Friday, March 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢኮኖሚውን ለውጭ ገበያ ክፍት ከማድረግ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ትልቅ ጉዳይ ተወዳዳሪነትን ማስፈን መቻል ነው›› ኪኒቺ ኢህኖ (ፕሮፌሰር)፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አማካሪ

ጃፓናዊው ኪኒቺ ኦህኖ (ፕሮፌሰር) ለአሥር ዓመታት ያህል መንግሥትንና ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዙሪያ ሲያማክሩ ቆይተዋል፡፡ የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ኦህኖ (ፕሮፌሰር) በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከትምህርት ተቋሙ ያገኙ ሲሆን፣ በኢንዱትሪ ፖሊሲ በኢኮኖሚ ልማት መስክ የዓመታት ምርምርና ተሞክሮ አዳብረዋል፡፡ በዚሁ በኢንዱስትሪ ፖሊሲ ረገድ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተሻገረ የቅርብ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከሁለቱ መሪዎች ጋር በየጊዜው እየተገናኙ ስለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያማክሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ግንኙነትም ወደ ተቋምነት ተቀይሮ በጃፓን መንግሥት በኩል በሚደረግ ድጋፍ፣ በየመንፈቁ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ባላሥልጣናት የሚታደሙበት ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ የምክክር መድረክ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከአምና ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) በአካል እንዳላገኟቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ቀድሞው አካሄድ ሳይሆን፣ በዙሪያቸው በሚገኙ አማካሪዎችና ባለሥልጣናት በኩል በሚቀርብላቸው ገለጻ ካልሆነ በቀር በአካል መነጋገሩን የፈለጉት እንደማይመስላቸው ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት የተተገበሩ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎች የተነሱበትን ዓላማ ማሳካት እንዳልቻሉ፣ በተለይም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ከመንገድ ስለቀሩባቸው ችግሮች፣ ስለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይዘቶችና በፖሊሲው መስተካከል ስላለባቸው ጉዳዮች ኦህኖ (ፕሮፌሰር) ያስቀመጧቸውን ነጥቦች ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ሲዘጋጁ ጀምሮ ይተሳተፉ ስለነበር፣ በዕቅዶቹ ከተካተቱት ግቦች ምን ያህሉ ተሳክተዋል?   

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ብዙም አልተሳኩም፡፡ ስለመጀመርያውና ስለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ስናነሳ ስለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊና ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ እንወያይ ነበር፡፡ ከውይይታችን የምገነዘበው ዋናው ቁምነገር ሁለቱም ለመማር የነበራቸው ጉጉት ነው፡፡ ከጃፓን፣ ከማሌዥያና ከሌሎችም አገሮች ብዙ ማወቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ማወቅና መረዳት በጣም መሠረታዊ ጉዳይ ነበር፡፡ በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ከነ ጃፓን የተወሰዱት እንደ ካይዘን የመሳሰሉ ሐሳቦች ተካተውበት ነበር፡፡ ስለምርትና ምርታማነትም በዕቅዱ ተካቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሐሳቦች ወደ ተግባር ሊለወጡ አልቻሉም፡፡ እንደምገምተው ሆን ተብሎ አይመስለኝም፡፡ እንደማስበው ኢትዮጵያ እነዚህን ነገሮች ለመተግበር በሚገባ ደረጃ ትምህርትና ተሞክሮ አልቀሰመችም፡፡ ፖሊሲ ማርቀቅ አንድ ጉዳይ ቢሆንም፣ መተግበሩ ግን መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱ አለመሳካት እንዳለ ሆኖ፣ የአቶ መለስና የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መታወሻ ወይም ‹ሌጋሲ› ግን ስለፖሊሲ ጉዳዮች ለመማር የነበራቸው ፍላጎትና ጉጉት ነው፡፡ ለመማር የነበራቸውን ቁርጠኝነት አደንቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ውጤቶች አልታዩም፣ አልመጡም፡፡ በምክክሮቻችን ወቅት ከምናነሳቸው አንኳር ጉዳዮች ዋናው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ነበር፡፡ የዘርፉ ጥንካሬና ሥርፀት፣ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የወጪ ንግድና ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ የዘርፉ ድርሻ ምንም ለውጥ አላሳየም፡፡ ትራንስፎርሜሽን ወይም ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግርም አልተፈጠረም፡፡ መማማሩ ላይ ችግር አልነበረም፡፡ የተማሩትም ነገር ስህተት አልነበረም፡፡ ችግሩ ግን ፖሊሲ መቅረፅ ላይ ብቻም ሳይሆን፣ አተገባበሩንም መማር ያስፈልግ ነበር፡፡

