Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቅማንት ኮሚቴ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ አለ

የቅማንት ኮሚቴ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ አለ

ቀን:

ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. የአማራ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከማዕከላዊና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የአማራና የቅማንት ተወላጆች በጭልጋ ወረዳ ባደረጉት ውይይት፣ የቅማንት ማንነትና ራስ አስተዳደር ይከበርልኝ ኮሚቴ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ድርጅት እንደዘገበው፣ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ውይይት፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ፍቃዱ ማሞ የቅማንት ኮሚቴ ያቀረበው ጥያቄ ለሁለቱ ማኅበረሰቦች ግጭት መንስዔ መሆን ስለማይገባው ለድርድር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ ሰላም በፍፁም ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥለት እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

‹‹በግጭት ምክንያት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መቆም አለበት፡፡ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እስኪፈታም በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ከሚፈልጉ ማንኛውም አካላት ጋር ለመወያየት ዝግጁ ነን፤›› ብለው፣ ሁለቱ ወንድማማች ማኅበረሰቦች በምንም ዓይነት ሁኔታ መጋጨት አይገባቸውም ሲሉ አክለዋል።

- Advertisement -

የክልሉ መንግሥት ቀደም ሲል ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ መግለጫ ማውጣቱ፣ እንዲሁም የሕዝብ ጥያቄ በሕዝብ ይሁንታ መፈታት አለበት የሚሉ ሐሳቦች ኮሚቴው ተቀብሎት እንደነበር በማስታወስ፣ ‹‹እኛና እናንተ ሳንባባል በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ውይይት መጀመሩ አስፈላጊ ስለሆነ፣ ኮሚቴው የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለውይይትም ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል።

ነገር ግን በውይይቱ ወቅት የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እናራምዳለን የሚሉ ሁለት ኮሚቴዎች መኖራቸውን፣ እነሱም በሕዝቡ መካከል ልዩነት እየፈጠሩ በመሆናቸው ለሰላማዊ ውይይት እንቅፋት አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፍቃዱ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የቅማንት ኮሚቴ ነን የሚሉት በሥነ ምግባር ችግር ያሰናበትናቸው ግለሰቦች ናቸው። በሰላማዊ ሒደቱ ላይ እንቅፋት ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡ አንድ ሕጋዊ ኮሚቴ ነው ያለው። እሱም እኔ በሰብሳቢነት የምመራው ነው። ሕዝቡም ዕውቅና ሰጥቶት ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

በውይይቱ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ባደረጉት ንግግር፣ የአማራና የቅማንት ማኅበረሰቦች ቤተሰብ እንደሆኑና በቤተሰብ መካከል የተፈጠረ ችግር በቤተሰቡ ካልፈታ በቀር ማንም ሊፈታው አይችልም ብለዋል።

በግጭት ማንም አሸናፊ መሆን እንደማይችልና ያለፈው ላይመለስ ለዛሬና ለነገ ሰላም ሁሉም የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሰላማዊ ውይይቶች በተለየ ይኼኛው ወደ ሰላም ሊያደርስ ያስችላል ተብሎ የታሰበ የመጀመሪያ ዙር ውይይት እንደሆነ አስረድተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ሰላማዊ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ ምሥጉንና ሚዛናዊ የአገር ሽማግሌዎች የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ማስታወሳቸው ተገልጿል። የተጀመረው ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የታሰሩ ሰዎች በምሕረት አዋጁ እንዲለቀቁ፣ እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

በአማራና በቅማንት ማኅበረሰቦች መካከል በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች በርካቶች መገደላቸውና መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ አውጥቶት በነበረው መግለጫ ከግጭቶቹ በስተጀርባ ሦስተኛ ወገን እንዳለ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...