Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሰልቺዎች!

ሰላም! ሰላም! ‘አሞራው በሰማይ ሲያይሽ ዋለ. . .’ ተብሎ የሠርግ ዘፈን በሚደምቅበት አገር፣ ሕዝብ በዕምባ ሲያራጩ የሰነበቱ ክፉ ሰዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ እንጃ። ከዓለም ሥልጣኔና ዕውቀት ተነጥለው ለሺሕ ዓመታት የኖሩ ይመስል በጭካኔ ተነስተው ለምን ወገናቸውን እንደሚያጠቁ በጭራሽ አይገባኝም። እዚህ በቅርባችን ያለውን በደንብ አጥርተን አውቀን ያልጨረስን ሰዎች፣ ስላልኖርንበትና ስላላየነው የተረት ዓለም በሐሰት ስለተነገረን ወሬ ወግነን ለምን ችግር ፈጣሪ ሆንን ስል ሰነበትኩ። ኧረ የሚያምታታን በዛ ምን ይሻላል ጎበዝ! ታዲያ ከሁሉ ነገር በላይ በፊት ኢትዮጵያዊ መሆኔ የሚያኮራኝና የሚያስደስተኝ፣ ለክፉም ለደግም ለአዲስ ነገር ያለመበገር ፅኑ መንፈሴ ነበር። አሁን ግን ራሴን መጠራጠር ጀምሬያለሁ፡፡ ክፉ ነገር በመጠየፍና በማጣጣል የምንታወቅ ሰዎች የክፋት ጠበቃ መሆናችን ይገርመኛል። እና ‹‹አገራችን አናት ላይ የሰፈረው ሰይጣን በፀበል ሳይሆን በመተባበር ነው የሚባረረው፤›› ያሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹ለመተባበር ዓላማ ያስፈልጋል፣ በተከፋፈለ ልብ ጊዜያዊ ኅብረት እንጂ ዘላቂ አንድነት ስለማይኖር የጋራ ዓላማ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፤›› ብሎኝ አርቄ እንዳስብ አድርጎኛል።

ባሻዬ ነገር በምሳሌ አምጥተው፣ ‹‹እንደምታውቁት የላሊበላ ሕንፃ የተገነባው ቀን ቀን በሥጋ ለባሾች፣ ሌሊት ሌሊት በመላዕክት ነው የሚል ዘመናትን የተሻገረ መልዕክት አለ። ታዲያ ይህንን እያስታወስን ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ ላሊበላን የመሰለ ዕፁብ ድንቅ ጥበብ ለዓለም ያበረከተች አገር፣ እንደ ዘመነ ጋርዮሽ ሰዎች የሚያስቡ ሰዎች በዚህ ዘመን ይኖሩባታል ሲባል አይገርማችሁም?›› ሲሉን አስደነገጡን፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ተምታቶብን ስንምታታ ስንቶች ዳር ሆነው እንደሚስቁብን ሳስበው ያሳዝነኛል፡፡ በእጆቻችን ስንትና ስንት ተዓምር መፍጠር ስንችል በድህነት ተኮራምተን ኋላቀሮች፣ ለማኞች፣ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ዘገምተኞችና ማፈሪያዎች እየተባልን በለጋሾቻችን የምንሰደብ እየመሰለኝ በደላላው አዕምሮዬ ስጨነቅ ውዬ አድራለሁ። በተለይ ደግሞ ይህ አልበቃ ብሎን የገዛ ወገናችንን ስገድልና ስናሳድድ እያዩን ምን ይሉን ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ይህንን ጭንቀቴን ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ባዋየው፣ ‹‹የሠለጠኑትማ እንደ ዝንጀሮ እያዩን ይዝናኑብናል!›› ሲለኝ መፈጠሬን ጠላሁ፡፡ ያለ ኃጥያቴ ምነው እናቴ ሆድ ውስጥ ውኃ ሆኜ በቀረሁ ስልም ተፀፀትኩ፡፡ ‹ቆጨኝ!› ነበር ያለችው እኮ ዘፋኝዋ!

