Tuesday, October 3, 2023

ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥትን በአወያይነት ማስገባት ለምን ፈለገች?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የጀመረችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በመቃወም፣ በኋላም ተቃውሞዋንና ሥጋቷን ከውይይትና ከድርድር በተጨማሪ ለስምንት ዓመታት የፈጀ ፈርጀ ብዙ ትግሎች አድርጋለች፡፡

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በ2003 ዓ.ም. ሲጀመር በወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት መሐመድ ሙርሲ የግብፅን የውኃ ድርሻ ማንኛውም የዓባይ ወንዝ ተጋሪ አገር መንካት እንደማይችል፣ ይህንን የተላለፈ አገር ቢኖር ግብፅ ጥቅሟን ለማስከበር እስከ ጦርነት ልትሄድ እንደምትችል የሚገልጽ ውይይት ከአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልሂቃን ጋር ማድረጋቸውና ይህም በወቅቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት መተላለፉ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሳይረበሽ የጀመረውን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ግዙፍ እንደሚሆን የሚጠበቀውን የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በማጧጧፍ በመቀጠል፣ በዓመት ጊዜ ውስጥ የዓባይ ወንዝ ተፍጥሯዊ መፍሰሻን ለግንባታው ሲባል ወደ ሰው ሠራሽ ቦይ መቀየሱ በግብፅ ላይ ከፍተኛ መደናገጥን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህ የግብፅ ድንጋጤ ኢትዮጵያ ግድቡን ከመገንባት እንደማትመለስ ያሳየ ነበር፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው ግብፅ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ግድቡ የግብፅን የውኃ ድርሻ እንዳይጎዳ ለማድረግ የተሻለው አማራጭ፣ ቀርቦ መነጋገር እንደሆነ ያሳመነና ወደ ውይይት ጠረጴዛ ያመጣ ወሳኝ ሁነት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ከዚህ በኋላ ነው የህዳሴ ግድቡ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በሆኑት ግብፅና ሱዳን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖና ጉዳትን የተመለከተ ውይይት፣ በሦስቱ አገሮች መካከል ቅርፅ ይዞ መካሄድ የጀመረው፡፡

የመጀመሪያው ሒደትም በኢትዮጵያ መንግሥት ሐሳብ አቅራቢነት ግብፅ ላይ የተፈጠረውን ሥጋት ለመቅረፍ እንዲቻል ገለልተኛ የሆኑ ዓለም አቀፍ የውኃ ጉዳይ ባለሙያዎች የሚመራና የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ባለሙያዎች የሚወከሉበት (ኢንተርናሽናል ፓናል ኦፍ ኤክስፐርትስ) ቡድን በግድቡ ላይ ጥናት በማካሄድ፣ ሊኖረው የሚችል ተፅዕኖ ካለ በመለየት ለሦስቱም አገሮች ሪፖርት እንዲያቀርብ ተደርጓል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን አንድ ዓመት የፈጀ ጥናት አካሂዶ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የታችኛው ተፋሰስ በሆኑት ግብፅና በሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት እንደሌለው አረጋግጧል፡፡ በሦስቱ አገሮች መካከል መተማመንን ለመፍጠር እንዲረዳ ግን የግድቡ ውኃ አያያዝና አለቃቀቅ፣ እንዲሁም የግድቡ ግንባታ ሊያደርስ የሚችለው ማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ በሦስቱ አገሮች በጋራ እንዲጠና ሲል ሁለት ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎም ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን እኩል በሚወጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች (ናሽናል ቴክኒካል ኮሚቴ)፣ ከላይ የተገለጹትን ምክረ ሐሳቦች ለማጥናት በመስማማት ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አራት ዓመታት የፈጁ 19 ውይይቶችን አካሂዷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተካሄዱት ውይይቶች ሲቋረጡ፣ እንደገና በሦስቱ አገሮች የፖለቲካ መሪዎች ጣልቃ ገብነት እንዲቀጥሉ ሲደረግ ዓመታት ቢያልፉም ስምምነት ላይ ግን መድረስ አልተቻልም፡፡ በዚህ መካከል ጣልቃ የገቡት የሦስቱ አገሮች መሪዎች እ.ኤ.አ. በ2015 የህዳሴ ግድቡን የተመለከተ የትብብር መርህ ማዕቀፍ (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) በሱዳን ከተማ ተፈራመዋል፡፡