ለምሳሌ ካይዘን በጥሩ ደረጃ እየተስፋፋ መጥቶ ነበር፡፡ እስከ ታች ድረስ ተጠናክሮ እንዲተገበርና እንዲዳብር መሥራት ይገባ ነበር፡፡ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲጠናከሩ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ሌላው ትልቅ ችግር የተሟላ ማኅበራዊ ለውጥ አለመታየቱ ነው፡፡ በምሥራቅ እስያ ለምሳሌ ለ15 ዓመታት ያህል የአሥር በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ የቀጠሉ አገሮች፣ የተሟላ ማኅበራዊ ለውጥ አሳክተዋል፡፡ ግብርናው እየቀነሰ ኢንዱስትሪው እያደገ መጥቷል፡፡ ይህም እየተስፋፋ ለመጣው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አስችሏል፡፡ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተዋል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ የኢኮኖሚውን 30 በመቶ ድርሻ መያዝ ችሏል፡፡ አንዳንድ ጊዜም እስከ 40 በመቶ ድርሻውን ይይዝ ነበር፡፡ ከዚያም እየቀነሰ ለአገልግሎት ዘርፍ ድርሻውን እየሰጠ ይመጣል፡፡ ኢኮኖሚውም ከፍተኛ የአገልግሎት ዓይነቶች ላይ የተመሠረተ መሆን ይጀምራል፡፡ ኢትዮጵያም በ15 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የዕድገት መጠን አስመዝግባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጃፓን፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከማሌዥያና ከቬትናም ጋር ስናስተያየው ምንም ዓይነት ትራንስፎርሜሽን ልታሳይ አልቻለችም፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ መጠየቅ አለብህ፡፡ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበው በምርት ዕድገት ሳይሆን፣ በመንግሥት ኢንቨስትመንት ላይ ተመርኩዞ ነው ይላሉ፡፡ ግብርናውም ኢንዱስትሪውም ምርታማነታቸው ለኢኮኖሚው ዕድገት ብዙም አስተዋጽኦ አላደረገም በሚለው ይስማማሉ?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- አዎን ትክክል ነው፡፡ በቅርቡ የሠራነው የሰው ኃይል ምርታማነት ጥናት ውጤት የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ የዕድገቱ የመጀመርያ ሰሞን የመንግሥት ኢንቨስትመንት ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉ ባልከፋ ነበር፡፡ እየቆየ ግን ሊለወጥና ትክክለኛውን አምራችና ምርታማነት በሚገልጽ አቅም ሳይሆን፣ መንግሥት ወጪ ማድረግ ስላለበትና በመንግሥት ኢንቨስትመንት ላይ በሰፊው የተንጣለጠ ኢኮኖሚ ሆኖ መቆየቱ የማምረት ብቃትንና ምርታማትን ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ማንም የሚያየው ነው፡፡ ሕንፃዎቹን ተመልከት፡፡ መንገድና ሌላውንም መሠረተ ልማት ተመልከት፡፡ ይህ ክስተት በሌሎች አገሮችም ዘወትር ያጋጥማል፡፡ በኢንዶኔዥያ፣ በማሌዥያ፣ በቬትናምና በታይላንድ ይህንኑ ችግር አስተውያለሁ፡፡ በጃፓንም ይህንኑ ተመልክቻለሁ፡፡ በኮሪያም ታዝቤያለሁ፡፡ በተለይ የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ ይህን ዓይነቱ አካሄድ የተመደ የፖለቲካ ምላሽ ነው፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚው ዕድገት እንዳይቀዛቀዝ ስለሚፈልግ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ ለአጭር ጊዜ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ለረዥም ዓመታት በዚህ አኳኋን መቀጠል ግን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ቀውሶች ውስጥ ይከታል፡፡ የበጀት ጉድለት፣ የዋጋ ንረት፣ የወጪ ንግድ ሚዛን መዛባትና የተባባሰ የውጭ ምንዛሪ ቀውስ መዘዞችን ያመጣል፡፡ ይህ ከመፈጠሩ በፊት ትክክለኛውን አካሄድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ወጪን በመቀነስ፣ የኢኮኖሚውን ዕድገትም በተወነሰ ደረጃ ማቀዛቀዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ የተለመደ ፖለቲካዊ ዑደት ነው፡፡

