Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በመድንና በአነስተኛ የፋይናንስ ሥራዎች የሚያሳትፉ አዋጆች ፀደቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተለያዩ ብድሮችም ፀድቀዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለበርካታ ዓመታት ሲተገበር የነበረውና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመድንና በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራዎች እንዳይሳተፉ የሚከለክሉ ሕጎችን የሚሽሩ አዋጆች አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው አምስተኛው ዘመኑ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ቀደም ብለው ቀርበውለት ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷቸው የነበሩ በርካታ ረቂቅ አዋጆችን በመጠነኛ ውይይት መርምሮ አፅድቋል፡፡

ከቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ውስጥ የመድን ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አንዱ ሲሆን፣ ረቂቁን ቀደም ብሎ በመስከረም ወር ለምክር ቤቱ ገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከሦስት ሳምንት በላይ ረቂቁን መርምሮ የደረሰበትን የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ መልሶ ባቀረበበት ወቅት የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በመድን ሥራ  እንዳይሳተፉ የተጣለው የሕግ ዕገዳ በማንሳት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይረዳል ብሏል፡፡ በተጨማሪም የተሻሻለው አዋጅ ለትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በአገሪቱ የመድን ሥራ እንዲንቀሳቀሱ ከመፍቀዱ ባሻገር፣ በአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጉዞ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያስችላቸውም ነው ሲል በውሳኔ ሐሳቡ ገልጿል፡፡

አዋጁ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ላይ ጥሎት የነበረውን ዕገዳ ከማንሳት በተጨማሪ፣ ሌሎች የተሻሻሉ ድንጋጌዎችንም አካቷል፡፡ ለአብነትም በዲጂታል ዘዴዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም በእስልምና መርሆች ላይ ስለተመሠረተው የታካፋል (Takafal) መድን አገልግሎት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በማሻሻያ አዋጁ ውስጥ ከተካተቱት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ የአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማገዝ የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ይረዳል ተብሏል፡፡

ከምክር ቤት አባላት ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅሙ እያጎለበተ መጥቷል የሚለው ምን ያህል ተጨባጭ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ናፈቁሽ ደሴ የኢኮኖሚውን አቅምና የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር አቅም እያጎለበተ መምጣቱን፣ ይህ ሲባል ግን ክፍተቶች የሉም ማለት እንዳልሆነና እነሱን ለመሙላት የሚያስችሉ የተለያዩ ሕጎች እየተዘጋጁ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ በስፋት ተወያይቶ በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አዋጁን አፅድቋል፡፡

በመቀጠል ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ መንግሥትና በፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ መካከል፣ ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሚመለከት ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ  አዳምጧል፡፡ ከፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ የተገኘው 85 ሚሊዮን ዩሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለመደገፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ብድሩ የሰባት ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ19 ዓመታት ውስጥ በመካከለኛ ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅ ሲሆን፣ አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት በመሆኑ የወጪ ጫናው ያልበዛና ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም ነው ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በዕለቱ ከብድር ስምምነቶች ጋር በተያዘ ከተመለከተው ውስጥ የቆላማ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽል፣ ለከርሰ ምድር ውኃ፣ መስኖ ልማትና የገጠር ግብርና ልማት፣ እንዲሁም የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ሊያሳድግ የሚችልን ጨምሮ ሌሎችንም ረቂቅ አዋጆችን በተመሳሳይ አፅድቋል፡፡

ከዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር የተገኘው 280 ዶላር በስድስት ክልሎች አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በ100 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያግዝ የብድር ስምምነት መሆኑን የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ ወ/ሮ ናፈቁሽ አስረድተዋል፡፡

በስድስት ክልሎች በፕሮጀክቱ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑት 50 በመቶ ሴቶችና 30 በመቶ ወንዶች እንደሚሆኑ ገልጸው፣ ለአርብቶ አደሮች ኑሮ ለማጠናከር ለግጦሽ መሬት ልማትና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ይውላል ተብሏል፡፡

እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር ለመጠጥ ውኃ አቅርቦትና አጠባበቅ የተገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር የብድር ገንዘብ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን በአገሪቱ በስፋት የሚታየውን የንፁህ የመጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግር ለመፍታትና ማኅበረሰቡን የልማቱ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብድር መሆኑን ተብራርቷል፡፡

ይህ የብድር ስምምነት አዋጅ አገሪቱ በቀጣይ ልትፈጽም ላቀደቻቸው በርካታ ተግባሮች ለአብነትም ለከርሰ ምድር ውኃ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ለፅዳት አጠባበቅ፣ እንዲሁም ለገጠር ግብርና ልማት ሥራ እንደሚውልና የውኃ ሀብት አስተዳደር አቅም ለማሳደግም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተጓደሉ የሕግ፣ የፍትሕና ዴሞክራሲ፣ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ለመመደብ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አፅድቋል፡፡ በአፈ ጉባዔው አቅራቢነት ተመስገን ባይሳ (ዶ/ር) የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ፣ እንዲሁም ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ ደግሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች