Thursday, June 13, 2024

በሕዝብ ስም የምትነግዱ ገለል በሉ!

ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› የሚባለውን ዕድሜ ጠገብ አባባል ያስታውሳል፡፡ ኢትዮጵያ ላጋጠማት ፅኑ ደዌ የማያዳግም ፈውስ ከመፈለግ ይልቅ፣ በሕመም ማስታገሻ ማስቀጠሉ የማትወጣው ማጥ ውስጥ እየከተታት ነው፡፡ ለጨጓሯ ሕመም መታሻ እንደማይታዘዘው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግርም ማድበስበስ መታዘዝ የለበትም፡፡ ችግሩ አፍጦና አግጦ እየታየና ደም እያፋሰሰ፣ በተድበሰበሱ ኮንፈረንሶች ሰላም ማምጣት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት በልሂቃን የተዘራው የጥላቻና የመለያየት ዘር ፍሬ አፍርቶ፣ አዲሱ ትውልድ በተቀደደለት ቦይ እየፈሰሰ አገር እየተተራመሰ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓት በመመሥረት ስም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ከመጠን በላይ ጎልቶ በመሰበኩ፣ የጋራ እሴቶችና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ አብሮነቶች እየተዳፈኑ ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል ከሚፈጠሩ ዕለታዊ ግጭቶች አንስቶ በፖለቲካ ልሂቃን መካከል የሚከሰቱ ተራ አለመግባባቶች ጭምር፣ ብሔርንና ሃይማኖትን እየታከኩ ንፁኃንን ሲቀጥፉና የአገር አንጡራ ሀብት ሲያወድሙ በግልጽ እየታየ እንደ ሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ መቅበር አያዋጣም፡፡ ይልቁንም የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ በሆነው መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይሻላል፡፡ የበዳይና የተበዳይ ትርክት አሁንም አየሩን ሞልቶት፣ በትውልዱ ሕይወት ላይ እየተቆመረ በነበረበት መቀጠል አይቻልም፡፡ ለአገር ህልውናና ለሕዝቡ ደኅንነት ሲባል ችግራችን ምንድነው ተብሎ ለመፍትሔው በጋራ መሥራት ይመረጣል፡፡ አሁን የሚታየው የልሂቃን የጽንፈኝነት አካሄድ አሸናፊም ተሸናፊም የማይኖርበት ውድመት ነው የሚያስከትለው፡፡

ኢትዮጵያ የ110 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የጋራ አገር መሆኗ አይካድም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ ወዘተ ምክንያት ብዝኃነት መገለጫቸው ነው፡፡ ይህ ብዝኃነት በአግባቡ መያዝ የሚችልና ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በክፉም ሆነ በደግ አብሮ ከመኖር ባለፈ፣ ልዩነት የሌለ እስኪመስል ድረስ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን በመሻገሩ ነው፡፡ ይህ የዘመናት ሕይወቱ በሥነ ልቦና ጭምር አንድ አድርጎት አገሩን በጋራ ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ በተለያዩ ገዥዎች የደረሱበትን ጭቆናዎች አብሮ የተካፈለ ከመሆኑም በላይ፣ ድህነትና ኋላቀርነትም አንድ ላይ ሲደቁሱት ኖረዋል፡፡ በታላቁ የዓድዋ ጦርነትም ታላቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ሲሆንም አንድ ላይ ሆኖ ነበር፡፡ አንዱ የተሻለ ተጠቃሚ ሆኖ ሌላው ሲበደል አይታወቅም፡፡ ከውስጡ የወጡ ጥቂቶች ግን እንዳሻቸው መሆናቸው አይካድም፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከአንድ አካባቢ የተመራረጡ ሳይሆኑ፣ ጥቅምና ሥልጣን ያቆራኛቸው ዘመነኛ ወዳጆች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ዘመን እንዳሉት የጥቅም ሸሪኮች ማለት ነው፡፡ በዚህ ዕሳቤ ላይ ተመሥርተን የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ ስንመረምር፣ ችግሩ ያለው ሕዝብ ዘንድ ሳይሆን ኃላፊነት የማይሰማቸው ልሂቃን ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ወቅቱ አደገኛ እየሆነ ያለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እንደሚታወቀው በተለያዩ ጊዜያት ልሂቃኑ በሚፈጥሩዋቸው ችግሮች ምክንያት ግድያዎች፣ መፈናቀሎችና ውድመቶች ሲያጋጥሙ ሕዝብ እርስ በርሱ ከለላ ይሰጣጣል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተፈጥረው ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ የአንድ ብሔር ተወላጆች ለሌሎች ከለላ ሲሰጡ እንደነበር በግልጽ የተነገረ ነው፡፡ አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ፡፡ ከግጭቶቹ በኋላ ልሂቃኑ ችግሮችን እያድበሰበሱና እያልኮሰኮሱ ለሰላም የማይመጥኑ ኮንፈረንሶች ሲጠሩ፣ ከተለያዩ ብሔሮችም ሆነ ቤተ እምነቶች የተወከሉ ሰዎች እውነቱን አፍርጠው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ከመደጋገፍና ከመተባበር ውጪ ችግር እንደሌለ በተደጋጋሚ ተነግሮ የሐሰት ኮንፈረንሶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ፣ በሌላ ጊዜ የንፁኃንን ሕይወት ያስገበሩ ጥቃቶች ለምን ተፈጸሙ ሲባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ከጥቅማቸው ውጪ ለአገርና ለሕዝብ የማያስቡ ልሂቃን በሕዝብ ላይ እየቆመሩ አገር ያተራምሳሉ፡፡ ልብ ተብሎ ከሆነ እነሱ በጣም አርቀው እሳቱን ስለሚቆሰቁሱት፣ የሚማገዱት የሚልኳቸው የዋሆችና የማይመለከታቸው ንፁኃን ናቸው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እንደ ቀበሮ ባህታዊ የተሰማሩ አስመሳዮችና ጨካኞች ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ታሪክንና የፖለቲካ አመለካከትን የግጭት መሣሪያ እያደረጉ ያፋጃሉ፡፡ ልዩነትን በጤነኛ መንገድ ለሐሳብ የበላይነት ልዕልና ማወዳደሪያ ማድረግ ሲቻል፣ የግጭት ነጋዴዎች የንፁኃንን ደም ያፈሱበታል፡፡ ችግሩን እያባባሱም የአገር ህልውናን ይፈታተናሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ይዘለቃል?

