Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የ15 ቢሊዮን ዶላር የትስስር መዋዕለ ንዋይ...

ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የ15 ቢሊዮን ዶላር የትስስር መዋዕለ ንዋይ ዕቅድ ይፋ አደረጉ

ቀን:

በቀጣናው የተሻሻለ ፖለቲካዊ ግንኙነት እየመጣ ነው በሚል ዕሳቤ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጂቡቲ ቀጣናዊ ትስስር የሚያጠናክሩበትን የ15.89 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ ይፋ አደረጉ፡፡

ዕቅዱ ይፋ የተደረገው አምስቱ አገሮች በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተካሄደው፣ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው፡፡ ይኼ ውይይትም ካሁን ቀደም በአዲስ አበባና በዋሽንግተን ዲሲ ተደርገው የነበሩ የአገሮቹ ከፍተኛ ባለሙያዎች ውይይቶች ቀጣይ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ስምምነቱን ያደረጉት የአምስቱ አገሮች የገንዘብ ሚኒስትሮች በአጠቃላይ የ180 ሚሊዮን ሕዝቦችና የ170 ቢሊዮን ዶላር አገራዊ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ያላቸው አገሮች ወኪሎች መሆናቸውን በመጠቆም ባወጡት መግለጫ ይኼ ዕቅድ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በዓለም ባንክ የሚደገፍ እንደሚሆንና አራት የትኩረት መስኮች እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

እነዚህ የትኩረት መስኮችም ቀጣናዊ የመሠረተ ልማት ትስስርን ማጎልበት፣ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስሮችን ማበረታታት፣ አይበገሬነትን መገንባትና የሰው ሀብት ልማትን ማጠናከር ናቸው፡፡

‹‹እነዚህ አዳዲስና ትራንስፎርሜሽን የሚያመጡ ዕቅዶች ሲሆኑ፣ በጋራ ሲሠራባቸው የሕዝቦቻችንን አገራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶችን የያዙ ማዕቀፎች ይሆናሉ፤›› በማለት በመግለጫው ያስታወቁት የገንዘብ ሚኒስትሮቹ፣ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት ዕቅድ ይሆናል በማለትም ገልጸውታል፡፡  

በተጨማሪም ከሦስቱ ድጋፍ ሰጪዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ማዕቀፎቹን በመተግበር በቀጣናው ትስስርና ብልፅግናን ለማምጣት የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዕቅዱ እ.ኤ.አ. በ2020 የመጀመርያው አጋማሽ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ይፋ እንደሚደረግ ያስታወቀው መግለጫው፣ ዝርዝር ይዘቶቹም በተመሳሳይ ዓመት የመጀመርያዎቹ ወራት እንደሚገለጹ አስታውቋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለ6,000 ኪሎ ሜትር መንገድ ዝርጋታ የተመደበው ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር፣ ከሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዝ ከመግለጫው ጋር አባሪ የተደረገው ሠንጠረዥ ያስረዳል፡፡ ይኼ ለቀጣናዊ የመሠረተ ልማት ትስስር ከተመደበው 12 ቢሊዮን ዶላር ሦስት አራተኛውን የሚወስደው ለኢኮኖሚ መስመሮች ልማት ይውላል፡፡ ለኪስማዩ፣ የላሙና ሞቃዲሾ መስመር፣ ለኪስማዩና ለጂቡቲ መስመር፣ ለበርበራና ለጂቡቲ መስመር፣ እንዲሁም ለሞቃዲሾ፣ ለበርበራና ለበሳሶ መስመር ግንባታ የሚውል ይሆናል ተብሏል፡፡

በዚሁ ዘርፍ 1.84 ቢሊዮን ዶላር የሚወስደው የቀጣናዊ የኃይል ንግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያና የጂቡቲ ሁለተኛ የኃይል መስመር ግንባታና የሶማሊያ የኃይል ማስተላለፊያ ዋና መስመር ግንባታ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ – ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ – ኤርትራ፣ የኬንያ – ሶማሊያ፣ የጂቡቲ – ሶማሊያ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ – ኬንያ ሁለተኛ የኃይል መስመር ግንባታዎች አዋጭነት ጥናት ለማከናወን ይውላል ተብሏል፡፡ አንድ የጂዲታል ገበያ ለመፍጠርም 1.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚመደብ ተመላክቷል፡፡

የተቀሩት ሦስት ዘርፎች የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር፣ አይበገሬነትን መገንባት፣ እንዲሁም የሰው ሀብት ልማትን ማጎልበት እያንዳንዳቸው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላርና 1.55 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሊድ ሸሪፍ ከስምምነቱ በኋላ፣ ‹‹የአፍሪካ ቀንድ የመልክዓ ምድራዊ ስትራቴጂክ አቀማመጥ በተለይም ከቀይ ባህር፣ ከዓረብ ባህረ ሰላጤ፣ ከህንድ ውቅያኖስ፣ እንዲሁም ከኤደን ባህረ ሰላጤ አኳያ ወሳኝ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ የላቀ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ይህም በአገሮቹ የትስስር፣ የአይበገሬነትና አዲስ የብልፅግና ዘመን ለማምጣት በማገዝ ከሰላም ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲገበዩ ያደርጋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ከሶማሊያ በስተቀር አራቱ አገሮች ከአፍሪካ አማካይ 3.5 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ዕድገት ያስመዘገቡ መሆናቸውንና ኢትዮጵያ 7.7 በመቶ፣ ጂቡቲ 5.6 በመቶ፣ ኬንያ 5.9 በመቶ፣ ኤርትራ 4.2 በመቶ፣ እንዲሁም ሶማሊያ 2.9 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡ ቀጣናው በኢትዮጵያና በኤርትራ ዕርቀ ሰላም ሳቢያ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ ይኼም በአገሮቹ በድንበር ዘለል ንግድ ምልክት ማሳየቱንና የኢኮኖሚ ትስስርን ያጎለብታል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...