[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ ነው]
- ምነው ተከዝክ?
- እንዴት አልተክዝ?
- ቡናህ እኮ ቀዘቀዘ፡፡
- እዚህ አገር ምን ያልቀዘቀዘ ነገር አለ?
- ቁርሱም እኮ እየቀዘቀዘብህ ነው ብላ እንጂ?
- ባክሽ ዘግቶኛል፡፡
- መቼም ጉሮሮህን ወጣቶቹ አላገኙትም?
- የትኞቹ ወጣቶች?
- መንገድ የሚዘጉት ናቸዋ፡፡
- ተይኝ እስቲ ባክሽ?
- ምነው?
- ሁሉም ነገር እኮ ግራ ያጋባል፡፡
- እንዴት?
- አንዱን ስትይው አንዱ እያለ መከራችንን በላን፡፡
- ብዙ አትጨነቅ ባክህ?
- እንዴት አልጨነቅ?
- ማለቴ ሁሉም ከልኩ አያልፍም ብዬ ነዋ፡፡
- እየቀለድሽ ነው?
- የምን ቀልድ ነው?
- ታዲያ አገር እንዲህ ተወጣጥራ እያየሽ ከልኩ አያልፍም ስትይኝ ነዋ?
- ምን ላድርግ ታዲያ?
- በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡
- እንዴት?
- አንዱን ቀዳዳ ስንደፍን ሌላው እያንጠባጠበ ተቸግረናል፡፡
- ዋናው ለራስ ማሰብ ነው ባክህ፡፡
- ምን እያልሽ ነው?
- መጀመርያ ለራስህ አስብ፡፡
- አልገባኝም?
- አንተ የተደላደለ ነገር ካለህ ሌላው ችግር የለውም፡፡
- የአገሪቱ ጉዳይ አያሳስብሽም?
- አንተ ጥሩ ነገር ካለህ መከራውም እኮ ቀስ ብሎ ነው የሚያገኝህ፡፡
- እ…
- አገሪቱ ላይ ችግር ሲከሰት እኮ ሀብታም በዜና ነው የሚሰማው፡፡
- እንዳይመስልሽ?
- እንዴት?
- የከፋ ነገር ከመጣ ሀብታሙ ራሱ ዜና ሊሆን ይችላል፡፡
- እ…
- ሀብት መቼም የሁሉ ነገር መልስ እንዳልሆነ ታውቂያለሽ፡፡
- በዚህ ሐሳብ ብዙም አልስማማም ባክህ፡፡
- ለምን?
- ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ የሚለው ነው ብዙ የሚገባኝ፡፡
- እ…
- ይኸው በቀድሞው ሥርዓት ሀብት የሰበሰቡ አሁን ምን ሆኑ?
- እ…
- ከሕግ በላይ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ እኮ ግልጽ ነው፡፡
- ማን ነው ያለው?
- እሱንማ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ነው የሚናገረው፡፡
- ምን አልሽ?
- ለማንኛውም አንተም የድርሻህን በጊዜ ብትወስድ ጥሩ ነው፡፡
- ሲኖር ነዋ፡፡
- እሱማ ከአንተ በፊት የነበሩት ጠራርገው እንደበሉት አውቃለሁ፡፡
- ተይኝ እስቲ፡፡
- ለማንኛውም ሌላው ቢቀር አንድ ነገር ለሁላችንም አመቻችልን፡፡
- ምን?
- ቪዛ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]
- ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ?
- ሁሉ ነገር፡፡
- አልገባኝም?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እኮ ተስፋ አስቆራጭ ሆናለች፡፡
- እንደዚህማ አትሁን፡፡
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- ለውጥ ላይ ነን እኮ፡፡
- ተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው?
- ለውጡማ ተቀልብሷል፡፡
- እ…
- እሱን ማረጋገጥ እችላለሁ፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ብዙ ጊዜ ነው እኮ ዕድል የሰጠናችሁ፡፡
- እሱንማ እናውቃለን፡፡
- ግን አገሪቱ እየባሰባት እንጂ ስትሻሻል አላየንም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ይኸው የእኔ ፋብሪካ እንኳን ለሦስተኛ ጊዜ እኮ ነው ጥቃት የደረሰበት፡፡
- ለምን?
- ገንዘብ አልሰጥም ስላልኩ ነዋ፡፡
- ለማን?
- ለስውር መንግሥቱ ነዋ፡፡
- የምን የስውር መንግሥት ነው?
- ይኼ እኮ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
- ምኑ ነው የአደባባይ ሚስጥሩ?
- ከመንግሥት ውጪ ሌላ ስውር ኃይል መኖሩ ነዋ፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ኃይል ባለሀብቶችን እያስጨነቀ ነው፡፡
- ምን አድርጉ ብሎ ነው የሚያስጨንቀው?
- ገንዘብ አምጡ እያለ ነዋ፡፡
- እ…
- አላመጣም ያለ ባለሀብት የእጁን ያገኛል፡፡
- ወይ ጣጣ?
