳለ፣ የኦሮሚያው መሪ በየትኛው ሥልጣናቸው አረጋጊ ይሁን ምን በውል ያለየለትን ያንን አደናጋሪ መግለጫ እንደ ሰጡ ማብራራት ያለባቸው ራሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎ የፖሊስ ኮሚሽነራቸው በማግሥቱ ብቅ ብለው “ጃዋር እኮ ለኦሮሞ ሕዝብ የዓይን ብሌኑ ነው” ሲሉ በአደባባይ መናገራቸውን የሰማን ወገኖች፣ ከቄሮው ፊታውራሪ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የእነ ማን እጅ እንዳለበት ለመገመት አላዳገተንም፡፡
ስለሆነም ኦዴፓ ከሕዝብ ጋር መታረቅ ከፈለገ የኦሮሚያ ክልልን ምክትል ፕሬዚዳንት ከፖሊስ ኮሚሽነራቸው ጋር፣ ሳይውል ሳያድር ከያዙት ኃላፊነት ሊያነሳቸውና ለስሜታቸው ወደ ቀረበ ሌላ የሥራ ገበታ ገለል ሊያደርጋቸው እንደሚገባ እኔ በበኩሌ አምናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የፌዴራሉን መንግሥት ባልፀዳ ተረኝነት ቁጥር አንድ ሆኖ የሚዘውረው ኦዴፓ ይህንን ማድረጉ ብቻ ይበቃዋል ማለት አይደለም፡፡ ኃላፊነት በጎደለው የግለሰቦች ዕርምጃና ይህንኑ ፈጥኖ ለመቀልበስ እያሳየ ባለው የበዛ ተለሳላሽነት ከኦዴፓ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ራሳቸው ከፖለቲካ ባለፈ የሕግ ተጠያቂ ናቸው፡፡
ጌታቸው አሰፋን ከመቀሌ ጠርዞ ማምጣት ቢያቅታቸው ጃዋርን ከቦሌ አስሮ ለፍርድ ማቅረብ እንደምን ዳገት ሊሆንባቸው ይችላል? ታዲያ ከሰማይ በታች ያለው ኃጢያት ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ብቻ ይደፈደፋል ማለት አይደለም፡፡ ከኦዴፓ ጋር ተጣምረው አገሪቱንና ሕዝቧን በኢሕአዴግ ስም የሚመሩትና እንደ አዴፓና ደኢሕዴን ያሉት ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አባሎቻቸውን በካቢኔው ውስጥ ሰግስገዋልና ከመጨረሻው ኃላፊነት እንደማያመልጡ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡፣
በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ለበለጠ ጊዜ እነርሱ ባመኑና በተረዱበት መንገድም ቢሆን ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ጥቅም መከበር ሲታገሉ ከኖሩት መካከል ኦቦ ዳውድ ኢብሳና ኦቦ ሌንጮ ለታ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት በአካል ተገኝተው ራሱን ጃዋርን ጨምሮ አብረዋቸው ከነበሩት ከእነ ከማል ገልቹና ከእነ በቀለ ገርባ በመለየት እንደተማፀኑት ሁሉ፣ የተከበሩ አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን ተሰሚነትና ማኅበራዊ ተቀባይነት ተጠቅመው የሰውየውን የድረሱልኝ ልፈፋ ያለ ጥያቄ ተከትለው ወደ አደባባይ በመትመም ከሚያካሂዱት ደም አፍሳሽ ሁከትና ትርምስ ይቆጠቡ ዘንድ ባልተለያየ ድምፅ ምክርና ተግሳፅ የማስተላለፉን ተግባር ያለ መታከት መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
በመጨረሻም አዲስ አበባ ውስጥ በተንደላቀቀ ቪላ ተቀምጦ የግል ጥበቃ ኃይሎቹ እንደተነሱበት ብቻ ሳይሆን መንግሥት ባሰማራቸው ኃይሎች አማካይነት የግድያ ሙከራ እንደ ተፈጸመበት ጭምር በማውሳት “ጀግናችሁን ተከላከሉ” ሲል በዕድሜ ያልበሰሉና በልምድ ያልጎለመሱ ለጋ ወጣቶችን ለአስከፊ ጥፋት የሚያነሳሳው ጃዋር መሐመድ ራሱን እንጂ፣ የትኛውንም የኦሮሞ ሕዝብ እንደማይወክል መታወቅ አለበት፡፡ ይልቁንም በሐሰተኛ ጥሪ የሚያሠልፋቸውን ሥራ አጥ ወገኖች ለእርስ በርስ ግጭት እየዳረገ የሚነደውን እሳት መሞቅ የሚያዝናናው ፍጡር ነው፡፡
ስለሆነም የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር ያልሆነ ቁርሾ ውስጥ እንዲገባና እስከ ወዲያኛው ድረስ ደም እንዲቃባ ተግቶ እየሠራ ያለውን የጃዋርን ጥላቻ ወለድ ቅስቀሳ እየሰሙ፣ በገዛ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ ቆንጨራና ገጀራ የሚያነሱትን ልጆቹን መምከርና ማስታገስ ይኖርበታል እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