በኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የላቀ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሙያቸው ጤና ላይ የተመሠረተና ከፍተኛ ትምህርትም የቀሰሙበት ስለሆነ፣ የእናቶችንና የሕፃናት ሞትን ለማስቀረት ዕውን ባደረጓቸው ተቋማት አማካይነት ሲተጉና ሲያስተጉ ኑረዋል፡፡
የሕክምና ባለሙያዋ ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ብዙዎች በቅጽል ስም ‹‹ቦጌ›› እያሉ ይጠሯቸው ነበሩ፡፡ እንደ ስማቸው ቦግ ብለው ብርሃን ያንፀባረቁበት አንዱ ተግባራቸው በትውልድ ቦታቸው፣ የከምባታ ሴቶች በአንድነት ቁሙ የሚል ፍች ያለውን ‹‹ከምባቲ ሜንቲ ጌዚማ ቶፔ›› (Kembatti Mentti Gezzima-Tope) ከእህታቸው ፍቅርተ ገብሬ ጋር መመሥረታቸው ነበር፡፡
በ1989 ዓ.ም. የተቋቋመውና ‹ኬኤምጂ› የተሰኘው ተቋም በወቅቱ በሰፊ ተዛምቶ የነበረውን ኤችአይቪን መከላከል፣ የሴቶችን መጠቃት፣ የልጃገረዶችን ግርዛት፣ ጠለፋንና ሌሎችም ለሴቶች ጎጂ የሆኑ የልማድ ተፅዕኖዎችንና ልምዶችን የመግታት ዓላማ አንግቦ ነበር የተንቀሳቀሰው፡፡
ኬኤምጂ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በ26 ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠና የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በመተግበር በቀጥታ ከ481 ሺሕ በላይ፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ችግረኛና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች (ከእነዚህ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው) በመድረስ ላይ እንደሚገኝ በአንድ ወቅት ተዘግቦ ነበር፡፡
ለራሳቸው ኩራትና እርካታ ለኅብረተሰባቸውም አለኝታ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወናቸው የሚወሳላቸው ዶ/ር ቦጋለች፣ የመሯቸው መርሐ ግብሮች በከንባታ የሚገኙ ሴቶች ለራሳቸው መብት እንዲቆሙ፣ ኑሯቸውን የሚመሩበት የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና በራሳቸው እንዲተማመኑ አስችሏቸዋል፡፡ በኅብረተሰቡም ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በከንባታ ጠንባሮ እ.ኤ.አ በ1999 መቶ በመቶ የነበረ የሴቶች ግርዛት ሥርጭት እ.ኤ.አ በ2008 በተደረገ ጥናት ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህን ተከትሎም ከግርዛት ጋር ተያይዞ ሴቶች በወሊድ ወቅት የሚደርስባቸው ሥቃይና ሞት ቀንሷል፡፡ አሥር ሚሊዮን ችግኞችንም በማስተከል የአካባቢው ሥነ ምኅዳር እንዲሻሻል ጥረት ማድረጋቸው በገጸ ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡
በማኅበረሰቡ አስተሳሰብ ላይ በወንዶችም ጭምር ዓይነተኛ ለውጥ እንዲመጣ የማኅበረሰብ ውይይትን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመው፣ በሁሉም የገጠር ክፍሎች ተግባራዊ ማድረጋቸው ለውጡም እንዲመጣ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው እ.ኤ.አ በ2002 ያልተገረዘች ሴት ባል ማግባት ችላለች፡፡
ዶ/ር ቦጋለች የእናቶችና ማህፀን ሆስፒታል ከንባታ ውስጥ እንዲሠራ፣ ሴት ተማሪዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አስተዋጽኦ በማድረግ አይደፈሬ የነበረውን የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተፅዕኖን ሰብረው በማኅበረሰብ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ በማስቻልም ይወሳሉ፡፡
በ1952 ዓ.ም. በከምባታ የተወለዱት ዶ/ር ቦጋለች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእስራኤል ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮሎጂና በማይክሮ ባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ለድኅረ ምረቃ ወደ አሜሪካ በማቅናት በፓራሲቶሎጂ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከማሳቹስቴስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምናቸውን በአሜሪካ ሲከታተሉ የነበሩት ዶ/ር ቦጋለች፣ ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ማረፋቸውን የከምባታና ጠምባሮ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን ጠቅሶ ኢቲቪ ዘግቧል፡፡
ዶ/ር ቦጋለች ላከናወኑት ላቅ ያሉ ተግባራት በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አገራዊ ተቋማት ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ እነሱም እ.ኤ.አ. በ2005 ከአውሮፓ ምክር ቤት የኖርዝ ሳውዝ ፕራይዝ፣ መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገው የዓለም ጤና ምክር ቤት የጆናታን ማን አዋርድ (2007)፣ ከቤልጂየም የኪንግ ባውዶዩን (Baudouin) ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት ፕራይዝ (2013) ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባም በ2008 ዓ.ም. የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት የበጎ ሰው ሽልማትን ሲሸለሙ ከተነገረው ዜና ሕይወታቸው የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
‹‹የሴቶችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንደ ግርዛት፣ ጠለፋ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ለጆሮ ያልደረሱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን መግታትና ሴቶች በክብር እንዲኖሩ ማድረግ ዓላማቸው ሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ጊዜ፣ ቁሳቁስ፣ ዕውቀት፣ ከሰው መግባባትና ሕይወት የሰጣቸውን ዕድል ሁሉ ተጠቅመው በማኅበረሰባቸው የለውጥ ምክንያት ለመሆን የተነሱ ነበሩ፡፡››