እንደማስበው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በመንገድ ግንባታ፣ በግድብ ሥራዎች፣ በተለይም እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ስህተት ናቸው ባልልም ከፍተኛ ወጪ ግን ይጠይቃሉ፡፡ ብድር ውስጥ መግባት የግድ ይሆናል፡፡ በርካታ የቻይና ብድሮች ማለትም የአጭር ጊዜ ብድሮች ውስጥ መዘፈቅን አምጥተዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በመጠኑ አካሄዱን ቀዝቀዝ ማድረግ ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ ይህም ጤናማ ምላሽ ነው፡፡ እርግጥ ነው መሠረተ ልማት ያስፈልጋል፡፡ ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ሚዛኑን መጠበቅም ግድ ነው፡፡ ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገትም ወሳኝ ነው፡፡ ትንሽ ቀዝቀዝ ማድረግ እንጂ ከእነ ጭራሹ ማቆምም አይመከርም፡፡ ሌላው መሠረታዊ ችግራችሁ የወጪ ንግዱ ደካማ መሆን ነው፡፡ የወጪ ንግድ ገቢና የብድር ዕዳ ክፍያው ንፅፅሮች ሲሠሩ ከምታገኙት ይልቅ ለዕዳ የምትከፍሉት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ከ15 ዓመታት በፊት በነበሩት የኢኮኖሚ ዕቅዶች ዋናው ትኩረት ድህነትን ማጥፋት ነበር፡፡ ቢቀንስም ድህነት አልጠፋም፡፡ ከአሥር ዓመታት ወዲህ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ግዴታ ነው ተባለ፡፡ ሳይሆን ቀረ፡፡ አሁን ደግሞ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብልፅግና በአሥር ዓመታት ውስጥ ይረጋገጣል ብሎ መንግሥት ተነስቷል፡፡ ይህንን አካሄድ እንዴት ያዩታል?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- እንደተረዳሁት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው ለሦስት ዓመታት የተቀረፀ ነው፡፡ የአሥር ዓመታት አቅጣጫ ያለው ከሆነም መልካም ነው፡፡ ስለፖሊሲው ይመለከታቸዋል የተባሉ ሰዎች ዝርዝር ጉዳዮች የተካተቱበት ሰነድ እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር፡፡ ማግኘት የቻልኩት በ‹‹ፓወር ፖይንት›› የተዘጋጀውን አጭር ሰነድ ብቻ ነው፡፡ በአማርኛ ከ100 ገጽ በላይ የተዘጋጀ ሰነድ እንዳለና እየተተረጎመ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል፡፡ ምክንያታዊ አስተያየት ለመስጠት ይህንን ሰነድ መመልከት ይኖርብኛል፡፡ ይሁን እንጂ ካለኝ የተወሰነ መረጃ በመነሳት፣ በሚዲያው፣ በመንግሥትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አካባቢ ውይይቶች እንደተደረጉበት እሰማለሁ፡፡ እንደ ጠቅላላ ማዕቀፍ ካየነው ችግር የለውም፡፡ መጀመርያ የኢኮኖሚው ችግሮች ምንድን ናቸው በማለት ይተነትናል፡፡ ትራንስፎርሜሽን አልመጣም፣ የመንግሥት ወጪዎች በጣም ከፍተኛ ናቸው፣ ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮች ተጽፈዋል፡፡ እስማማለሁ፡፡ መካተት ያለባቸው ሌሎች መረጃዎችም ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የሰው ኃይል ፍልሰትና እንቅስቃሴና የአመለካከት ችግሮች መካተት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል እነሱ ሪፎርም ብለው ያስቀመጧቸው ሦስት የለውጥ ምሰሶዎች ተካተዋል፡፡ አንደኛው የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግሮች ማስተካከል ላይ ያተኮረው ነው፡፡ ይህን ማካተት ቅድሚያ የሚሰጠውና ጥያቄ የማይቀርብበት ነው፡፡ ጥያቄው ግን ችግሩን መፍታት ይችላሉ ወይ የሚለው ነው፡፡ ሁሉም አገሮች ለኢኮኖሚ ዕድገት ቅድመ ሁኔታ ስለሚሆንባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ማስተካከል ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ ከፖሊሲ አኳያ ከታየ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማስተካከል ብዙ አያጨቃጭቅም፡፡

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እነሱ መዋቅራዊ ለውጥ ያሉት እኔ ግን ፕራይቬታይዜሽን፣ ለዚሁ የሚስማሙ ሕጎችን ማውጣትና ትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶችን ለመሸጥ የሚደረግ ለውጥ እለዋለሁ፡፡ መዋቅራዊ ማሻሻያ ያሉት እኛ ጠቅላላ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንለዋለን፡፡ ሦስተኛው የዘርፍ ማሻሻያ ያሉትና የተመረጡ ኢንዱስትሪዎችን ለማሻሻል ያላቸውን ፍላጎት ያስቀመጡበት ሰነድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ‹‹ዋሽንግተን ኮንሰንሰስ›› በተሰኘው የፖሊሲ ምክረ ሐሳባቸው ማክሮ ኢኮኖሚንና ጠቅላላ የፖሊሲ ማሻያ ማዕቀፍ እንዲኖር ይወተውታሉ፡፡ ይሁን እንጂ የተወሰኑ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የሚደረጉ ለውጦች ላይ ብዙም ምክር አይሰጡም፡፡ እነ ዓለም ባንክ የተወሰኑ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ማስፋፋቱ ላይ አታተኩሩ ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ምክር የምትቀበል አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም አቶ መለስ ይህንን ምክረ ሐሳብ በፅኑ ተቃውመውት ነበር፡፡ የአቶ መለስ ችግር ግን የኢንዱስትሪ ፕሮሞሽን ላይ ጊዜ ማጥፋታቸው ነው፡፡ ከእነ ጃፓን፣ ኮሪያና ማሌዥያ መማራቸው ጥሩ ቢሆንም ውጤታማ ሊያደርጋቸው የሚችልና ወደፊት በመንግሥት እጅ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ግል ለማዛወር የሚያግዝ የረዥም ጊዜ ዕቅድ አለማዘጋጀታቸውም ጎድቷቸዋል፡፡ በዚህ እኔም ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ በእሳቸው የሥልጣን ዘመን ኢኮኖሚው ለውጭ ተወዳዳሪዎች ባይከፈት እንኳ፣ ወደፊት እንዴት መከፈት እንዳለበት የሚያመላክት አቅጣጫ ማስቀመጥ ነበረባቸው፡፡ ይህ አቅጣጫም ውድድርን መሠረት ባደረገ ቅድመ ሁኔታ ላይ እንዲመሠረት ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡

ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን ለውድድር ክፍት ማድረግ ከተፈለገና ዘርፉን ማሻሻል ካስፈለገ መጀመርያ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች ተሠርተውና ተሟልተው፣ ከዚህ ዘርፍ ውስጥ ይህን ያህሉን ብቻ ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት እናደርጋለን ማለት ይቻል ነበር፡፡ እንዲሁ ዘርፉን ለመክፈት ብለህ አይደለም ክፍት የምታደርገው፡፡ ተወዳዳሪነትህን ስታጠናክርና የውጭ ኩባንያዎችን መፎካከር የምትችልበት አቅም ላይ ስትደርስ ነው ዘርፉን ክፍት ማድረግ ያለብህ፡፡ በዚህ ሒደት የሚጎዱ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ትክክለኛው አካሄድ አቅም ከዳበረ በኋላ መክፈቱ ነው፡፡ አቶ መለስ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሥራ አልሠሩም፡፡ እኔ በጣም የማደንቃቸው መሪ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ለውድድር ክፍት ማድረግ ስለሚቻልበት የረዥም ጊዜ ዕቅድ ካለማስቀመጣቸውም በተጨማሪ፣ በኢንዱስትሪው መስክ ያደርጉት የነበረው የማበረታቻና የፕሮሞሽን እንቅስቃሴም ብዙ ውጤታማ አልሆነላቸውም፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ስኬታማ አልነበሩም፡፡ አሁን እየመጣ ያለው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያካተታቸው ሦስት የለውጥ ማዕቀፎች አንዳንዶች እንደሚተቿቸው፣ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ምክረ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ እነ የዓለም ባንክ ስላሉ ሳይሆን፣ መንግሥት በማሻሻያ ያስቀመጣቸው ሦስቱ የለውጥ ሐሳቦች በምሥራቅ እስያም ተንፀባርቀዋል፡፡ ግን ደግሞ በውስጣቸው የሚኖሩ ይዘቶች ምንድን ናቸው የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡

እነዚህን የፖሊሲ ሐሳቦች በምን መንገድ ውጤታማ ታደርጋቸዋለህ? ምን ያህል ክብደት ትሰጣቸዋለህ? የሚለው የጨዋታው ማጠንጠኛ ነው፡፡ እንደማስበው ሰዎች የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ ምክር ነው እያሉ መተቸት ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ አይደለም፡፡ በየትኛውም አገር የሚደረግ ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግር መፍታት ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አይፈልግም፡፡ ፖለቲካዊ ይዘት ቢኖረውም በአብዛኛው የቴክኒክ ጥያቄ ነው፡፡ ሌሎች ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎችን ማሻሻል ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግና ወደ ግል ማዛወር፣ ጃፓንም ከድኅረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከተለችው አካሄድ ነው፡፡ የንግድ ዘርፉን ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ተወዳዳሪዎች ክፍት ከማድረጉ ቀደም ብሎ ለአሥር ዓመታት ያህል ሲያዘጋጀው ነበር፡፡ የማሽነሪ ኢንዱስትሪው እንዲያድግ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችና የተሽከርካሪ ማምረቻው ሁሉ ተወዳዳሪ እንዲሆን በመደረጉ ውጤታማ መሆን ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለውጭ ተወዳዳሪዎች በሯን ክፍት ያደረግባቸው ዘርፎች ላይ ተገቢውን ሥራ አልሠራችም ማለት እንችላለን?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- በዚህ መንገድ ልግለጸው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው የመጀመርያው ጉዳይ ክፍት የሚደረገው ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ማብቃት ነው፡፡ በሁሉም መስክ ሳይሆን በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተወዳዳሪነትን ማስፈን ይገባል፡፡ ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ለምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ተሞክሮ መውሰድ አለበት፡፡ በተለይም በአተገባበር ላይ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች በመቅረፍ ተወዳዳሪነቱ የተረጋገጠ ዘርፍ ሲፈጠር፣ የውጭ ኩባንያዎችም እንዲገቡበት ማድረጉ ነው የሚመከረው፡፡ እንዲያውም የተወዳዳሪነት አቅሙ የተፈጠረለትን ዘርፍ ክፍት ከማድረግ በፊት አምስትና አሥር ዓመታት መጠበቅ ይገባል፡፡ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ለዚህ መሥራት አለባቸው፡፡ ጃፓን በመኪና ምርት ይህንን አሳክታለች፡፡ እዚህም በጨርቃ ጨርቅና በአልሳት ዘርፍ ብሎም በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ የአገር ውስጥ አቅም ከጎለበተ በኋላ ለውጭ ክፍት ማድረጉ ይመረጣል፡፡ ኢኮኖሚውን ሊበራላይዝ ለማድረግ ስትነሳ እንዲህ ዓይነቱን ጨዋታ ቀድመህ መጫወት ይጠበቅብሃል፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ተዳዳሪዎች ክፍት ተደርጓል፡፡ በዚህ ዘርፍ ተወዳዳሪነት ተገንብቶ ነው እንዴ ለውጭ ክፍት የተደረገው?