Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለባለአምስት ኮከብነት የታሰበው አገር በቀሉ ግራንድ ኤሊያና ሆቴል አራት ኮከብ አግኝቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሆቴል የደረጃ ምደባ ከ340 በላይ ሆቴሎች ከአንድ እስከ አምስት ኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ዓመትም አዲስ የተሠሩትን ጨምሮ የመጀመሪያውን ደረጃ ያገኙ ሆቴሎች በሙሉ ሁለተኛ ዙር ዳግም የደረጃ ምደባ እንደሚካሄድባቸው ይጠበቃል፡፡

አዳዲስ ከተሠሩና ከተከፈቱ የአገር ውስጥና የውጭ ሆቴሎች መካከል ለሁለት ዓመት ተኩል የማጠናቀቂያ ግንባታ ሲያካሂድ የቆየው ግራንድ ኤሊያና ሆቴል (ኮንፈረንስ ኤንድ ስፓ) ከአገር በቀል ሆቴሎች አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ የማስፋፊያ ግንባታቸውን በማከናወን የደረጃ ምደባ ከወጣላቸው መካከል ሃያት ሬጀንሲ ሆቴልና ግራንድ ኤሊያና ሆቴል ደረጃ ማግኘታቸው ተዘግቧል፡፡ በዚሁ መሠረት ሃያት ሬጀንሲ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ሲያገኝ፣ ግራንድ ኤሊያና ባለአራት ኮከብ ሆቴል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ለሆቴሎቹ የምሥክር ወረቀት መስጠቱን አረጋግጧል፡፡

በሚኒስቴሩ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለተቋማቱ የተሰጣቸውን ደረጃ የሚያረጋግጥ የምሥክር ወረቀት ተልኮላቸዋል፡፡ ስላገኙት ደረጃ ዝርዝር ውጤት የሚገልጽ ሪፖርት እንደሚላክላቸውም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የባለአምስት ኮከብ ደረጃ ይጠብቅ የነበረውና ለዚሁ ደረጃ የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶችንና የማስፋፊያ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ የሚነገርለት ግራንድ ኤሊያና ሆቴል፣ በ82 መኝታ ክፍሎች፣ ከ500 ያላነሱ ተመልካቾችን የሚያተስናግዱ ሁለት ሲኒማ ቤቶች፣ እስከ 2000 ተሰብሳቢዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽን ጨምሮ 12 አነስተኛና መካከለኛ የስብሰባ አዳራሾችን፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች መዋኛ ገንዳዎችን አካቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ መንፈቅ አስቆጥሯል፡፡ ሆቴሉ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ እንደሚያገኝ ታስቦ እንደተገነባ ሲነገር፣ ለዚሁ ደረጃ ከሚያበቁትና ከላይ ከተዘረዘሩት መጠይቆች በተጨማሪ የስፖርት፣ የሳውናና ስቲም፣ የጃኩዚ፣ የሬስቶራንት አገልግሎቶችንና ባለሦስት ፎቅ የመኪና ማቆሚያ ከማሟላት ባሻገር፣ ሆቴሉ ከሚገኝበት ከፒያሳ አካባቢ የሚገኙ ቅርሶችን፣ ለመርካቶም ሆነ ለቦሌ ካለው ቅርበት፣ ለቱሪስቶች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚችልበት ዋና ቦታ ላይ መገንባቱ ለደረጃ ብቁ ከሚያደርጉት መካከል እንደሚጠቀሱለት ይነገራል፡፡

በአራት ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ፣ 3,300 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ግራንድ ኤሊያና ሆቴል፣ በሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ መስፈርት ሥር የተቀመጡ መጠይቆችን እንዳሟላና ይጠብቅ የነበረውም አምስት ኮከብ እንደነበር ለሆቴሉ ባለንብረቶች ቅርበት ያላቸው አካላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሆቴሉ ባለቤቶች ስለጉዳዩ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሆቴሉ በተሰጠው ደረጃ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግና ዳግም እንዲታይላቸው ሊጠይቁ እንደሚችሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ግራንድ ኤሊያና፣ ከዚህ ቀደም በግብይት ማዕከልነት የተወሰነውን አገልግሎት ወደ ሁለገብ የሆቴል አገልግሎት ማዕከልነት በማስፋፋት፣ በርካታ የገበያ ማዕከላትን፣ የመድን ኩባንያዎችንና ሌሎችንም ያካተቱ ባለ12 ፎቅ የሆቴልና ባለአራት ፎቅ የገበያ ማዕከል ሕንፃዎችን አጣምሮ የያዘ ሁለገብ ሆቴል ነው፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት አሥር ያህል የውጭና አገር በቀል ሆቴሎች ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ ሸራተን አዲስን ጨምሮ፣ ሃያት ሬጀንሲ፣ ካፒታል ሆቴል፣ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል፣ ኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ፣ ማሪዮት ኤግዚኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴል፣ ጎልደን ቱሊፕ፣ ራዲሰን ብሉ ባለአምስት ኮከብ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ሃያት ሬጀንሲ ከ13 ዓመታት በላይ ግንባታው ሲጓተት ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በ188 ክፍሎች አገልግሎት መስጠት የጀመረና 25 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የጠየቀ ሆቴል ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡ እነዚህ ጨምሮ አዳዲስ የመጡትንና ከአራት ዓመታት በፊት ደረጃ የተሰጣቸው ደረጃ ዳግም ምዘና በዚህ ዓመት እንደሚካሄድበት ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች