በሰኔ ወር መጨረሻ 2011 ዓ.ም. የፀደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ የተቃወሙ የ71 ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ለሁለት ቀናት ሊያደርጉ ያሰቡትን የረሃብ አድማ ለጊዜው በመተው በሰሞኑ ጥቃት ለተጎዱ ወገኖች ደም እንደሚለግሱ አስታወቁ፡፡
በፓርላማ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀውን የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የሥነ ምግባር አዋጅ በመቃወም ለ48 ሰዓታት የሚቆይ የረሃብ አድማ በአራት ኪሎ ሚያዝያ 27 አደባባይ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕቅድ ይዘው ነበር፡፡
ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ለከተማ አስተዳደሩ የፈቃድና የጥበቃ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም፡፡ የአስተዳደሩ የሚመለከተው አካል በቃል ቦታ እንዲቀይሩ ጠይቋቸው እንደነበርና እነሱ ደግሞ ቦታ እንደማይቀይሩ በመግለጽ እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁም፣ ኃላፊው ቢሯቸው ባለመገኘታቸው በጸሐፊያቸው ስለተነገራቸው ዕቅዳቸውን ማዘግየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ የረሃብ አድማውን በማዘግየት፣ በሰሞኑ ጥቃት ለተጎዱ ወገኖች ረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ደም ለመለገስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የምርጫ አዋጁን የተቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከረሃብ አድማው በተጨማሪ፣ በሰላማዊ ሠልፍና በአዳራሽ ስብሰባዎች ተቃውሞአቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ አዋጁ የዜጎችን የመደራጀት መብት የሚገድብና ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ህልውና አደጋ የደቀነ በመሆኑ እንደሚቃወሙት አስታውቀዋል፡፡