እናላችሁ ሳይበላ መኖር አይቻልምና ስለገበያው፣ ኑሮው፣ ወቅታዊ የልዩ ልዩ አውቶሞቢሎች የዋጋ ተመን ‘አፕዴት’ የምንደራረግባት አነስተኛ መሰባሰቢያ ካፌ አለችን። ታዲያ ይኼ የሰሞኑን የመከራ ቅኝት ዜና ተነሳና ወዳጆቼ አስተያየት መስጠት ጀመሩ። አንዱ ጀመረ፣ ‹‹እኔ በፊት ከእኛ ውጪ በዓለም ላይ ሩህሩህ ፍጡር አለ ብዬ አላምንም ነበር። ደግነታችን፣ እንግዳ ተቀባይነታችንና አስተዋይነታችን ተጋኖ እየተነገረን ይሁን ወይም እርስ በርስ በደንብ ባለመተዋወቃችን ውስጣችንማ የተደበቀ ነገር አለ። ምናልባት ልክ እንደ ዩፎ ሚስጥራዊ ባህሪ ሳይኖረን አይቀርም፡፡ እንደ በራሪ አካላቱ እኛም ላይ ሳይንሳዊ ምርምር ካልተካሄደ በስተቀር፣ አሁን ባለው ሁኔታችን ለራሳችን ቀርቶ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጭምር አስፈሪ እየሆንን ነው፡፡ እነሱም የጌታ ምፅዓትን ለማመቻቸት በቅድሚያ የተላኩ ሥጋ ለባሽ መንኮራኩሮች ሳይሆኑ አይቀሩም የሚሉን እየመሰለኝ ነው፤›› ሲለን ሳንወድ በግድ ሳቅን። አንዳንዴ እኮ ምሬት ምን የማይፈጥረው መላምት አለ! እስኪ መላ በሉ ማለትስ አሁን ነው!

‹‹ኧረ በፈጠራችሁ አሁን ይኼን ወሬ ብለን ስናወራ እንፈር፡፡ እዚህ ከጎናችን ከእኛ እንዳልተፈጠሩ፣ እንዳልተጎራበቱ፣ አብረውን እንዳልበሉና እንዳልጠጡ ባዕዳን ፍጥረታት የሚያሰቃዩን እያሉ፣ እስኪ አሁን የሳይንስ መላምት ዮፎዎች ምን አደረጉን ብለን ነው እንዲህ እያነሳን የምንጥላቸው?›› ያለው ሌላኛው ግራ የገባው ደላላ ወዳጃችን ነበር። ይገርማችኋል ኋላ ብቻዬን ሆኜ የተባሉትን እያስታወስኩ ከራሴ ጋር ሳወራ ትልቅ ሐሳብ እንደተነሳ ገባኝ። አንዳንዶች ለምን እንደሆነ አላውቅም ሲለዩንና ሲያልፉን ነው የተናገሩት የሚገባን። በተለይ እዚህ አገርማ ሰውን መሬት ስትበላው ነው፣ ‘እሱ እኮ የሚናገረው አንዱ እንኳ መሬት ጠብ አይልም’ ይባልለታል። እናም ለራሴ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ‹‹ማን ነው ዩፎው? እያወቅነው ለምን ስሙን መጥራት አዳገተን? አካፋን አካፋ ለማለት ለምን አቃተን? መለስ ብዬ ሳስበው ግን ችግራችን ገባኝ፡፡ እንኳን እኔና ቢጤዎቼ ደላሎች መንግሥትስ መቼ ደፈረ? መንግሥት ያልደፈረውን ዩፎ የእኔ ቢጤ ምስኪን እንዴት አድርጎ ሊሞክረው? ‹ማወቅስ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን› የተባለው እኮ ዋስትና የሚሰጥ ከለላ በመጥፋቱ መሰለኝ! መሰለኝ ብቻ ሳይሆን ነውም!