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ተወዳዳሪ እንኳ አይደላችሁም፡፡ ዘርፉ በመንግሥት ሞኖፖል ሥር የቆየ ነው፡፡ ኢንተርኔት ምን ያህል ቀርፋፋ እንደሆነ እያየሁ ነው፡፡ መንግሥት የቴሌኮምና የሎጂስቲክስ ዘርፎች አፋጣኝ ገንዘብ ያስገኛሉ ብሎ አስቦ ከሆነ የከፈታቸው ስህተት ነው፡፡ መንግሥት ሊረዳው እንደሚችለው ዘርፎቹ ረዥም ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ያሉትን ቁልፍ ዘርፎች ለውጭ ተዋናዮች ክፍት ስታደርግ መጀመርያ ጥናት ማካሄድ ይኖርብሃል፡፡ እንደገና ዘርፉን የማደራጀትና ምን ያህል ትርፍ ሊያስገኝ እንደሚችል ካረጋገጥክ በኋላ ነው ዘርፉን መሸጡ የሚመከረው፡፡ የቀድሞዋ የሶቪዬት ኅብረት ከመውደቋ በፊት ይህ ጥናት በአውሮፓ ኅብረት የልማት ባንክ አማካይነት ተካሂዶ ነበር፡፡ እነ ኪርጊስታን፣ ካዛኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን የመሳሰሉት አገሮች ሲወጡ ይህ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ተጣድፎ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመሸጥ መነሳት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቃት ያለው ተቋም በመሆኑ አሁን ባለው አደረጃጀትና ባለቤትነት ለረዥም ዓመታት መዝለቅ ይችላል፡፡ ምናልባት የውጭ ተወዳዳሪዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ እንደማስበው ተገቢውን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ለአካባቢ ጥበቃም ተገቢውን ትኩረት መስጠትም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የዓለም ባንክ ድጋፍ እየሰጠ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ግን መጠናከር አለበት፡፡

ከፕራይቬታይዜሽንም ሆነ ኢኮኖሚውን ለውጭ ገበያ ክፍት ከማድረግ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ትልቅ ጉዳይ ተወዳዳሪነትን ማስፈን መቻል ነው፡፡ ለምሳሌ ቴሌኮምን ክፍት ማድረግ ካስፈለገ ምን ዓይነት የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ነው የውጭ ኩባንያዎች እንዲሠማሩ የሚፈለገው? ዘርፉን ገዝቶ የሚገባው ኩባንያ ምን ዓይነት ሥራ ነው የሚሠራው? ምን ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል? የሚሉት ጉዳዮች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ የምዕራብ አገሮች በተለይም አሜሪካ ዘርፎቻቸውን ክፍት ከማድረጋቸው በፊት በሕጋዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የመብትና የአሠራር ጉዳዮች ያሳስቧቸዋል፡፡ ጃፓን የዘርፉ ተወዳዳሪነት ያሳስባታል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች እንዲጠልፉት፣ ገንዘብም ትርፍም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንዳያደርጉ የሚከላከል አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብዙ ዓመታት ይጠይቃል፡፡ ተጣድፎ መሸጥ መክሰርን ያስከትላል፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለ ማርያም ፈጣን ተማሪዎች ናቸው፣ ስለኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለማወቅ ጉጉት ነበራቸው ብለዋል፡፡ እርስዎን ከመሳሰሉ ምሁራንና ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ተዋንያን ጋር አብዝው ይገናኙ ነበር ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አካሄድ ግን ከሁለቱ መሪዎች እንደሚለይ ይገልጻሉና ይህንን ቢያብራሩልኝ?