በዘለዓለም እሸቴ (ዶ/ር)
ተጻፈ በእምዬ ኢትዮጵያ ስም። አስተዋይ ያስተውል። ያልሠራናትን ኢትዮጵያ ስንናፍቅ ጉድ ሆነናል። የራሳችንን ድርሻ መወጣታችንን ከማየት እንጀምር። ብዙኃን ዝምተኛው ኢትዮጵያዊ (Silent Majority) ፖለቲካው ቆሻሻ ሆኖበት ቁጭ ብሎ፣ ጥቂት በፖለቲካው ያረጁና ያፈጁ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ሰውተው፣ አቡክተውና ጋግረው የሚያመጡልንን ኢትዮጵያ 50 ዓመታት ሙሉ ስናይ ኖረናል። ሁላችንም የአገራችን ነገር እየከነከነን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እነዚህ ፖለቲከኞች ጋግረው ያመጡልንን ኢትዮጵያ አልመች ብሎን፣ አንዱን ስናሞግስና ሌላውን ደግሞ ስንሰድብ ሰንብተናል። ከዓመት ዓመት ይህንኑ ስናደርግ፣ ዓይናችን እያየ ኢትዮጵያ ከኮማ ወደ ሞት ዝቅ እያለች እየሄደች ነው። ይህ አካሄድ ታሪክ ብቻ ሆኖ መቅረት አለበት። ዛሬ!
የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ተሳታፊ መሆንን ሁላችንም የውዴታ ግዴታ ማድረግ አለብን። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም በፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈን መደራጀትና ትግሉን በቃልና በሥራ መቀላቀል አሁን አሁን የግድ ነው። ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳይሆን፣ ስለኢትዮጵያ ግድ ብሎት ማውራት እንደ ነውረኛ የማያስቆጥር ባህል በኅብረተሰባችን ይፈጠር። ለኢትዮጵያ የሚሠራ በዝቶ፣ ቁጭ ባይ ወረኛ ይጠፋ ዘንድ አንዳችን ሌላኛውን እንዳደፋፍር። ፖለቲካ ኤሌክትሪክ/ቅጥፈት ነው የሚል ትርክትን አፍርሰን፣ ፖለቲካ የዜግነትና የክብር ግዴታ ነው በማለት ይተካ። ይቻላል!
አዲስ ፓርቲ መመሥረት፣ ወይም ሁሉንም ጨፍልቆ አንድ ማድረግ ጊዜው ያለፈበት ጉዳይ ነው። ሁሉም የየራሱን ፓርቲና አደረጃጀት ይዞ፣ ነገር ግን በአንድ ኢትዮጵያዊነት (ሰው መሆንና) ፍልስፍና ጥላ ሥር ግንባር ፈጥረን፣ ሁነኛ አማራጭ ሆኖ መቅረብ ለኢትዮጵያ ከሞት ማምለጫ ብቸኛ መንገድ መሆኑ ግን አሁን ላይ ፍንትው ብሎ በርቷል። ሁሉም እኔ እኔ እያለ በሚወዳደርበት ዓውድ ውስጥ፣ የሁሉም እኔነት (Ego) እንቅፋት በማይሆንበት ሁኔታ፣ በጥበብ ይህንን የአማራጭ ግንባር ሰብሳቢ እንዴት ወደ ብርሃን ማምጣት እንደምንችል እጠቁማለሁ።
ከየት እንጀምር የሚለውን ጥያቄ ለመፍታት ታስቦ የሚደረግ ጥሪ ይህ ነው። እኔነት (Ego) እንቅፋት እንዳይሆን ጅማሬውን ታናሽ ማድረግና ከዚህ በፊት አምላክ ከሠራው ታሪክ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል። “ቀጣዩ አሻጋሪ” ማን ይሁን ብለን ባለመግባባት ከምንለያይ፣ በመጀመርያ “ቲም ኢትዮጵያን” ለመውለድ እንሞክር። ከዚህ “ቲም ኢትዮጵያ” ወደ ፊት አማራጭ ግንባሩንና ሰብሳቢውን (ቀጣዩ አሻጋሪ) በጊዜ ሒደት የሚታወቁ ይሆናል። ያም “ቀጣዩ አሻጋሪ” ለአማራጭ ግንባሩ ሰብሳቢ ይሆናል ማለት ነው።
የሚቀጥለው ጥያቄ ይህ “ቲም ኢትዮጵያ” እንዴት ይወለድ የሚል ነው። አሁንም ከአንድ ሰው መጀመር ይቀላል። እያወራን እርስ በርስ ስንፈራራና ሳንተማመን መንገድ ላይ እንዳንቀር መላው ምንድነው? ጽሑፍ እየጻፍንና ጽሑፍ እያነበብን እንዲሁ ሜዳ እንዳንቀር ብልኃት ያስፈልገናል። ከምንቆራቆሰው ብሔር ውጪ የሆነና በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደ ወርቅ ተፈትኖ የነጠረ ከመካከላችን፣ ከኢሕአዴግ መንግሥት ውጪ የሆነ ማነው? እኔ ይህ ሰው ኦባንግ ሜቶ ይመስለኛል። እኔ ከኦባንግ ሜቶ ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም። ከእርሱም ጋር አልተነጋገርኩም። እኔ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በፖለቲካ ያልተሳተፍኩ፣ ለዕርቅና ለመግባባት ከመሞገት ውጪ ማንንም የማላውቅ ታናሽ ሰው ነኝ። ኦባንግ ሜቶ ከፖለቲካው ውጪ ሆኖ ስለኢትዮጵያዊነት የሚያቀነቅን እንደሆነ አያለሁ።
በተጨማሪ ደግሞ ከኦባንግ ሜቶ ብንጀምር፣ ከእርሱ የተሻለ ኢትዮጵያዊ አለ የሚል ሰው ቢኖር እንኳን ኦባንግ ሜቶ ራሱ ችቦውን ለማስተላለፍ ብቃት ያለው ሰብዕና ይኖረዋል ብዬ መገመት እመርጣለሁ። ቁምነገሩ ጊዜ የለንም። እጅግ አስቸኳይ ጉዳይ ስለሆነ ብቻ የመጣደፍ ጭንቀት እንዳለብኝ ታይቶ ስህተተኛ ከሆንኩም ይቅርታ ይደረግልኝ። ይህንን ሐሳብ በንፁህ ህሊና ተወስዶልኝ፣ ከማውራት ለመላቀቅ የተደረገ ጥረት ተደርጎ እንዲወሰድና ማስተካከያ ይሰጥበት ዘንድ አደራ እላለሁ። ብሳሳትም፣ በሞትና በሕይወት መካከል ላለችው እናት አገር ሞኝ ተደርጌ ብቆጠርም ክብር ነው እላለሁ። ታዋቂ ሰው ስላልሆንኩ፣ ይህ ሐሳብ ፍሬ የሚያፈራው በተዓምር ፈጣሪ እጁን ጣልቃ ካገባበት ብቻ ነው።
የመጀመርያውን አሻጋሪ ለቀቅ ቀጣዩን አሻጋሪ ጠበቅ
ሚስጥሩ ሁለት አሻጋሪ እንደሚያስፈልገን ማስተዋል ነው። ነፃ አውጭ ሙሴው ዶ/ር ዓብይ ከባርነት ቀንበር የ“ኤርትራን ባህር” አሻግሮ ጥሪውን በዴሞክራሲ አዋላጅነት ለማጠናቀቅ ሲጥር፣ እኛ በምድረ በዳ እንዳንቀር የ“ዮርዳኖስን ባህር” አሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ኢትዮጵያዊነት ምድር የሚያስገባን፣ ከዶ/ር ዓብይ ትይዮ የሚሠለፍና አማራጭ ግንባሩን የሚመራ “ኢያሱ” እንዲወጣ ሁላችንም አንድ ልብ እንዲሰጠን ፀሎቴ ነው። እግዚአብሔር ዓብይን ለኢትዮጵያ ሰጠ። አሁን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሆነው ቀጣዩ አሻጋሪ እንዲገለጽ መተባበር መቻል ነው። ዓብይን የሚያምነው ሰው እውነት ዓብይን ከወደደ ለ“ቀጣዩ አሻጋሪ” መገለጥ ይሥራና ዓብይ የሚወዳትን ኢትዮጵያን ይርዳ።
ዓብይን የሚጠረጥረው ሰው እውነት ኢትዮጵያን ከወደደ ለ“ቀጣዩ አሻጋሪ” መገለጥ ይሥራና የሚወዳትን ኢትዮጵያን ይርዳ። ዶ/ር ዓብይ ላይ ብቻ ተጠምዶ ሰው ቁጭ ካለ፣ በምድረ በዳ አልቆ፣ የእስራኤልን ታሪክ ዳግመኛ በራሳችን ላይ እንዳንደግም እንፍራ! አሁን አሁን ዶ/ር ዓብይን መደገፍም ሆን መቃወም አይጠቅማቸውም። አይጠቅመንምም። ይልቁንስ እንልቀቃቸውና በራሳችን ሥራ እንጠመድ። ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጉልበት አግኝተው በበጎነት ይገለጻሉ እንጂ ክፉ ሆነው ክፉ አያደርጉም።