- እኔም እንግዲህ የዚያ ገፈት ቀማሽ ነኝ፡፡
- ማለት?
- ይኸው ገንዘብ አልሰጥም በማለቴ ጥቃት ደርሶብኛል፡፡
- ይኼማ ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡
- የአገሪቱ ሕገወጥነት ከተንሰራፋ እኮ ቆየ፡፡
- እ…
- የሕግ የበላይነት ከተረሳ ሰነባበትን፡፡
- እንደዚህ አትበል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ራሱ ሕግ ማስከበር ካቃተው ሰነባበተ እኮ፡፡
- እ…
- ለማንኛውም አደዋወሌ ለመሰነባበት ነው፡፡
- የምን ስንብት ነው?
- ከእነ ቤተሰቤ ልንለቅ ነው፡፡
- ምን?
- አገር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- ምን እየተካሄደ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የት?
- አገሪቱ ውስጥ ነዋ፡፡
- ለውጥ ነዋ፡፡
- ነውጥ ማለትዎ ነው?
- ኧረ አይባልም፡፡
- እንዴት አይባልም?
- አንተ ሚኒስትር ነሃ፡፡
- ብሆንስ?
- እንዴት አገሪቱ ውስጥ ነውጥ አለ ትላለህ ታዲያ?
- መቼም ሰላም አለ አልል ታዲያ?
- ለውጥ ላይ ነን ነው የሚባለው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሁሉም ነገር አንገሽግሾኛል፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ሥልጣን ላይ የወጣነው እኮ ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡
- ማን አይደለም አለህ ታዲያ?
- እሱን እያደረግን ግን አይደለም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ሕዝብ እኮ እያለቀ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- ይኼ ምን ማለት እንደሆነ ያውቃሉ?
- ምን ማለት ነው?
- እኛ ሥራችንን እየሠራን አይደለም ማለት ነው፡፡
- ያለብንን ፈተና ታውቃለህ አይደለም እንዴ?
- ባውቅስ ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉም ነገር በአንዴ አይለወጥማ፡፡
- ሕግ ማስከበር ግን የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- አሁን ግን ግለሰቦችና ቡድኖች ከሕግ በላይ እየሆኑ ነው፡፡
- እ…
- በዚህ ምክንያት ደግሞ በርካቶች እያለቁ ነው፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ታዲያ እንዴት እንቅልፍ ይወስድዎታል?
- እ…
- አገራችን ላይ ይኼ ሁሉ እየሆነ እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም፡፡
- ጭንቀትህ ይገባኛል፡፡
- እሱ መፍትሔ አይሆንም፡፡
- አሁን እኮ እያደረግን ያለነው ከዚህ የባሰ ዕልቂት እንዳይመጣ ነው፡፡
- እንደዚህ ግን ነገሮች አይቀጥሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ይደረግ?
- ይኼንን ጥያቄ ነዋ መመለስ ያለብን፡፡
- እ…
- እኔ በበኩሌ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡
- ምን ልታደርግ ነው?
- ሕዝብ እንደዚህ እያለቀ ሥልጣን ላይ መቀመጥ አልችልም፡፡
- ማለት?
- እለቃለሁ፡፡
- ከምን?
- ከሥልጣን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር በጣም ተጨንቄያለሁ፡፡
- በአገሪቱ ጉዳይ ነው?
- ከአገሪቱ በላይ ያስጨነቀኝ የፓርቲያችን ጉዳይ ነው፡፡
- እ…
- ያው ፓርቲያችን ፈረሰ ማለት እኮ አገር ፈረሰ ማለት ነው፡፡
- ይህቺን ነገር የት ነበር የሰማሁዋት?
- እ…
- ፓርቲና አገርን ምን አገናኛቸው?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ አገር ሁለቱ መቼ ይለያያሉ?
- ማወቅ ያለብህ ግን ሁለቱ አንድ ያለ መሆናቸውን ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ውህደቱ ግን ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡
- ለምን?
- እውነቱን ልንገርዎት?
- አዎ ንገረኝ፡፡
- እንደ እኔ ዓይነት ሰዎች ምንም ቦታ አያገኙማ፡፡
- እንዴት?
- ማለቴ ፓርቲያችን ተዋህዶ አንድ ከሆነ አቅም ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸዋ ወደ ሥልጣን የሚመጡት፡፡
- ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡
- እ…
- ስለራስህ ብቻ ነው አይደል የምታስበው?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼን ቦታ ያገኘሁት አቅም ኖሮኝ አይደለም እኮ፡፡
- እሱንም ማወቅህ ጥሩ ነው፡፡
- እውነቴን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለነገሩ አንተ ጥሩ አቅምህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- ምንድነው?
- ሴራህ ነዋ፡፡
- እ…
- ስለዚህ መቀላቀል ትችላለህ፡፡
- ማንን?
- ሴረኛ ፓርቲውን!