Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያወዛግብ የቆየውን አስገዳጅ የሰበር ውሳኔ  ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነው...

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያወዛግብ የቆየውን አስገዳጅ የሰበር ውሳኔ  ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ነው በማለት ውሳኔ አሳለፈ

ቀን:

በአስገዳጁ ውሳኔ በርካታ ሴቶች ሀብትና ንብረታቸውን አጥተዋል

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከ13 ዓመታት በፊት በ1999 ዓ.ም. በሰ/መ/ቁ 20938 ሰጥቶት በነበረውና ሲያወዛግብ የቆየውን አስገዳጅ ውሳኔ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ‹‹የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን ነው፤›› በማለት የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ፡፡

ሰበር ሰሚው ችሎት አስገዳጅ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ‹‹በመለያየት ፍቺ ወይም ሳይፋቱ ፍቺ›› (Defacto Divorce) በሚለው ላይ ነው፡፡ ይኼ ማለት በሕግ በግልጽ ከተደነገገው ውጪ ባልና ሚስት ለበርካታ ዓመታት ያለ ፍቺ ተለያይተው በመኖር፣ የየራሳቸውን ሕይወት እየኖሩ (አግብተው ወይም ሳያገቡ) ከቆዩ፣ ‹‹ምንም እንኳን ቀደም ብሎ የተፈጸመ ጋብቻ የነበራቸው ቢሆንም፣ ሁለቱም በየፊናቸው የየራሳቸውን ሕይወት መጀመራቸው ከተረጋገጠ፣ ጋብቻቸው እንደፈረሰ ይቆጠራል፤›› የሚል አስገዳጅ ውሳኔ በመስጠቱ ምክንያት፣ በርካታ ሴቶች ሀብትና ንብረታቸውን ማጣታቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በአስገዳጅ ውሳኔውም ላይ ከፍተኛ የሆነ ውዝግብ ሲነሳ ቆይቷል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰበር የሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔ ለመሰረዝ ወይም ለመሻር  ያስቻለው፣ ስለጋብቻና ጋብቻ ስለሚፈርስበት ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ፍርድ ቤቶች ካላቸው ሥልጣን በተቃራኒ መሆኑን በመግለጽ፣ በርካታ አቤቱታዎች ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በመቅረባቸውና ጉባዔውም አቤቱታውን ምክንያት በማድረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በመመርመር ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 ሕግ የመተርጎም ሥልጣን ለፍርድ ቤት፣ በአንቀጽ 55 ደግሞ ሕግ የማውጣት ሥልጣንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጠ ቢሆንም፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ግን ከሕጉ ዓላማ ውጪ የሆነ አስገዳጅ ትርጉም በመስጠት፣ ሴቶች ንብረታቸውን የሚያሳጣ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው በመግለጽና ሕገ መንግሥቱንም የሚቃረን መሆኑን በመጥቀስ ለጉባዔው አቤቱታ እንደቀረበለት ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

