Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየብሽሽቅ ፖለቲካው ሰለባዎች

የብሽሽቅ ፖለቲካው ሰለባዎች

ቀን:

ጉዳዩ የተፈጸመው አርሲ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበራቸው የተለያየ የፖለቲካ አቋም ቂም ቋጥረዋል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ሥፍራዎች የተከሰተው ግጭት ደግሞ እነዚህን ቂም የቋጠሩ ሰዎች እርስ በርስ ለመበቃቀል አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ነበር፡፡ በየቡድናቸው ተሰሚነት ያላቸው ሁለቱ ግለሰቦች ግንባር ለግንባር ባይገናኙም ተከታዮቻቸው ግን እስከ ቤተሰብ ዘልቀው ሥጋት መሆናቸው አልቀረም፡፡ ሁለቱ ሰዎች በነፍስ ሲፈላለጉ፣ ጭንቅ ውስጥ የገቡበት እዛውና በአዲስ አበባ ያሉ ቤተሰቦች ጭምር ናቸው፡፡

ከአንድ ወገን ቤተሰብ የሆነው ወጣት ናትናኤል (ስሙ ተቀይሯል) ተወልዶ ካደገበት አርሲ አዲስ አበባ የመጣው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመከታተል ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ ትምህርቱን ሲጨርስም ሥራ የያዘው እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ሆኖም ሰሞኑን በአርሲ የተከሰተው ግጭት ሰላሙን ነስቶታል፡፡

 አርሲ ቤተሰቦቹ ከገቡበት ጭንቀት ለማውጣትና በተለያዩ ቤተሰቦች መካከል ባሉ ልጆች የተፈጠረው የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ወላጆች ድረስ ዘልቆ ጉዳት እንዳያስከትል የአካባቢ ሽማግሌዎችን ይዞ መምከር ግድ ስለሆነበት አርሲ መጓዝን መርጧል፡፡

‹‹እያንዳንዱ ወጣት ቤተሰቡን አስይዞ ነው ግጭት ውስጥ የሚገባው›› የሚለው ናትናኤል፣ በትንሽ  አንዳንዴም በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦች የሚነገረው የብሽሽቅ ፖለቲካ በርካታው ነዋሪ ቤት ድረስ ዘልቆ ኅብረተሰቡን ግራ ሲያጋባና ሲያፈናቅል፣ ለጉዳትና ለሞት ሲዳረግ ማየቱ ከሁሉም በላይ ግጭት ባለበት አካባቢ ለሚኖሩት ፈተና ሆኗል ይላል፡፡

ናትናኤል እንደሚለው፣ እሱ ባደገበት አርሲ የተለያየ ብሔረሰብና እምነት ያለበት፣ ሁሉም ተከባብሮ የሚኖርበት ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም ሲነገሩ የነበሩ አሉታዊ ታሪኮች፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጎራ ለይቶ የተጀመሩ የብሽሽቅ የፖለቲካ አካሄዶችና ንግግሮች ኅብረተሰቡ ዛሬ ላይ ለገባበት መከራ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በሁሉም እምነት ዘንድ በዓላት ሲከበር ‹‹የኔ ይበልጥ ያንተ›› ዓይነት ፉክክር መኖሩ፣ በፖለቲካ አቋም ተከፋፍሎና ተቧድኖ በሐሳብ ከመግባባት ይልቅ በልዩነት ላይ ቂም ቋጥሮ መለያየቱ፣ ‹‹እኔ ያመንኩት፣ የሆንኩትና የተናገርኩት ትክክል ነው›› ብሎ ሌላውን ማንቋሸሽና የአንዱ የፖለቲካ አቋም ወይም እምነት ተከታይ መሆን በሌሎች ዘንድ እንደጠላት እንዲፈረጅ ማድረጉ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ናትናኤል፣ ‹‹አብሮ ይበላና ይጠጣ የነበረ፣ በዕድርና ዕቁብ የተሳሰረ አብሮነት ዛሬ ላይ ሥጋት ላይ ወድቋል፡፡ ለብዙ ዓመታት አብረው የኖሩ ሰዎች ተፈራርተዋል፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ወትዋቾች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ጽንፍ ይዘው የሚወራወሯቸው ቃላት እነሱን ሳይሆን ማኅበረሰቡን እየገረፉት ይገኛሉ›› ብሏል፡፡

