የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በአሜሪካም ሆነ በሌላ ሦስተኛ ወገን አማካይነት ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለመደራደር ያደረገችው ስምምነት እንደሌለ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ቢሮ ለሪፖርተር በላከው መረጃ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል በአሜሪካ መንግሥት ጋባዥነት ሰሞኑን የሚደረገው ውይይት እንጂ ድርድር አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
“ድርድር የሚካሄደው በአንድ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ላይ የሚገኙ ወገኖች፣ ቀጣይ ውይይት ማድረግ በማይችሉበት ጊዜ በመረጡት በሌላ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ለመወያየት በሚስማሙበት ጊዜ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል፤” ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ “ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ያልተቋረጠና እየተካሄደ በመሆኑ ለድርድር የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፤” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአሜሪካ የሚገናኙትም ሐሳባቸውን በማቅረብ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ለማከናወን እንጂ፣ ድርድር ለማካሄድ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡
“ሦስቱ አገሮች ድርድር ለማደረግ የየትኛውንም አገርም ሆነ ተቋም ድጋፍ አልጠየቁም፣ ይህ እንዲሆንም ያደረጉት ስምምነት የለም፤” የሚለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሶቺ ከተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ አለመስማማታቸውንም አመልክቷል፡፡