በቀደም ደግሞ ውዷ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹መንጋ ሳይበላኝ በፊት ዶሮ ወጥ አብላኝ፤›› ብላ ሰቅዛ ያዘችኝ። የሚሸጥ ቢኤምደብሊዩ አውቶሞቢል እጄ ላይ ነበርና መጀመርያ ትኩረቴን ወደ ድለላዬ አደረግኩ። ‹‹አንድ ዶሮ ለመግዛት ምነው ይኼን ያህል ጭንቅ?›› አለኝ አንድ ሆላንድ የሚኖር ዳያስፖራ ወዳጄ በቫይበር። ‹‹አንተ ምን አለብህ? በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ልጅነቱን፣ ጉርምስናውንና ጎልማሳነቱን የጨረሰ ዶሮ በትንሽ ዩሮ ገዝተህ ትበላለህ፤›› አልኩት እንዳየ ሰው። እኔ እኮ ያልኩት በግምት ነው። ‹‹በምን አወቅክ ዘጠኝ ዩሮ እንደሆነ?›› አይለኝም? እንግዲህ ዘጠኝ ጊዜ ሰላሳ ምናምን ብላችሁ በሕጋዊ ተመን ስትመቱት ሒሳቡ ይመጣል። ‹‹ለነገሩ ያው ነው. . .›› ስለው ‹‹ተው! ተው! ያው ቢሆንማ ይኼን ያህል ዘመን ከአገሬ ወጥቼ እቀራለሁ?›› ብሎ በቀን በቀን ሙሉ ዶሮ በዚያው ዋጋ እየገዛ ቤቱ እንደሚገባ አጫወተኝ። ‹‹እኛ ደረቅ ዳቦ አሮብን በሠልፍ የምንጠበሰው አልበቃ ብሎ አብረን በኖርናቸው ሰዎች እንጠበሳለን፡፡ ሥጋ፣ ዕንቁላል፣ ወተት፣ ዓሳ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ወዘተ. ከዚህች ድንግል መሬት ላባችንን ጠብ አድርገን በርካሽ ማግኘት ሲገባን፣ ባልበላ አንጀታችን ስንጋደል እናሳዝናለን፡፡ የሚያዩንም ከሰው የሚቆጥሩን አይመስለኝም፡፡ አሁንማ ዙ ውስጥ የምንኖር እንስሳት ሳንመስላቸው አይቀሩም. . .›› እያለ ምሁሩ ወዳጄ ሲናገር እሸማቀቃለሁ፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

ወይ የአውሮፓና የአፍሪካ ልዩነት? ‹‹እዚያ የዶሮ የነፍስ ወከፍ ገቢ የእኛን የሰዎቹን በእጥፍ ይበልጠዋል እኮ ማለት ነው፤›› ስለው ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ቢሆንም እኛ ታርደን አንበላ . . .›› እንዳለ አፉን ከፍቶ ቀረ። ምናልባት ላይ ሲደርስ በዚህች ምስኪን ምድር ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ የቀረው ሰው ቁጥር ትዝ ብሎት ይሆናል ብዬ እኔም ዝም አልኩት። እና እንዳልኳችሁ ወሬዬን አቁሜ ተፍ ብዬ ያቺን ቢኤምደብሊዩ አሻሻጥኩና ኮሚሽን ተቀብዬ ዶሮ ልገዛ ወደ ገበያ ሄድኩ። ደረቱ እንደ ቅርፅ ተወዳዳሪ ጡንቸኛ ዶሮ ገዛሁና ወደ ቤቴ መጓዝ ጀመርኩ። መንገድ ላይ የሰሞኑን የማንጠግቦሽ ሁናቴ ትዝ እያለኝ አስባለሁ። ብታይዋት ዕቃ ማጠቡን፣ ልብስ ማለቅለቁን፣ በብርጭቆ ቀድታ ውኃ መጠጣት ሳይቀር ችላ ብላለች። በተለይ ባለፈው ክረምት ከአንድ ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች በጎርፍ ይጠቃሉ የሚል መርዶ ማን እንደነገራት አላውቅም። እኔማ ሚትዮሮሎጂ ደግ ደግ የአየር ፀባይ መተንበይ ሲሳነው፣ ለማናችንም የማይቀርልንን በከፊል ወደ መተንበዩ ገባ እንዴ እያልኩ ከባሻዬ ጋር አውርቼ ነበር። ባሻዬ ደግሞ ረሃብ ጥጋቡን መተንበይ ባልቻለ አገር፣ ለደመና ተንባይ ተቋም በጀት መመደቡ ያስገርማቸዋል። ‹‹የሰውነታችን ሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠር የሚያስችል ጤናማ አኗኗር ሳይኖረን፣ የተመጣጠነ ምግብ ሳንመገብ ነገ ይበርዳል እሳት ሙቁ፣ ነገ ይሞቃል ተገላለጡ የሚል ትንበያ እርባናው አይገባኝም፤›› ይላሉ። ‹‹ያው ቢሞቅ ከልኩ፣ ቢበርድም ከልኩ በማያልፍ ተፈጥሮ ያደላት አገር. . .›› በማለትም የሚሉት አያጡ። እኔ ግን ተንባይ አያሳጣን እላለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ቅድመ ማስጠንቀቂያ የግድ ነው!›› ይላል፡፡ እውነቱን ነው ቀድሞ ማወቅን የመሰለ ምን አለ? ‹የበላ በለጠኝ የሮጠ አመለጠኝ› አይደል እንዴ ብሒሉ!