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ሁለቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለዩ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ እንደ እነሱ ያለ መሪ አልገጠመኝም፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የተለየ ትኩረት ነበራቸው፡፡ ለጨርቅ ጨርቅ፣ ለስኳር ኢንዱስትሪዎችና ለማሽነሪ ዘርፍ ብሎም ለተናጠል ኩባንያዎች ሳይቀር ትኩረት ይሰጡ ነበር፡፡ ሁለቱም በግላቸው ለካይዘን ፍልስፍና ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር፡፡ ከተጣበበ የሥራ ሰዓታቸውም ቢሆን እየቀናነሱ እንደ እኔ ላሉትና ከእኔ በላይም ታዋቂነትን ላተረፉ ምሁራን፣ ለኢንቨስተሮችና ለዲፕሎማቶች የሚሰጡት ጊዜ ነበራቸው፡፡ ይህ በሌሎች አገሮች ያልታየ ነው፡፡ እንደማስበው ዓብይ (ዶ/ር) መደበኛውን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን አካሄድ የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርን ያህል ነገር በቀላሉ ማግኘትና ለሁለት ሰዓታት ያህል ስለፖሊሲ ጉዳይ ማውራት መደበኛ የመንግሥት አሠራር አይደለም ብለው ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ ስለዚህ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የሌሎችም ጉዳዮች ላይ ባለሟሎቻቸው ይመስሉኛል ገለጻ የሚያደርጉላቸው፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ዋና ፍላጎታቸው የሚታዩትን ችግሮች ከመፍታት ባሻገር በሳይንስና ኢኖቬሽን ላይ የማተኮር ይመስላል፡፡ እንደ ቴሌኮም ዘርፍ ያሉትን ወደ ግል የማዘዋወር፣ ከዓለም ባንክ ጋር የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታዎችን ለማሻሻል መሥራት ላይ ያተኮሩ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች ላይ አቶ ኃይለ ማርያም እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ በጥቅሉ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቅጣጫቸውም በትኩረታቸውም ከቀድሞቹ የተለየ አካሄድ የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ፍላጎታቸው አጠቃላይ ማሻሻያ ማድረግና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወሩ ላይ ያተኮረ ይመስላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለእነዚህ ጉዳዮች ቅድሚያ አልሰጡም ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ፖሊሲ የማውጣቱን ሥራ በጽሕፈት ቤታቸው ለሚገኙ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪዎቻቸው፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ለሌሎችም በውክልና የሰጡ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ አካላት ስለፖሊሲ ጉዳይ ኃላፊነት የተሰጣቸው በመሆናቸው፣ እነዚህን ተቋማትን ከሚመሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ነው የምንነጋገረው፡፡ በቀጥታ እሳቸውን አናገኛቸውም፡፡ ይህ ምናልባት መደበኛ አሠራር ሊሆን ይችላል፡፡ የዘይቤ ለውጥ አለ፡፡

እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የምጠይቃቸው እየተካሄዱ የነበሩና አሁንም የሚታሰቡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በግል ቁርጠኝነት ኖሯቸው እንዲያስተገብሩ ነው፡፡ ካይዘን አሁንም እንዲተገበር ቢደረግ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ እንዲፈጸም ከመጠበቅ ይልቅ የተመረጡት ላይ መረባረቡ ይመከራል፡፡ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅድሚያ በሚሰጧቸው የተመረጡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ትልቁን አጀንዳ እንዲያሳካ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለዚህም ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡ እኔ ብሆን ሦስት፣ አራት፣ ግፋ ቢል አምስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየወሩ ኮሚቴ እየሰበሰቡ ስለወጪ ንግድ አፈጻጸም ወይም ደግሞ ስለኢንዱስትሪ ፓርክ ላይመክሩ ይችላሉ፡፡ ይህ የእሳቸው አመራር ዘይቤ ላይሆን ይችላል፡፡ ችግር የለውም፡፡ በሌላ መንገድም ቢሆን ግን ግላዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸውና ችግር ሲያጋጥምም በቀጥታ ችግሩን በመመልከት መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አቶ መለስ የዚህ ዓይነት አካሄድ ነበራቸው፡፡ ዓብይም (ዶ/ር) በራሳቸው የአመራር ዘይቤ መጓዛቸው ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ጋር አንድ መጽሐፍ በቅርቡ በአርትኦት ተሳትፋችሁና አዘጋጅታችሁ ለንባብ አቅርባችኋል፡፡ አርከበ (ዶ/ር) ወደ አካዴሚው ያደሉ ይመስላሉ፡፡