ዶ/ር ዓብይ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለው ምንም እንከን በእሳቸው ላይ ላለመመዝገብ የተገዘቱ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር ዓብይ አስመሳይና መሰሪ ናቸው ብለው የሚምሉና ፍርድ ቤት የቀረቡ ይመስል የማስረጃ ትንታኔ ላይ ተጠምደው ጊዜያቸውን ያቃጥላሉ። የተለመደው የፖለቲካ ጥበባችን የሚመክረን እውነታዎች በሁለቱ አካሄድ በኩል እየፈረጀን እስከ መቼ እንደሚሸውደን አላውቅም። ብናስተውል በዚህ ሰሞን የተከሰተው የጃዋር ግርግር ለኢትዮጵያ ታላቅ ሐዘን ቢያስከትልም የፈሰሰው ደም ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ከፈለግን፣ ከዚህ ሰቅጣጭ ሐዘን ውስጥ በሁለት ጎራ ተከፍለን የምንሞግት ዶ/ር ዓብይ ተኮር ዜጎች (ተቃዋሚና ደጋፊ) ዶክተሩን ለቀቅ አድርገንና በኅብረት ሆነን ለአንድ ዓላማ ወደ ሥራ እንግባ እላለሁ።
ኢትዮጵያዊነት ስለተሰበከ አገር ሁሉ በፍቅርና በተስፋ እንደተነቃነቀ አምና ዓይተናል። ግን ምን ያደርጋል ከተበታተነ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ይልቅ፣ በወደቀ ራዕይና ዓላማ አንድነትን የፈጠረ ድርጅት የበለጠ ኃይል ኖሮት ለእርስ በርስ ዕርድ እያዘጋጀን ይገኛል። ግና! በሺዎች ዓመታት እንደ አልማዝ ተፈትኖ ነጥሮ የወጣው ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ራዕይ ጥላ ሥር ተሰባስበን፣ አንድ ሁነኛ አማራጭ ግንባር የምንፈጥርበት ቀን ደርሷል። ኢሕአዴግ የተለያየ ፓርቲዎችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠፍሮና ግንባር ፈጥሮ ለ27 ዓመታት ሲነግሥ ዓይተን ስናበቃ፣ ዛሬ ደግሞ ይህ ኢሕአዴግ የተለያየ ፓርቲዎችን በመደመር ንግግር ጠፍሮና ግንባር (ውህደት) ፈጥሮ ሌላ 27 ዓመታት ሊገዛ ሲደራጅ፣ በትንንሽ ራዕይና በተበታተነ ፓርቲዎች እርስ በርስ ፉክቻ መዳከር ሊያበቃ ነው። ዝምተኛው ብዙኃን ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ዓብይን በመደገፍና በመቃወም እየተዋከበ፣ የኢትዮጵያን ትንሳዔ በምትሃት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ሊቀር ነው እንግዲህ።
ሌላው ቀርቶ ኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች እያለ ለዘመናት የሚያላግጥባቸው ዛሬ ዛሬ ሊያቅፋቸው ላይ ታች ሲል፣ ይህ አማራጭ ግንባር ዕውን ሆኖ እነዚህ የተገፉ ሕዝቦች ለአባልነት ይጋበዛሉ። አሮጌ ነገር እያረጉ አዲስ ነገር መጠበቅ የሰለቸን ጊዜ ላይ ደርሰናልና እንንቃ! ዶ/ር ዓብይን የሽግግር መንግሥት ምናምን እያልን በመግለጫና በጥያቄ ከምናዋክባቸው፣ እሳቸውን ለቀቅ አድርገን እኛ “የሽግግር” አማራጭ ግንባር ለውድድር እንዲቀርብ የምንፈጥርበት ወቅት ይሁን። ኢሕአዴግ በፌዴራሊዝም አግባብ ሲጣሉ፣ እኛ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተገነባውንና ፍፁምነት ጭምር የተላበሰውን “ኢትዮጵያዊ ፌዴራሊዝምን” እናስተዋውቃለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲህና እንዲህ አድርጉ እያልን አዳዲስ ሐሳቦችን እንዲቀበሉን መወትወት ትተን፣ እነዚያን አዳዲስ ሐሳቦች በራሳችን ላይ አውለን አማራጭ ግንባር ሆነን እንገለጻለን።
ህርማችንን አውጥተን ሀቁን እንቀበል