ይህ ስምምነት የህዳሴ ግድቡን ግንባታ፣ የውኃ አሞላልና ኦፕሬሽን በተመለከተ የሦስቱ አገሮች መሪዎች ስምምነት ያረፈበት ገዥ መርሆዎችን የያዘ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ግብፅ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት እንዳላት ተቀበላ የፈረመችበት ሰነድ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና በተለይም በዓባይ ውኃ የፖለቲካ ጉዳዮች ምርምር የሚታወቁት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፣ የትብብር መርህ ማዕቀፉን ግብፅ ለመፈረም የተገደደችው ፈልጋ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡

የትብብር መርህ ማዕቀፉ ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶች አስተዳደርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በዓባይ ውኃ ዓውድ ውስጥ በማስገባት የተቀረፀ በመሆኑ፣ ግብፅ ይህንን ስምምነት መቀበሏ የግድ እንደነበር ገልጸው፣ ይህም የሆነው ለይስሙላ እንጂ ግብፅ አምናበት የተቀበለችው አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የግብፅ መንግሥት አቋም ትናንትም ሆነ ዛሬ አንድና አንድ ስለመሆኑ የሚናገሩት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ “ይኸውም ነባር የውኃ ድርሻዬ አይነካም፤” እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ የሲቪል ሥራዎች ግንባታ እ.ኤ.አ. በ2019 ከ80 በመቶ በላይ መፈጸሙን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የህዳሴው ግድብ አካል ሆነው በቅድሚያ የተተከሉትን ሁለት ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2020 ሥራ ለማስጀመር በመጪው ክረምት በግድቡ ውኃ ማቆር እንደምትጀምር ማስታወቁን ተከትሎ፣ የግብፅ መንግሥት የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ይመክሩበት የነበረውን የውይይት አጀንዳ በመዝለል የግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቅን በተመለከተ በተናጠል ያሰናዳውን ምክረ ሐሳብ ባለፈው መስከረም ውር ላይ ለውይይት አቅርቧል፡፡

ግብፅ በተናጠል ባቀረበችው ሰነድ ከተመለከቱትና በኢትዮጵያ መንግሥት በእጅጉ ከተተቹት ነጥቦች ዋነኛው፣ “የግድቡ የውኃ ሙሌት በሰባት ዓመታት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንድትለቅ፣ የህዳሴ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ ዝቅተኛ የውኃ ይዞታ የግድቡ 165 ሜትር መሆኑን ማረጋገጥና የአስዋን የውኃ መጠን በዚህ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ከያዘችው ውኃ ላይ መልቀቅ እንደሚኖርባት የሚጠይቅ ነው፤” የሚለው ተጠቃሽ ነው::

በተጨማሪም የህዳሴ ግድቡ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በግብፅና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች በጋራ እንዲመራ፣ ይህንንም የሚከታተል ቢሮ በኢትዮጵያ እንዲከፈት የሚጠይቅ ሐሳብ ይገኝበታል፡፡

ኢትዮጵያ በግብፅ በኩል የቀረበውን የተናጠል ምክረ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገችው ቢሆንም፣ የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉዳዩ ላይ ተወያይተው የኢትዮጵያና የሱዳን ሐሳብ ቀርቦ ውይይት እንዲካሄድበት በመግባባት ውይይቱ ቢቀጥልም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ተደራዳሪ፣ በግብፅ በኩል የቀረበው ሐሳብ በምንም ሁኔታ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን የግብፅ ምክረ ሐሳብ ተቀበለች ማለት ግድቡን በውኃ ለመሙላት አትችልም ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የግብፅ ምክረ ሐሳብ አንድምታ ወደ ግብፅ የሚፈሰው የውኃ መጠን ፈፅሞ መቀነስ አይችልም ማለት እንደሆነ፣ ይህንን ነጠላ ሐሳብ በማስቀረት ሌሎቹን ምክረ ሐሳቦች መቀበልም ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ለመሙላት ከ16 እስከ 30 ዓመታት እንደሚፈጅባት ያስረዳሉ፡፡ ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ተቀባይነት እንዳጣ የተረዳችው ግብፅ፣ ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት እንዲገባ ጥያቄና አቤቱታዋን አስተጋብታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ መንግሥት በሦስተኛ ወገን አወያይነት እንዲገባ በተናጠል ጥሪ አቅርባለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በህዳሴ ግድቡ ላይ ከግብፅ ጋር በቀጥታም ሆነ ሦስተኛ ወገን ባለበት የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ ችግር እንደሌለበት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎም የአሜሪካ መንግሥት የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በዚህ ሳምንት ወደ አሜሪካ በመጥራት ማወያየት ይጀምራል፡፡ ግብፅ የአሜሪካ መንግሥትን በአወያይነት የመምረጧ ምክንያት ምንድነው? እንዲሁም በዚህ ውይይት ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት ሚና ምን ይሆናል? የሚሉት ጥያቄዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የቤት ሥራ ይሆናሉ፡፡

