Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊያላባራው የኤድስ ተጋላጭነት

ያላባራው የኤድስ ተጋላጭነት

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

በኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በአብዛኛውም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ በሽታውም የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት ሠራተኞች ፌዴሬሽን ጥናት እንደሚጠቁመው፣ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚሰማሩ ሰዎች ለኤችአይቪ ኤድስ የመጋለጥ ዕድላቸው በሌላ ዘርፍ ተሰማርተው ለበሽታ የመጋለጥ ዕድል ካላቸው ሰዎች በሁለት ዕጥፍ ይበልጣል፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤልነህ አግደው፣ አብዛኛውን ጊዜ በቫይረሱ የሚጠቁት የከባድ፣ የሚኒባስና የቱሪስት መኪና አሽከርካሪዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሕዝብ የሚያመላልሱ መኪኖችና ከባድ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎች ለረዥም ቀናት ከቤተሰቦቻቸውና ከሴት ጓደኞቻቸው ተለይተው የሚቆዩ መሆናቸውና ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር የመተኛት ዕድለቸው ሰፊ በመሆኑ በበሽታው እንደሚያዙም አክለዋል፡፡ በግንኙነት ጊዜም አብዛኛዎቹ ኮንዶም እንደማይጠቀሙ ተገልጿል፡፡

ባቡር ጣቢያዎችና የተሽከርካሪ መናኸሪያዎች የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት መስፋፊያ ቦታዎች በመሆናቸው፣ አሽከርካሪዎችም በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመናኸሪያ አካባቢም በየጊዜው የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር ስለሚጨምር አሽከርካሪዎች በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነና በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ለዚህ በሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ ለኤድስ ተጋላጭ ከሆኑት አብዛኛዎቹም ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 39 ዓመት ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እንደሆኑና ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎችም አደንዛዥ ዕፆችን በመጠቀም በግድየለሽነት ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር በመተኛት በበሽታው እንደሚያዙም ተገልጿል፡፡

50 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪዎች አግብተው የፈቱ ወይም ደግሞ ያላገቡ ሲሆኑ፣ በኑሯቸውም መካከለኛ ገቢ ያላቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡   

አቶ አቤልነህ እንደሚሉት፣ በ2010 ዓ.ም. ከኤችአይቪ ኤድስ የመከላከል መልዕክቶችን የያዘ 6,500 የቦሎ መለጠፊያ እስቲከር፣ 23,728 ብሮሸሮችና 210 ፖስተሮች፣ 211 ኦዲዮ ቪዲዮ ሲዲዎች ተሠራጭተዋል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው የዘርፍ ሠራተኞችን በማኅበር በማደራጀትና እንዲጠናከሩ በማድረግ አራት ጊዜ ድጋፍና ክትትል ተደርጓል፡፡

በአዳማ፣ በሞጆ፣ በወሊሶና በአምቦ ከተሞች ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ የዘርፍ ሠራተኞችን በማኅበር በማደራጀት መሠራቱን በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል ባለሙያ፣ አስተባባሪና ተጠሪ በመመደብ ክትትልና ድጋፍ መደረጉን ተመልክቷል፡፡

3,150 ኮንዶሞችን ለማሠራጨት ታቅዶም፣ 4,063 ኮንዶሞች መሠራጨታቸውን በ2011 ዓ.ም. በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት 2,000 የሚሆኑ ቅጅ በኦዲዮ በማዘጋጀት ለማሠራጨት መቻሉም ተገልጿል፡፡ አምስት ቦታዎች ላይ አምስት የኮንዶም ማግኛ ለማስቀመጥና 4,626 ለማሠራጨት ታቅዶ፣ 14 የኮንዶም ማግኛ እንዲኖር በማድረግ 6,780 ኮንዶሞችን ለማሠራጨት ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እየተደገፉ ያሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ የዘርፍ ሠራተኞች በማኅበር እንዲደራጁ ሲደረግ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌና ከአዲስ አበባ በስተቀር በሌሎች የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች ኤችአይቪ ኤድስ ለመከላከል ባለሙያና ተጠሪ ተመድቦ እንደነበር ተነግሯል፡፡

በ2012 ዓ.ም.  በመስከረም ወር በሦስት ቦታዎች ሦስት የኮንዶም ማግኛ ለማስቀመጥና 566 ኮንዶሞ ለማሠራጨት ታቅዶ፣ 1,000 ኮንዶሞችን ለማሠራጨት እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በደቡብ ክልል አንድ ማኅበር ለማቋቋም የቅድመ ዝግጀት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሕክምና ባለሙያ አስተባባሪ፣ ተጠሪ ያልተመደቡ የክልል ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች ላይ ምደባ እንዲያደርጉ እየተሠራ ነው፡፡

የትራንስፖርት ዘርፍ ለኤችአይቪ ኤድስ የተጋለጠ እንዳይሆን የክልልና የከተማ መስተዳደር ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች አንድ ላይ በመሆን በተመደቡ አስተባባሪዎች የተጠናከረ አደረጃጀትና ቅንጅታዊ አሠራር በመፍጠር ቫይረሱ በዘርፉ ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ አቤልነህ ተናግረዋል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ላለባቸውም አስፈላጊውን ክትትል በማድረግና ምክር በመስጠት መሥራት እንደሚገባም አስታውሰዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚገኙ አሽከርካሪዎችም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቫይረሱ እንዳይዙ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግና በመመርመር ለጤናቸው እንክብካቤ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ አቶ አቤልነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍ የኤችአይቪ ኤድስ የሥነ ተዋልዶ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መኮንን እንዳሉት፣ በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ሚኒ ሚዲያዎችንና የፀረ ኤችአይቪ ኤድስ ክበባትን በማቋቋም ተማሪዎች የበሽታውን አስከፊነት እንዲረዱ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችም በሚማሩባቸው የትምህርት መስክ ውስጥ በሦስት የትምህርት ዓይነቶች ላይ ስለኤችአይቪ ኤድስ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማስገባት ስለኤችአይቪ ኤድስና ሥነ ተዋልዶ እንዲሁም በጤና ላይ የሚያመጡትን ችግሮች በማስተማርና በማወያየት ተደራሽ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡  በትምህርት ቤት፣ በሕክምና ቦታዎችና በሌሎች ሥፍራዎች ላይ ስለኤድስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን አጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋልም ሲሉ አሳስበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...