እስቲ አገራችንን ከማየት እንጀምር። አገራችን ጃንሆይ ያስራቧት፣ ደርግ ያቆሰላትና ኢሕአዴግ ኮማ ውስጥ የከተታት እምዬ ናት። ጠላቶቿ ግባተ መሬቷን ከአሁን አሁን አየን እያሉ ቢጠብቁም፣ ፈጣሪ ከእሷ ጋር ጉዳይ አለውና ይኼው ኢትዮጵያ እየተባለች ስሟ ከመጠራት እስካሁን አልቀረም። ምድረ በዳ ሆና ባንዲራዋ በሰማይ የሚታይ ሆናለች። ሰው የዶ/ር ዓብይን ልብ ለማወቅ ይመራመራል። የትኛውም ልብ ይኑራቸው አሁን በኮማ ያለችውን ኢትዮጵያ ነፍስ ሊዘሩ አይችሉም። ይመስለናል እንጂ ማንም አይችልም። ወደድንም ጠላን ኢትዮጵያ በሰው እጅ ሥራ እንዳትንሰራራ ተደርጎ በኮማ ውስጥ እንድትገባ ተደርጋለች። ህርማችንን እናውጣና ይህን ሀቅ ማለትም በሰው እንደማይቻል እንቀበል። ምክንያቱም ያሳለፍነው ጉድ ከሰውነት አውጥቶን እንደ ባለ አዕምሮ ማሰብ እንዳንችል አድርጎናል።
አገሪቱን የሚዘውሩት ልሂቃን ተብዬዎች ሁሉ፣ ሁሌም ጥል ላይ ያለንና ሁከት ውስጥ የምንዋኝ ያልታወቀልን “ዕብዶች” ነን። በደመነፍስ የምንመላለስ ሆነናል። መርገም ይዘን በረከት እንዲወርድልን ስንባዝን ከርመናል። ንፁህና ትልቅ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኛ ዳተኝነት ታግቶ፣ መጨረሻዬ ምን ይሆን ብሎ ጉዳታችንን ከማየት ያለፈ ነገር ማድረግ እንዳይችል ሆኖ በሥጋት ተቀምጧል።
ልብ እንግዛና የኢትዮጵያን አምላክ ከማየት እንጀምር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋው ፈጣሪ እንደሆነ ዕሙን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰብ እንደሆነ እውነት ነው። ነገር ግን ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘውሩት አምላክን ዜሮ እንዳደረጉት የአደባባይ ሚስጥር ነው። በእጃቸው ያለው ደምና በልባቸው ያለው መከፋፋት አምላክን ለረድኤቱ እንዳይጠሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ያለፈውን በደልና ቁርሾ ማውራትና በቁስል ላይ እንጨት መስደድ እንጂ፣ በአምላክ ፍቅርና ረድኤት በይቅርታ ያለፈውን ፋይል ዘግቶ መፈወስ እንዳለ አይታሰብም። የጎሳውን ወገን “ወንድማችን” ይላል እንጂ፣ መላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ እንደሆነ ዘንግቶ በወንድማማቾች መካከል ፀብ መዝራት ፋሽን ነው። እርግማን ተይዞ በረከት መጠበቅ ሞኝነት ነው። የበረከት ምንጭ የሆነው አምላክ ተንቆና ገሸሽ ተደርጎ፣ መድኃኒት እንዲመጣ መልፋት ባዶነት ነው።
እንዲሳካልንና ምድራችን የተዓምር ምድር እንድትሆን ከፈለግን፣ እኛ ከቁጥር የማናስገባውን የኢትዮጵያ አምላክ ሕዝቡ ታምኖበታልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘወትር እንደሚያደርገው ሁሉ፣ እኛም ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ያስፈልገናል። ለሰው የማይቻል ለፈጣሪ ይቻላልና። ሁላችንም በመመለስ የኢትዮጵያን አምላክ የኢትዮጵያ ንጉሥ እንዲሆን በአደባባይ ለሁሉ እናውጅ። ያኔ ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች’ የሚለው ትንቢት እውነት ይሆናል። የአሜሪካ አባቶች እግዚአብሔር ላይ ተደግፈው የእግዚአብሔርን ስም በዶላራቸው፣ በሳንቲሞቻቸውና በብሔራዊ ስሜታቸው ውስጥ አስገብተው ፈጣሪን ሲያከብሩ፣ እነሆ የዓለም ንጉሥ ሆነው አረፉት። የሚያሳዝነው ፈሪኃ እግዚአብሔር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መሪዎቹ በፈጣሪ የሚያፍሩ መሆናቸው ነው። የፈጣሪ በረከትና ረድኤት እንዲደርሰን የፖለቲካ መሪዎቻችን ራሳቸውን ከማማው ላይ አውርደው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታመንበትን ፈጣሪ ከፍ እንዲል ያድርጉ። አምላክን በንግግር መጨረሻ ላይ ጣል የምናደርገው ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ እንዲሆን በኅብረት የምንፈጥረው ግንባር የአምላክን ረድኤት እንደ ዋና መሪ ቃል ማስቀመጥ አለበት።