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- አሁን እንኳ ብዙም እየተገናኘን አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም አርከበ (ዶ/ር) በኢንዱስትሪ መስክ ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ በአዲሱ አስተዳደር ሥር ሌላ ሚና ያላቸው ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ወደ አካዴሚው አተኩረዋል፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ምን እንደሠራችና ምን መሥራት እንደምትፈልግ ለዓለም ለማስረዳት፣ እንዲሁም የዓለምና የአፍሪካ የልማት ዕሳቤዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይፈልጋሉ፡፡ በወጣቱ የመንግሥት አስተዳደር ወቅት የአንጋፋዎቹ ሚናም ይኸው ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለፕራይቬታይዜሽን በተለይም ስለውጭ ድርጅቶች መግባት ሲነሳ፣ ይህንን የማከናወን ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ አርከበም (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያማክሯቸው ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ሲገልጹና ስለአስፈላጊነቱም ሲያስረዱ ይታያሉ፡፡ ስለእነዚህ ጉዳዮች ከአርከበ (ዶ/ር) ተወያይታችሁ ታውቃላችሁ?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- አርከበ (ዶ/ር) ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት አላውቅም፡፡ ባለፈው ዓመት ስለኢኮኖሚ ጉዳዮች በየዕለቱ ይነጋገሩ እንደነበር አጫውተውኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ስላለው ነገር አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በማክሮ ኢኮኖሚ መስክ ያሉት ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ከቀጠለ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የት ልትገኝ ትችላለች? ወይስ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደሚለው ለውጥ ውስጥ እንገባለን?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች የሚሉ ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ልክ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ካልተሳሳትኩ የአዲስ ተስፋ ምድር የሚል እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ አሁን የአገር በቀል ማሻሻያ እየተባለ ነው፡፡ የአሥር ዓመታት ዕቅድ ለመንደፍ እየተሠራ ነው፡፡ ይህ በየአምስት ዓመቱ የሚመዘጋጅና የሚተገበር ዝርዝር የበጀትና የፕሮጀክት ዕቅዶች የሚካቱበት ሰነድም እየተተዘጋጀ ነው፡፡ እነዚህን ለማስፈጸምም የየዓመቱ ዕቅድ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ወደ አንድ አቅጣጫ ማቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ የፕላን አውጪዎችን ከሚገባው በላይ በሥራ በመወጠር ለዕቅድ ትግባራትና ለቁጥጥር የሚበቃ ጊዜ ማሳጣት እንዳይመጣ ከወዲሁ ማሰብና መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በየዓመቱ የሚዘጋጀው ዕቅድ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሌላ ወሳኝ የረዥም ጊዜ የዕቅድ ሰነድ ማዘጋጀቱም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከሚገባው በላይ የዕቅድ ሰነድ ዝግጅት ላይ ያውም ለአሥር ዓመታት የሚሆን ዕቅድ ለማውጣት መጣደፍ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ እንደሚገባኝ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ዕቅድ ነው፡፡ ይህም ለአሥር ዓመቱ አቅጣጫ መሠረት የሚጣልበት ነው፡፡ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የተቀመጡት ጉዳዮች ጥቅልና ሰፊ ሐሳቦች ናቸው፡፡ በተለይም በመዋቅራዊ ለውጥ ማሻሻያው ውስጥ የተቀመጡት ዝርዝር ሥራ ይፈልጋሉ፡፡ ከመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ቀደም ተብሎም የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግሮች ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት፣ የውጭ ብድር ዕዳ፣ የዋጋ ግሽበትን የመሳሰሉ ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሔ ይሻሉ፡፡ ሌሎቹ እንደ አይሲቲ፣ ማዕድን ዘርፍ ላይ የታሰቡት የማሻሻያ ሥራዎች ብዙም ቅድሚያ የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም እነዚህን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ የሞከሯቸውና ያልተሳኩላቸው ሥራዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ በዕቅዱ በረዥም ጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተፈጻሚ ከሚደረጉ መካከል ቢካተቱ ይመረጣል፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት የምንዛሪ ተመን የሚመራበትን አስተዳደርና የዋጋ ሥርዓት ከመንግሥት ቁጥጥር ሥር በማውጣት በገበያ እንዲመራ ወደ ማድረጉ እየመጣ ይመስላል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ይህ እንዲደረግ እየመከረ ነው፡፡ ይህን ማድረግ አሁን ላይ አስፈላጊ ነው?