በርካታ ተመሳሳይ ማመልከቻዎች ቢኖሩም ለማሳያነት ለመጥቀስ ያህል፣ ወ/ሮ አያልነሽ ሞገስ የተባሉ አመልካች የአቶ አገኘሁ ፈንቴ (በሕይወት የሉም) ሚስት መሆናቸው ተረጋግጦ ማስረጃ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤት ሲያመለክቱ፣ ፍርድ ቤቱ አረጋግጦ ሰጥቷቸዋል፡፡ አቶ አገኘሁ ከወ/ሮ አያልነሽ ጋር ከተለያዩ በኋላ፣ በ1980 ዓ.ም. ተጋብተው እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አብረው የኖሩት ሚስት ወ/ሮ አመልማል አሳዬ የተባሉ ግለሰብ ተቃውሞ አነሱ፡፡ ተቃውሞአቸውም ሟች ባለቤታቸው ከወ/ሮ አያልነሽ ልጆች የወለዱ ቢሆንም፣ በ1977 ዓ.ም. ተጣልተው መለያየታቸውንና ከእሳቸው ጋር ጋብቻ ፈጽመው እስከ ዕለተ ሞታቸው መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ወ/ሮ አያልነሽ ከ26 ዓመታት በኋላ፣ ‹‹ሚስት ነኝ›› ብለው በእሳቸውም ላይ ሆነ በሟች ባለቤታቸው ላይ ክርክር ማንሳት እንደማይችሉና ንብረትን በሚመለከትም አሥር ዓመታት ስላለፈው በይርጋ ቀሪ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎትም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም (ከላይ የተጠቀሰውን) እንደሰጠበትም አክለው ተቃውመዋል፡፡ ወ/ሮ አያልነሽ ከሟች አቶ አገኘሁ ፈንቴ ጋር የተለያዩት በ1977 ዓ.ም. በተፈጠረ ችግር ምክንያት፣ ከቤታቸው ሸሽተው መውጣታቸውንና ለብቻቸው በሚኖሩበት ጊዜ ሌላ ልጅ መውለዳቸውን በማመን፣ ነገር ግን ልጅ መውለዳቸው ከሟች ጋር የነበራቸውን ጋብቻ ሊፈርስ የሚችልበት የሕግ አግባብ እንደሌለም በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤት፣ ወ/ሮ አያልነሽ ከሟች ጋር ተለያይተው መኖራቸውና ሟችም ከወ/ሮ አመልማል ጋር ተጋብተው መኖራቸውን የሚያውቁ መሆኑ፣ ከሟች ጋር የነበራቸው ጋብቻ ለመፍረሱ ማስረጃ በመሆኑ ወ/ሮ አያልነሽ ሚስት እንዳልሆኑ ገልጾ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡  የከተማ አስተዳደሩ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም በአብላጫ ድምፅ ውሳኔውን በማፅናት፣ የወ/ሮ አያልነሽን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ‹‹ጉዳዩ ለሰበር አያስቀርብም፤›› በማለት የወ/ሮ አያልነሽን አቤቱታ ውድቅ በማድረጉ፣ ግለሰቧ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመግለጽ ለሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም፣ በመ/ቁ 20938 የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም መሠረት በማድረግ፣ የአስተዳደሩ መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 2198/02 ወ/ሮ አያልነሽ ሚስት ናቸው ያለውን ውሳኔ ሰርዞታል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት ባልና ሚስት ተለያይተው ከኖሩ ‹‹ፍቺ እንደፈጸሙ ይቆጠራል›› በማለት የያዘው አቋም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 (1) ለፍርድ ቤቶች የተሰጠውን ሕግ የመተርጎም ሥልጣን ያለፈና በአንቀጽ 55 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተለይቶ የተሰጠውን ሕግ የማውጣት ሥልጣን የሚጋፋ መሆኑን፣ የወ/ሮ አያልነሽ ጠበቃ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረቡት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡

በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ድንጋጌ መሠረት፣ ጋብቻ መፍረስ የሚችለው በሞት፣ በመጥፋት፣ ለጋብቻ የሚበቁ ሁኔታዎች አለመሟላትና በፍርድ ቤት ውሳኔ መሆኑ ተደንግጎ እያለ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ‹‹ባልና ሚስት ተለያይተው ከኖሩና የየራሳቸውን ኑሮ ከመሠረቱ ጋብቻው ፈርሷል፤›› ብሎ አስገዳጅ ትርጉም የሰጠው፣ በሕግ ከተደነገጉ ሦስት ምክንያቶች ውጪ ራሱ አራተኛ ምክንያት በመፍጠር በመሆኑ፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 79 በመተላለፍ ሕግ የመተርጎምና ወይም ከዳኝነት ሥልጣን በላይ መሥራቱን እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው አስገዳጅ ትርጉም ሕገ መንግሥታዊ መብት የጣሰ መሆኑን ትርጉም እንዲሰጥላቸው ለጉባዔው አመልክተዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጊዜ ወስዶ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የቀረቡለትን ጉዳዮች መመርመሩን ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡

ጉባዔው ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመ/ቁ 20938 የሰጠው አስገዳጅ ትርጉም፣ ከሕገ መንግሥቱና አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር ማገናዘቡም ተጠቁሟል፡፡ ጉባዔው አስገዳጅ ትርጉሙን ሌሎች የሥር ፍርድ ቤቶች እንደ አንድ የሕግ ድንጋጌ በመጥቀስ ውሳኔ እየሰጡ ቢሆንም፣ ጠበቃው በአቤቱታቸው እንዳብራሩት፣ ለፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሚሰጠውን አንቀጽ 79፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን የሚሰጡትን አንቀጽ 51 እና 55 የሚቃረን ወይም የሚጋፋ ውሳኔ መሆኑን ገልጿል፡፡ ተጨማሪም ጋብቻ ሊፈርስ የሚያስችልባቸውን በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 እና 82 ድንጋጌዎችን በማለፍ አራተኛ ምክንያት ማስቀመጡም ተገቢ አለመሆኑን እንዳረጋገጠ ጠቁሟል፡፡

የጋብቻን ፍቺ የመወሰንና ጋብቻው በፍቺ መፍረስ የሚስከትለውን ውጤት የመወሰን ሥልጣን የፍርድ ቤት ብቻ ሆኖ የተደነገገበት የራሱ ዓላማ እንዳለው ጉባዔው ገልጿል፡፡ በዋነኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ጋብቻ በፍቺ ሲፈርስ የተጋቢዎችን የንብረት ክፍፍልና የሕፃናትን የአስተዳደግ ሁኔታ አገናዝቦ ውሳኔ መስጠት ያለበት ፍርድ ቤት ነው ከሚል መነሻ መሆኑንም ጉባዔው አሳውቋል፡፡ በሕግ አውጪው እንደ ምክንያት የተወሰደው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34  ላይ የሴቶችና ሕፃናት ሕገ መንግሥታዊ መብትን ለማስጠበቅ የጎላ ድርሻ እንዳለውም አክሏል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት ሕገ መንግሥታዊ መብትን ወደ ጎን በመተው፣ ከሕግ አውጪ ዓላማ ውጪ በሆነ መልኩ ባልና ሚስት ፍቻቸውን በፍርድ ቤት መፈጸማቸውን ሳይረጋገጥ፣ የሁለቱን ተጋቢዎች የንብረት ክፍፍልና የሕፃናት ጉዳይ ዓይቶ ተገቢውን ውሳኔ ሳይሰጥበት፣ ተጋቢዎች ተለያይተው በመኖራቸውና የየራሳቸውን ሌላ ሕይወት በመጀመራቸው ‹‹ጋብቻቸው ፈርሷል›› ብሎ ትርጉም መስጠቱ የሕጉን ዓላማ የሳተ መሆኑን ጉባዔው አረጋግጧል፡፡ በሌላ መልኩ እንደዚህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ፣ ተጋቢዎች በቸልተኝነት ጋብቻቸውን ከፍርድ ቤት ዕውቅና ውጪ በፍች መልክ እንዲያቋርጡ መንገድ የሚከፍትና ሕገወጥነትን የሚያበረታታ መሆኑንም አክሏል፡፡

ጉባዔው እንዳብራራው ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ትርጉም፣ የቤተሰብ ሕጉ አንግቦ የተነሳውን መሠረታዊ መርህ ወደ ጎን በመተው፣ ‹‹ጋብቻ ከፍርድ ቤት ውጪ በተጋቢዎች ተለያይተው መኖር ምክንያት ብቻ ሊፈርስ ይችላል፤›› ማለቱ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የወጣውን የቤተሰብ ሕግ መሠረት የሳተ መሆኑንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱትን የወ/ሮ አያልነሽ ጉዳይ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ ውሳኔ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ በአንቀጽ 51 ለፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር፣ በአንቀጽ 79 (3) ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ ከሚሉት ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ ሆኖ ስላገኘው፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጉባዔው በሙሉ ድምፅ በመወሰን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84 (1) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3 (1) ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በመቀበልና ይሁንታ በመስጠት አስገዳጁ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን ሰርዞ ጋብቻ ሊፈርስባቸው ከሚችሉ ሦስት ምክያቶች ውጪ ዝም ብሎ መለያየትና መቆየት ጋብቻን ሊያፈርስ እንደማይችል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...