እንግዲህ ይኼ የባሻዬ አመለካከትና አረዳድ የተለየ ነው። ድንገት ባሻዬን እንዲህ እያስታወስኩ ገደድ ስል፣ ‹‹አትዘቅዝቀው እንጂ ቀና አድርገው፤›› ብሎ አንዱ ጆሮዬ ላይ ጮኸ። ዘወር ብዬ ሳየው እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እኔ ላይ አፍጥጧል። ‹‹እኔን ነው?›› ስለው ክው ብዬ፣ ‹‹ታዲያ ማንነው ይህንን ተናፋቂ ክቡር ነገር ዘቅዝቆ የያዘ?›› ብሎ ዶሮውን ጠቆመኝ። ይኼኔ እኮ የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ቢያይ ትንፍሽ አይልም። ለነገሩም እኛም አንልም። ‹‹ምነው ባንተነፍስ አይደል እንዴ ዕድሜ የቀጠልነው? ስንት ዓይነት ሰው አለ. . .›› ብዬ ሳልፈው ደግሞ፣ ከወዲያኛው አስፋልት አንዱ ወደ እኔ አቅጣጫ እየተሻገረ፣ ‹‹እናንተ ምን አለባችሁ? ብርዱ ቆዳችንን የዶሮ ቆዳ አስመስሎት ውለን እናድራለን እናንተ ቁርስ የዶሮ ፍርፍር፣ ምሳ የዶሮ ፍትፍት፣ ራት የዶሮ መረቅ ታማርጣላችሁ፤›› ብሎኝ አለፈ። ‘እናንተ› እና ‹እኛ’ እስኪ አሁን ቢቀርስ?! ምናለበት መጀመርያ በቅጡ መረጃ ብንቀባበል? ሌላው ቀርቶ የነተበውን ካፖርቴንና ላዬ ላይ እያለቀ ያለውን ባርኔጣዬን ዓይቶ መረጃ ቢጠይቀኝ? ያንን መከረኛ ዶሮ ተሸክሜ በእግሬ ሳዘግም የታወሰኝ መከረኛው ድህነቴ ነበር፡፡ ከሽሮና ከቂጣ ለመላቀቅ ባልቻልኩበት የሕይወት ዘመኔ ከእኔ የባሰው ምስኪን ሲማረርበት ሳይ ከፋኝ፡፡ ዕድሜ ለማንጠግቦሽ ከመማረር ወደ ማማረር ደረጃ ከፍ ማለቴ የበለጠ ምሬት ፈጠረብኝ፡፡ ይኼኔ ነው እንግዲህ ክፋትና ጭካኔ እንዴት እንደሚፈጠሩም የገባኝ፡፡ ‹አሳየው ላላየው!› ነው ያሉት የአራዳ ልጆች? ኖረው ከሞቱ አይቀርስ እንደ አራዳ ልጆች ነው!