አሜሪካ አደራዳሪ ናት?

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሪፖርተር በላከው ማብራሪያ በህዳሴ ግድቡ ላይ ሦስቱ አገሮች በአሜሪካ የሚያደርጉት ውይይት መሆኑን፣ የአሜሪካ መንግሥት ሚናም መድረኩን በማመቻቸት ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ማመቻቸት መሆኑን አመልክቷል፡፡

“ድርድር የሚካሄደው በአንድ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ላይ የሚገኙ ወገኖች ቀጣይ ውይይት ማድረግ ሳይችሉ በመረጡት በሌላ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ለመወያየት በሚስማሙበት ጊዜ መሆኑን ያብራራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ፣ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ሲገናኙ ሐሳባቸውን በማቅረብ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራሉ እንጂ ድርድር አያካሂዱም፤” ብሏል።

የሱዳን፣ የኢትዮጵያና የግብፅ ብሔራዊ የባለሙያዎቸ ቡድን በደረሱት ስምምነት መሠረት ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ የቴክኒክ ውይይታቸውን እያካሄዱ መሆኑን፣ የግድቡ ውኃ አሞላልን በተመለከተ ያለው ልዩነት በሦስቱ አገሮች መካከል የቴክኒክ ቡድኖች እንደሚፈታም አስረድቷል፡፡

ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) የአሜሪካ መንግሥት በሦስቱ አገሮች መካከል ያለው ልዩነት በውይይት እንዲፈታ፣ እንደ ወዳጅ መንግሥት የውይይት መድረክ አመቻች እንጂ የአደራደሪነት ሚና የለውም ብለዋል፡፡

ሌላ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ በበኩላቸው፣ እስካሁን የአሜሪካ መንግሥት ሚናን አስመልክቶ የሚታወቀው አወያይነት እንደሆነ፣ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ስላለመቀየሩ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ግብፅ አሜሪካን ለምን ፈለገች?

ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ሥጋት ለመቅረፍ በሦስተኛ ወገን አወያይነት የአሜሪካ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በተናጠል ጥሪ ማድረጓን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግሥት በማዕከላዊ ባንክ ኃላፊ (ትሬዠሪ ሴክሬታሪ) በኩል ለሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥሪ አድርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ የገቡ ሲሆን፣ ከረቡዕ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.  ጀምሮም ውይይት እንደሚጀምሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ውይይቱ ከመጀመሩ ከሁለት ቀናት በፊትም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከግብፅ አቻቸው ጋር ውይይቱን በተመለከተ በስልክ መነጋገራቸውን፣ የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ቢሮ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡ ይህንን ተከትሎም የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሉ አለመግባባቶች ግብፅን በሚጠቅም መንገድ እንዲፈቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያደርጋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕን በሚያሞግሱ ቃላት ከሽነው ስለመናገራቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የሦስቱ አገሮች ተወያዮች በዋይት ሀውስ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ቅድመ ውይይት እንደሚያደርጉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ተሳታፊ እንዲሆኑ አሜሪካ ጥሪ ያቀረበች መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ የዓለም ባንክ የሚኖረው ሚና ግን በግልጽ አልታወቀም፡፡

ግብፅ በዚህ ውይይት የአሜሪካን ሚና የፈለገችው ለምን ሊሆን እንደሚችል፣ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ ያስረዳሉ፡፡