 የሰላም ሚኒስቴር ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተ ግጭት የተፈናቀሉ ሕዝቦችን በመመለስና የውይይት መድረኮች በመፍጠር ቢሠራም፣ ዛሬም ኅብረተሰቡ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ከየቀየው መፈናቀሉ፣ መሞቱና መጎዳቱ አልቀረም፡፡

ደቡብ ላይ ያለ የሰላም ዕጦት ተቀረፈ ሲባል ሰሜን፣ የሰሜን ተቃለለ ሲባል ምዕራብ፣ የምዕራብ ችግር ተፈትቷል ሲባል የምሥራቅ ብሎም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች፤ የችግሩን ቆሽቋሾች ሳይሆን ከታች ያለውን ማኅበረሰብ ሰላማዊ ኑሮ ነጥቀውታል፡፡

ከላይ ያሉ ፖለቲከኞችም ሆኑ የፖለቲካ ወትዋቾች ስብስባ ተቀምጠውና መግለጫ አውጥተው በልዩነቶቻቸው ላይ ተግባብተናል ቢሉም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ኅብረተሰብ ዘንድ የተፈጠረውን መቃቃር በአዎንታዊ መንገድ መመለሱ በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈታው ቀላል አልሆነም፡፡ እስከ ሰው ሕይወት መነጠቅ የደረሰ መስዋዕትነትን ያስከፍላል፡፡ ዘግናኝ ድርጊቶች ተፈጸሙ ሲባል የሚሰማውም ብዙኃኑ ኅብረተሰብ ዘንድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የተከሰተውን ግጭት አስመልክተው ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫም፣ በኢትዮጵያ አንዳንድ ቦታዎች በተፈጸመው አንገት የሚያስደፉ ድርጊት 82 ወንድና አራት ሴቶች በአጠቃላይ 86 ሰዎች እንደዋዛ መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

በግጭቶች ወቅት ጥቂቶች የሰው ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ ሞተዋል፡፡ ሰዎች እንዳይገደሉና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሲሉ የሸሸጉም ለማትረፍ የደከሙም አሉ፡፡ ሆኖም የተነሳው የግጭት እሳት ሁሉን ነክቷልም ብለዋል፡፡

ግጭቱ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ከማስከተል ባለፈም ለብዙዎች መፈናቀል ምክንያትም ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም ያጎርሱ የነበሩ እጆች ዛሬ ላይ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ወቅት እየጠበቀ በሚከሰተው ድርቅ የአንዳንድ አካባቢ ነዋሪዎች ለዕርዳታ የሚዳረጉ ቢሆንም፣ ከግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ ጎሳዎች የሚጋጩባቸው ወቅቶች ቢኖሩም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያንን የገጠመው ፈተና ከነዚህ የተለየ ሆኗል፡፡

እርስ በርስ በመቧደን በሚከሰት ግጭት በርካቶች እየተፈናቀሉ፣ ለዓመታት ከኖሩበት አካባቢ እየሸሹ፣ መሸሻ የሌላቸው ደግሞ ባሉበት ሆነው በመቸገራቸው ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚጠብቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

አርሲ ዶዶላ ሰሞኑን በተከሰተ ግጭት 4,700 ያህል አባወራዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በአብያተ ክርስቲያናት ተጠልለዋል፡፡ አጠቃላይ የተፈናቀለው ስድስት ሺሕ ያህል ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በቤቱ አሊያም በሌላ ቦታ ተሸሽጎ ሰብዓዊ ዕርዳታን የሚጠብቅም ይገኛል፡፡

 በአርቲስት ያሬድ ሹመቴ፣ በአቶ መሃመድ ካሳና በሌሎችም አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቅጥር ግቢ ከጥቅምት 17 እስከ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉት ሰብዓዊ ዕርዳታ ሲሰበሰብ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ ከአርሲ ዶዶላ በተጨማሪ በድሬዳዋ 680፣ በሐረር 130 እንዲሁም በምዕራብ ጉጂ 6,400 ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ናቸው፡፡

የጥላቻ ንግግሩና ፅንፍ የረገጠው የፖለቲካ ሽኩቻ የፈጠረው መፈናቀል አብሮ የነበረውን ማኅበረሰብ እንዳልነበረ አድርጎ አቃቂሞታል፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት፣ ጓደኛ ከጓደኛ እንዳይተማመን፣ ትናንት አብሮ ያደገ፤ ዛሬ አንዱ በአንዱ ላይ እጁን እንዲያነሳ ምክንያትም ሆኗል፡፡

በሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት በኩል በሀገር ፍቅር ቴአትር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የለገሱትን ከሕፃናት እስከ አዋቂ የሚያገለግል አልባሳትና ምግብ ለማከፋፈል ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር አርሲ ዶዶላ አብረው የተጓዙት በጎ ፈቃደኛ አቶ ሳምሶን መገርሳ እንደነገሩን፣ በሥፍራው በነበረው ግጭት ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ ሁሉም ተጎጂ ሆኗል፡፡   

በወለደች በአንድ ቀኗ ጨቅላ ልጇን ይዛ ከቤቷ የተፈናቀለችን ጨምሮ ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ሴት ወንድ ሳይል ቤት ንብረታቸውን ጥለው መጠለያ የገቡ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ዳግም ወደ መኖሪያቸው ለመመለስም ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከተጠለሉበት ሥፍራ ለሱቅም ይሁን ለሕክምና ወጣ ያሉ ሰዎች በሰላም ያለመመለሳቸው ነው፡፡

መከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ፖሊስ በሥፍራው የገቡ ቢሆንም፣ አቶ ሳምሶን መታዘብ የቻሉት፣ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ጭንቀትና ፍርኃት ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ‹‹ተስፋ ቆርጠዋል›› የሚሉት አቶ ሳምሶን፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሁሉም እምነት ያሉ የሃይማኖት አባቶች ሥፍራው ላይ ተገኝተው ተከታዮቻቸውን ማስተማርና መገሰጽ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በመቻቻልና አብሮ በመኖር ላይ ጥልቅ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ መሃመድ ካሳ፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰቱ ችግሮች ያለመደማመጥ፣ በእርጋታ ያለመነጋገርና የጥሞና መጉደል የፈጠሯቸው ናቸው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሃይማኖትና ባህል ያላቸው፣ አንዱ ለአንዱ የሚኖር፣ አንድ ሰው ሠርቶ ብዙ ቤተሰብ የሚያኖርበት፣ ታላቅ ታናሹን የሚረዳበት፣ የሚንከባከብበትና አንዱን ከአንዱ ለመለየት የማይቻል ሕዝብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንደሚሉትም፣ በችግርና በደስታ፣ በግጭትም ቢሆን ችግርን በዕርጋታ መወጣት የለመደና የተሳሰረ ሕዝብ ነው፡፡

እንደ አቶ መሃመድ፣ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ንግግሮችንና ውይይቶችን አለማድረግ፣ የከተሜዎች፣ አወቅን ወይም ሠለጠንን የሚሉ ፖለቲከኞች ችግር እንጂ ታች ላለው ማኅበረሰብ የጎላ ችግር ባይሆንም፣ ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት ሰለባ የሆኑት ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና የመንቀሳቀስ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የችግሩ  መንስኤ የሆኑ ፖለቲከኞች ላይም ጉዳት ደረሰ ሲባል አይሰማም፡፡

‹‹የተጎዳነውም እኛ፣ የተጎዳዳነውም እኛ›› የሚሉት አቶ መሃመድ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ቀውሱን በማረጋጋት፣ ጥሞና እንዲመጣ፣ የኔ መንገድ ብቻ ልክ ነው የሚለው እንዲወገድ፣ የሌሎችም ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

‹‹አገር በቅብብሎሽ የምትቀጥል ናት፣ የአንዱ ችግር የሌላው ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም እኔን አይመለከተኝም የሚባሉበት ወቅት ላይ አይደሉም›› ብለዋል፡፡

ግጭቶችን በኃይል ማስቆም ጊዜያዊ መፍትሔ ያመጣ እንደሆን እንጂ ዘላቂነትቱን አያረጋግጥም፡፡ በመሆኑም ሕፃናትና ታዳጊዎችን በአገር በቀል ዕውቀት ማነፅ፣ ትምህርት ቤቶች ደርሶ መምጫ ብቻ ሳይሆኑ፤ በሥነ ምግባር፣ በዜግነት በኃላፊነት፣ በአገርና ብቁ ዜግነት ላይ ማስተማር ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታው እንደሚችል ያላቸውን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡

የተሰባሰበው ዕርዳታ፣ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተሠራጨ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