በሉ እንሰነባበት። ከስንት ስድብና ግልምጫ በኋላ ቤቴ ስደርስ አላመንኩም። ደረታሙ አውራ ዶሮ ራሱ ያን ሁሉ ስድብና ሒስ ሲያዳምጥ ውሎ በቀላሉ የሚታረድልኝ አልመሰለኝም ነበር። ኧረ አፍ አውጥቶ ‘በሕግ አምላክ! እስራቴን ፍታ!’ ብሎ ቢጮህብኝ ኖሮስ? ፈረንጆቹ ከሰው መብት ይልቅ ለእንስሳት እንደሚያደሉ የሰማሁ መሰለኝ። ካላመናችሁ ያን ሆላንድ የሚኖር ወዳጄን ስልክ እሰጣችሁና ታወሩታላችሁ። ‹‹ደቾች ከውሻ ጋር እጅግ የተለየ ቁርኝት አላቸው፤›› አለኝ በቀደም። ‹‹ምን ይገርማል ይኼ? ፈረንጅ ሲባል ለውሻ ልዩ ትኩረት አለው፤›› አልኩት ቀለል አድርጌ። ‹‹የለም! የለም! ለምሳሌ እዚህ አንድ የምታውቀው ደች ውሻው መሞቱን ሰምተህ እግዜር ያፅናህ ካላልከው በቃ ያንተና የእሱ መጨረሻ ተቆረጠ ማለት ነው። ከቻልክ የውሻው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት አለብህ፤›› አይለኝም? እዚህ እኛ ማን ይሆን ገድሎ የሚጥለን የሚለው ይወዘውዘናል፣ ያደላቸው ውሻ በአስከሬን ሳጥን ይቀብራሉ። ባሻዬ የእኔን ልዩ መረጃ ስነግራቸው መሳቅም ማልቀስም ቸግሯቸው እንደ ሌሊን ሐውልት ወደ ግራ እንደ ዞሩ ቀሩ። ምን ያድርጉ? ሁኔታችን ከእንስሳት እያሳነሰን ነዋ!

አዛውንቱ ባሻዬ ከዞሩበት ሲመለሱ፣ ‹‹የተመረቁት ለውሻ ለቅሶ እዝን ያደራጃሉ። አለን እንጂ እኛ ኑሮም ሞትም የማያምርብን፤›› ብለው ተቆጡ። እኔ ግራ ገባኝ። ‹‹ግን እኮ ባሻዬ እኛ ኢትዮጵያውያንን የመሰለ የተዋጣለት አዛኝና አስተዛዛኝ የለም ነበር የሚባለው፤›› ስላቸው፣ ‹‹ሚስጥሩ ምን ይመስልሃል ታዲያ?›› መልሰው ጠየቁኝ። ‹‹እንጃ!›› ከማለቴ፣ ‹‹ወዮው ለራሴ ነው። ድሮ የእኛ ሐዘን ወዮ ለራሴ ነው ይባል ነበር በደጉ ጊዜ። ሐዘን ሲደምቅ ደረት ሲደቃ፣ ፊት ሲቧጠጥ ብታይ ወዮ ለራሴ ነበር። ሰው ከሰው ተወልዶ የውሻን ያህል እንኳ ያለ ክብር፣ ያለ መብት፣ ያለ ነፃነት፣ ያለ ዕውቀት ዘቅጦ ኖሮ ሲሞት ስታይ ባታውቀውም ታለቅስ ነበር። ለምን እንደሆነ ገባህ?›› ሲሉኝ ቀለብ አድርጌ፣ ‹‹ወዮ ለራሴ!›› አልኳቸው። ‹‹ኤግዛክትሊ!›› ብለው ጨዋታውን ደመደሙት። በክብር ኖረን፣ መብት ጠብቀን፣ መብት አስጠብቀን፣ ግዴታ አሟልተን፣ እንዲያው በአጭሩ እንደ ሰው ኖረን እንደ ሰው ሟች ያድርገን ብያለሁ። ይኼ እንግዲህ ምኞት ነው፡፡ ምኞት አይከለከልም። የምኞት ነገር ሲነሳ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የሚመስሉ ወሬዎች የበዙበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ እንደ ሰው የሚያኖሩና የሚያሳልፉ ሳይሆኑ፣ ከሰውነት ደረጃ የሚያወርዱ አሮጌ ድርሳናት በዝተዋል፡፡ በተረት ተረት የተጀቦኑ አሰልቺ ትርክቶች፡፡ ሰው መሆንን ሳይሆን ከሰው በታች መሆንን የሚሰብኩ፡፡ በአዲስ መሸፈኛ ውስጥ የተደበቁ አሰልቺ ሐሳቦች፣ አሰልቺ ምኞቶች፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ አሰልቺ ዝባዝንኬዎች! መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት