ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሚከናወነው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡ ሐሙስ ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. የጀመረው የመራጮች ምዝገባ፣ እስከ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚቆይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ምሽት ድረስ በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን የደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
የመራጮች ምዝገባ ሒደት በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸው፣ ‹‹በአንዳንድ ቦታዎች ከተጠበቀው በላይ ተመዝጋቢዎች በመምጣታቸው የቁሳቁሶች ቀድሞ ማለቅ የተከሰተ ቢሆንም፣ ከቦርዱ ጋር በመነጋገር በአስቸኳይ እየተፈታ በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ ነው፤›› በማለት ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ለሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ ሁለት ሚሊዮን ያህል ድምፅ ሰጪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ድምፅ ሰጪዎች ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን ወይም የደቡብ ክልል አካል ሆኖ እንዲቀጥል ይወስናሉ፡፡ ሐሙስ ዕለት በጉዳዩ ዙሪያ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ሒደቱ ሰላማዊ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
በመግለጫቸው ወቅትም 15 የማስተባበሪያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ገልጸው፣ ለአንድ ማዕከል እንደ ሁኔታው ከሁለት እስከ ሦስት ወረዳዎች እንዲካተቱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አንፃር 1,692 የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በእነዚህ ጣቢያዎች የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ስድስት ሺሕ አስፈጻሚዎችም ተመድበው ሥራቸውን እየሠሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የቅስቀሳ ጊዜ እንዲሆን መወሰኑን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ቅስቀሳው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን በመግለጽ በአንድ አካባቢ ብቻ ለቅስቀሳው ከተፈቀደው ወሰን አልፎ የመቀስቀስ አዝማሚያ በመታየቱ፣ እንዲቆም መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ በርካታ ውዝግቦችና ግጭቶች የነበሩ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. አጋጥሞ የነበረው ግጭት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉ አይዘነጋም፡፡