ለኢትዮጵያ ከፌዴራል ሥርዓት የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የፌዴራል ሥርዓቱ የግለሰብንም ሆነ የቡድንን መብት መሳ ለመሳ እንዲያስተናግድ፣ በኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነት የማይፈጥር ሥርዓት እንዲገነባ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ዜጎች በሙሉ በሕግ ፊት እኩል እንዲሆኑ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን፣ በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መንግሥት እንዲመሠረት፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች ገለልተኝነት እንዲረጋገጥ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበርና በአጠቃላይ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚመች ዓውድ ማደላደል የሁሉም ወገኖች ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ጤናማና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ሊኖር የሚችለው እነዚህና መሰል ጉዳዮች ተግባራዊ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ አንደኛው የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት አሠራርም ሆነ ሥርዓት ከዚህ ዘመን ጋር አይሄድም፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ስለዚህ ዓይነቱ ጤናማ ሥርዓት በሰከነ መንገድ መነጋገር ሲገባቸው ግጭት ለምን ይመርጣሉ? ወደኋላ እየሄዱ ለዘመኑ በማይመጥኑ ትርክቶች ለምን ይወዛገባሉ? የፌዴራል ሥርዓቱ ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ እንዲገነባ ከመነጋገር ይልቅ፣ ሕዝቡንም አገሪቱንም ወደኋላ በሚመልሱ የማይረቡ ጉዳዮች ለምን ይነታረካሉ? ለምንስ ንፁኃንን ግጭት ውስጥ እየከተቱ ሰለባ ያደርጋሉ? የማይመስል ሰበብ እየፈጠሩ አገር ከማተራመስና ሕዝቡን ከማሰቃየት፣ ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሰላማዊው ፖለቲካ ላይ ቢያተኩሩ ይመረጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ፈፅሞ መቀጠል  አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ጉልበተኞችን፣ ጨካኞችን፣ ከመጠን ያለፉ ራስ ወዳዶችንና ሥርዓተ አልበኞችን እስከሚበቃው ዓይቷል፡፡ ይህ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ አሁንም የእነዚህ ግዴለሾችና ስግብግቦች ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ በመንግሥትና በአንድ ግለሰብ መካከል አጋጠመ በተባለ ችግር ምክንያት 86 ሰዎች ተገደሉ ሲባል እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ ከማሳዘን አልፎም ያሳፍራል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ሰቆቃ መስማት ጤና ይነሳል፡፡ መንገዶች ተዘጋግተው ንፁኃን ሲገደሉና የአገር ሀብት ወድሞ የሕዝቡ ደኅንነት ለአደጋ ሲጋለጥ፣ የአገር ህልውና ሥጋት ተጋርጦበት የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆን በራሱ በጣም ያንገበግባል፡፡ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር ተስኖት ሽብር ሲፈጠር ያስቆጫል፡፡ ስንትና ስንት መልካም ተግባራት የሚከናወኑበት ውድ ጊዜ ሲባክን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ለአገራቸው ዕድገትና ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚጠበቅባቸው ወጣቶች፣ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ሆነው በገዛ ወገናቸው ላይ ሲዘምቱም በኃፍረት አንገትን ያስደፋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያገኘችው መልካም አጋጣሚ ከእጇ ላይ አምልጦ ሲፈረካከስ ያናድዳል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ግን በድንገት ወይም ሳይታሰብ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ ለመሆኑ ምንም መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ መታረም ካስፈለገ አሁንም ጊዜ አለ፡፡ በማድበስበስ ግን መቀጠል አይቻልም፡፡ ኃላፊነት በማይሰማቸው

የፖለቲካ ልሂቃን ምክንያት ኢትዮጵያ መበደል የለባትም፡፡ በሕዝብ ስም የምትነግዱ ገለል በሉ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...