አምላክን የምንማፀነው የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ሳይሆን (ሃይማኖት የግል ነው)፣ ያለ ፈጣሪ ረድኤት የኢትዮጵያ ትንሳዔ ፍፁም በሰው ኃይል እንደማይሳካ ከልብ ስለገባን መሆን አለበት። ይህ ድርጊት ደግሞ መድኃኒትነቱ በእኛ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ለምሳሌ በመሪ ቃላችን “ፈጣሪ ኢትዮጵያን አስባት” ብለን ብንነሳ፣ አምላክ ይህንን ለምልክት አድርጎት የሚባርከን እኛን ብቻ ሳይሆን፣ እኛን ለዓለም በረከት በማድረግ ምድርን ሁሉ በክብሩ ይሞላል።
በቸልተኝነት አይለፍብን፣ ይልቁንስ ጊዜውን ከማየት እንጀምር። በአብዮት ትርምስ ውስጥ የነበረ ትውልድ በሞት አልቆ አዲስ ትውልድ ሊመጣ ያለበት አፋፍ ላይ ደርሰናል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የጃንሆይ ጊዜ ግርግርን የሚያውቅ ሰው በሕይወት የሌለበት ዘመን ሩቅ አይደለም። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ስለነበረው ቀውስ ሒሳቡን በይቅርታ ዘግተን፣ አዲሱን ትውልድ መክረንና መርቀን፣ የኢትዮጵያን አይቀሬ ታላቅነት በጭላንጭል ዓይተን፣ ወደ ማንመለስበት ሞት ኢትዮጵያን ተሰናብተን በዕፎይታ እንድንሄድ ፈጣሪ ምሕረት እንዳደረገልን ስለጊዜው ምንነት ማወቅ ተስፋ ሰጪ ነው።
ጊዜው በጠላታችን ሴራ ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ቀጠሮ የተያዘበት ብቻ ሳይሆን፣ በይበልጥ ጊዜው ለውድ እናት አገራችን ልዩ የመዳን ቀን ለመሆኑ ምልክቱ ብዙ ነው። አብዮት ሳይፈነዳ በለውጥ ጉዞ ላይ መሆናችን መለኮታዊ እጅ እንዳለበት የሚጠራጠር፣ ለውጡን እኔ በአመፅ አመጣሁት ብሎ የሚፎክርና ፊት ፊቱን ብቻ የሚያይ ፍጡር ነው። በመጀመርያ አካባቢ ሕዝብን በተስፋና በደስታ ፍንጣቂ ኢትዮጵያዊነትን ቦግ ብሎ እንዲበራ ያንተገተገው የዶ/ር ዓብይ ሰብዕና ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ፣ የማይታየውን የመለኮት እጅ የማያገናዝብ ሰው ነው። በመጨረሻ የአገሬው ሰዎች የሆንን ስንቀዘቅዝ በዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ያስታቀፋቸው፣ ይህ ስኬት ስለዶ/ር የሚናገር ብቻ ሳይሆን መለኮት “አስተውሉ! ጊዜውን!” እያለን ለመሆኑ ማወቅ የሚሳነው የማያስተውል ሰው ብቻ ነው።
በአጭሩ የነገሩ ድምዳሜ ይህ ነው፡፡ ያም ጊዜው በማያሻማ ሁኔታ የኢትዮጵያ ነው። የምንተኛ እንንቃ! የስብራታችንን ጥልቀት ላስተዋለው፣ የጨለማውን ድቅድቅነት ለተመለከተው፣ ሊነጋ እንዳቅላላ እርግጠኛ መሆን ይችላል።
ከቅዱስ ቃሉ የተወሰደ
- የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፡፡
- አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፣ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።
- ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