 አንደኛው ምክንያት አሜሪካ በዓለም ያላት የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና መሆኑን የሚያስረዱት ተደራዳሪው፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ለአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ፍላጎት ስትራጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቢሆንም አስፈላጊነታቸው በደረጃ ቢቀመጥ ግን የተለያየ መሆኑንም በማያያዝ ያነሳሉ፡፡

ለአብነትም በአንድ ዓመት ውስጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕና ፕሬዚዳንት አልሲሲ አራት ጊዜ ሲገናኙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግን ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር አንድም ጊዜ አለመገናኘታቸውን በመጠቆም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ያሳያሉ፡፡

በሌላ በኩል አሁን የተጠራው ውይይት ከመጀመሩ ከቀናት በፊት ፕሬዚዳንት ትራምፕና አልሲሲ ውይይቱን አስመልክቶ በስልክ መነጋገራቸው፣ ከውይይቱ አስቀድሞም የሦስቱ አገሮች ተወያዮች ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ግብፅ ምን ያህል ቅርበት እንዳላት ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በሁለተኛ ምክንያትነት የሚያነሱት መሠረታዊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይኸውም የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በመባል የሚታወቀውን በእስራኤልና በግብፅ መካከል እ.ኤ.አ በ1978 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ነው፡፡

በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር አደራዳሪነት በግብፅና በእስራኤል መካከል ለ30 ዓመታት የቆየውን ጥል በዕርቅ ለመፍታት የተደረገው ስምምነት፣ ሌሎች ሚስጥራዊ የጎንዮሽ ስምምነቶችም እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

ይኸውም በአሜሪካና በግብፅ መካከል የተደረጉ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ስምምነቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስምምነቶች መካከል ወታደራዊ ስምምነቱ አሜሪካ በግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከሌሎች የባህረ ሰላጤው አገሮች የሚነሳ ሥጋትን፣ እንዲሁም ከዓባይ ውኃ ተጋሪ አገሮች የሚመጣ ሥጋትን ለመቀልበስ ያደረጉት የትብብር ስምምነት ተጠቃሽ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ የተገለጹትን ሥጋቶች ለመቀልበስ እንዲቻላት፣ አሜሪካ የግብፅን ወታደራዊ አቅም በመሣሪያና በሥልጠና ለመገንባት ያደረገችው ስምምነት እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ዘወትር የሚያስጨንቃት አሜሪካ፣ ግብፅን ከዓባይ ውኃ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ማንኛውም ዓይነት ሥጋት ለመጠበቅ ስምምነት መግባቷ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይን በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ለመፍታት ያስችለኛል ብላ የመረጠችው መንገድ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

አሜሪካ ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉትን ውይይት ከማመቻቻት ባለፈ የዓለም ባንክ በውይይቱ ተሳታፊ እንዲሆን ያደረገችውም፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚነሱ መከራከሪያዎችን በዓለም ባንክ በኩል ለመግደል አስባ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ የህዳሴ ግድቡ በተራዘመ ዓመት እንዲሞላ የምታነሳውን ጥያቄ ኢትዮጵያ ጥቅሟን እንደሚጎዳ በመግለጽ ውድቅ ስታደርግ እንደቆየች የሚያስታውሱት ተደራዳሪው፣ ኢትዮጵያ የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮችን ሳትጎዳ ግድቡን በስድስት ዓመታት ለመሙላት እንደምትፈልግ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከግድቡ መጠቀም ካልቻለች ግን በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታጣ ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ የዓለም ባንክን በውይይቱ እንዲሳተፍ ያደርገችው ይህን መሰል መከራከሪያ ቢነሳ ጉዳቱ በዓለም ባንክ በኩል እንደሚካስ መተማመኛ በመስጠት፣ ጉዳዩን ለመግደል ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

 “በኢትዮጵያ ተወያዮች በኩል መደረግ ያለበት ምንም ዓይነት ስምምነት ሳያደርጉ የሚነሱ አማራጮችን በመንግሥት ደረጃ መክረንበት እናሳውቃለን በማለት ማለፍ፤” ነው ሲሉ ይመክራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሊመጣ ከሚችል አጣብቂኝ ለመውጣት ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ ሊሆን እንዲሚገባ ይገልጻሉ፡፡

የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የራሱን ፍለጎት እንጂ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን የማይመለከት መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግና በዚህ መንገድም ነገሩ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -