ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ ከመዋጮ በበለጠ ብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ የግድቡ ግንባታ በኢትጵያውያን አስተዋጽኦ እንደሚጠናቀቅ ያለውን እምነት ገልጾ፣ ሕዝቡ የውስጥ አንድነቱንና መግባባቱን ጠብቆ ከቀጠለ የተጀመረው ግንባታ በአጭር ጊዜ ዕውን እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
በ2011 ዓ.ም. 970 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥ ድጋፍ መሰብሰቡን ያስታወሱት የጽሕፈት ቤቱ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም፣ አሁንም የሕዝቡ ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉንና በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት 168.9 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ሕዝባዊ ተሳትፎው ከግድቡ ግንባታ አፈጻጸምና የሦስትዮሽ ድርድሩ ጋር በተያያዘ ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የሕዝቡ ድጋፍ ግን ያለማቋረጥ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም. የብሔራዊ ምክር ቤቱ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱና ለግድቡ ገቢ የሚያስገኙ ሁነቶችን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመው፣ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡ ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እየሠሩ መሆኑንም አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