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ከዚህ ቀደም ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ይህ ሐሳብ ሲነሳ ሰምቻለሁ፡፡ ይሁንና እኔ ከዚህ የሚቃረን ሐሳብ አለኝ፡፡ የምንዛሪ ተመኑ የሚመራበት ሥርዓት አሁን ባለው በከፊል በመንግሥት ቁጥጥጥር ሥር እንዲቆይ ነው የምመክረው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን ወይም እንደ አውሮፓ አገሮች ያለ የኢኮኖሚ አቋም ላይ ብትሆን ኖሮ፣ የምንዛሪ ተመኑ በገበያ እንዲመራ መፍቀዱ ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ ይሁንና ገና በልማት ላይ የሚገኝና በርካታ የመዋቅራዊ ችግሮች ባሉበት አገር ውስጥ የምንዛሪ ተመኑ በመንግሥት ቁጥጥር ዋጋው እንዲወሰን መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ አሁን ባለው የተመን አስተዳደር መሠረት የምንዛሪ ተመን ዋጋ ለውጡ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በዓመታት ውስጥ ጥቂት የዋጋ ዕድገት ሲዘመገብ ቆይቶ ነበር፡፡ ኢኮኖሚያዊ ችግርና ቀውስ በሚከሰትበት ወቅት ግን የዋጋ ለውጡ ከፍተኛ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚህም በተጨማሪ በመደበኛው የምንዛሪ ተመን ዋጋና በጥቁር ገበያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡

ኦህኖ (ፕሮፌሰር)፡- ይህ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረቱ የፈጠረው ቀውስ መገለጫ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ የምንዛሪ ተመን ለውጥ ማድረጉ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚ መዋቅር በጣም ስስ በሆነ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡ በርካታ የማኑፋክቸሪንግ አቅም ቢኖራችሁ ኖሮ ባልከፋ ነበር፡፡ ምርቶቻችሁ በዋጋ ተወዳዳሪ ሆነው በውጭ ገበያ እንደ ልብ በተሸጡ ነበረር፡፡ ይህ አቅም በሌላችሁ ጊዜ የምንዛሪ ተመን ለውጥ ብታደርጉና የምንዛሪ ተመኑን በገበያ ዋጋ እንዲተዳደር ብትፈቅዱ፣ የቡናና የሰሊጥ ዋጋ ከዓለም ዋጋ በታች ሊወርድ ቢችልም ከዓለም ዋጋ በላይ በመክፈል ነዳጅ፣ ማሽነሪዎችና ሌሎችም ምርቶችን ለመግዛት ትገደዳላችሁ ማለት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ሳይሆን፣ የግብርና ምርቶችን የምትሸጡ በመሆናችሁ ይህ የኢኮኖሚያችሁ ሥሪት የዋጋ ተመን ለውጥ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አያስችላችሁም፡፡ እንደማስበው ባለፈው ጊዜ ያነጋገርሁት የዓለም ገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ተጠሪ ይመስለኛል፣ የምንዛሪ ተመን አስተዳደርን በገበያ እንዲመራ ከማድረግ ይልቅ በመንግሥት እጅ እየሆነ ነገር ግን መጠነኛ የገበያ ሥርዓት እንዲጫወት ማድረጉ ይበጃል፡፡ ቬትናምም ይህንኑ ነው የምታደርገው፡፡ የምንዛሪ ተመኑን መለወጥ የዋጋ ግሽበትን ከማባባስ አልፎ፣ የኢኮኖሚውን ወጪ ከፉኛ ስለሚያንረው ትርፍና ኪሳራን አሥልቶ መጓዙ ይበጃል፡፡ በጠቅላላው ግን በታዳጊ አገሮች ውስጥ የምንዛሪ ተመን ዋጋ ላይ ለውጥ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...