የዘንድሮው 19ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የፊታችን እሑድ ኅዳር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኅዳር ወር መገለጫ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው፣ በጉጉት የሚጠበቅ ትውፊት ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በርካታ የውጪ አገር ዜጎችን የሚያሳትፈው ታላቁ ሩጫ፣ ከሁለቱም ጾታ 500 ታዋቂና ታላላቅ አትሌቶችን ጨምሮ 45,000 ተሳታፊዎች በአረንጓዴና በቀይ ቲሸርት ይታደሙበታል፡፡ ጀማሪ አትሌቶች ለመታየት ሲሉ የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ ከዓምና ጀምሮ ለአሸናፊዎች የሚሰጠውን ሽልማት ወደ 100,000 ብር ከፍ ማድረጉ በተወዳዳሪዎች ተመራጭ ሆኗል፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዓለም ላይ ሊሮጥባቸው ከሚገቡ ውድድሮች ተርታ መቀመጡ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በማኅበራዊ ረገድም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እየሆነ ነው፡፡ ዘንድሮስ ምን አቅዷል? ለሚለው ደረጀ ጠገናው፣ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ አየለ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከሩጫ ያለፈ ትርጉም እየያዘ ከመምጣት በላይ፣ አሁን ላይ በርካቶች ዕለቱን በጉጉት እንዲጠብቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ የዘንድሮ ፕሮግራም ሳምንታት እየቀረው የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፣ አዲስ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ኤርምያስ፡- ከአምስት ሳምንት በፊት ብዙዎች እንደሚያስታውሱት፣ የልጆች ሩጫ፣ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችና በዚህ ዓመት የምናስገነባውን ትምህርት ቤት ጨምሮ በመክፈቻ ፕሮግራማችን የስድስት ሳምንት ፕሮግራም የየሳምንቱን የተለያዩ መልዕክቶች እንዲተላለፉባቸው ዕቅድ ይዘን ቆይተናል፡፡ ይህም ተሳታፊው ቀደም ብሎ አቅዶ እየተዘጋጀ እንዲቆይ ለማድረግ በሚል ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የመጀመሪያው ሳምንት የዱብ ዱብ ሳምንት (ይህ ማለት የስድስት ሳምንት ልምምድ አሥር ኪሎ ሜትር ለማጠናቀቅ ብቁ ስለሚያደርግ)፣ ሁለተኛውን ደግሞ የጤና ሳምንት ይህም ሰው ለውድድር የሚስፈልገውን ልምምድ ከመጀመሩ በፊት ጤንነቱን አውቆ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ነው፡፡ የሚቀጥለው ሳምንት “ምንጭ” ብለነዋል፣ ይህን ያልንበት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ መጠሪያ “አረንጓዴው ጎርፍ” ቀጣይነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ምንጭ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ እንደሚታወቀው በታላቁ ሩጫ አሳታፊነት በየዓመቱ 300 ወንዶችና 200 ሴቶች በድምሩ 500 አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ከወንዶች ለክለቦች የሚሰጠው 200 ሲሆን፣ ለሴቶች ደግሞ 100 ሆኖ ቀሪው ኮታ ለጀማሪ አትሌቶች ነው፡፡ ምንጭ ሊያስብል የቻለው ለዚህ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ለጥቂት ቦታ ሦስት መቶና ከዚያ በላይ ጀማሪ አትሌቶች የሚሳተፉ ከሆነና ኢትዮጵያ “የሯጮች ምድር” ተብላ ስለምትታወቅ ምንጩን በማጣሪያ አድርገን ተሳትፎዋቸው እንዲጨምር አድርገናል፡፡ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ የበጎ ፈቃድ ሳምንት ብለን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይህም በገንዘብ ሲተመን እስከ 35 ሚሊዮን የሚያወጣ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ቀሪው ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የፅዳት ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የቀሪው ሳምንት ዕቅድ እንደተጠበቀ፣ እስካሁን ባለው ከኅብረተሰቡ፣ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ይሁን ከሌላ ባለድርሻ አካላት ምን የገጠማችሁ ነገር አለ?
አቶ ኤርምያስ፡- እንደሚታወቀው ታላቁ ሩጫ ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በየዓመቱ የምንማራቸው ነገሮች እንደተጠበቁ፣ ዘንድሮ በተቻለ መጠን ዕቅዶቻችንን ቀድመን ነው የጨረስነው፣ ይህ ማለት ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ነው የሚል አምነት ባይኖረንም በአብዛኛው ጥሩ ነበር፡፡ ታላቁ ሩጫ በሚቀጥለው ዓመት 20ኛ ዓመቱን ያከብራል፡፡ ከዚያ በፊት ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀ “ቤስት ኢንተርናሽናል ራኒግ ኢቨንት” በሚል ትልቅ ዕውቅና አግኝተናል፡፡ ይህ ለታላቁ ሩጫ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ነገር ነው፣ የሯጮች አገር የሚለውን የሚያጠናክር ስለሚሆን ጭምር ማለት ነው፡፡ ዓለም ላይ ያሉ እንደ ኒውዮርክና ለንደን የመሳሰሉ በርካታ ተሳታፊዎች የሚካፈሉባቸው ሩጫዎች አገሮቹ ያን ያክል የሚታወቁ አትሌቶች ሳይኖሯቸው ነው፡፡ እኛም ይህን ዕድል ወደ ቱሪዝም የሚለውጥበትን እያመቻቸን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የታላቁ ሩጫ ዓመታዊ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ሱፐር ስፖርቶች የአንድ ሰዓት የአየር ሽፋን እንደሚሰጡት ይታወቃል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ሽልማት ጨምሮ በአገሪቱ በጣም ብዙ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ታላቁ ሩጫ ምን ያሰበው ይኖራል?
አቶ ኤርምያስ፡- የሱፐር ስፖርት የአንድ ሰዓት ፕሮግራም ዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሁም በዋግህምራ አካባቢ የሚያሠራቸው የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ጨምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ሽልማት የተካተተበት እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ ይህንኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስፖርት አዘውታሪ መሆናቸው ስለሚታወቅ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ዕቅድ አለን፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ በሱፐር ስፖርት አማካይነት የሚኖረውን ሽፋን “ብራንዲንግ ኢትዮጵያ” ብለነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በይፋ ያስመረቁት ዩኒቲ ፓርክም ስላለ እሱም ለማካተት ዕቅድ አለን፡፡ የአፍሪካውያን ሰንደቅ ዓላማዎች ብዙዎቹ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ምልክት ያላቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት በመሆኗ ነው፡፡ ይህን ከስፖርት ቱሪዝም ጋር በማገናኘት ልንጠቀምበት ካልቻልን የአትሌቶች አገር መባሉ ብቻውን ትርጉም የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት አለመረጋጋት ይስተዋላል፣ ይህ ለዝግጅታችሁ ተፅዕኖ የለውም?
አቶ ኤርምያስ፡- በእኛ ዝግጅት ላይ ያን ያህል ተፅዕኖ የለውም፡፡ ምክንያቱም ታላቁ ሩጫ ሁሉም እንደሚውቀው፣ ዘንድሮ 19ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡ በ1997 ዓ.ም. በአገሪቱ ከምርጫ ጋር በነበረው ግርግር እንኳ ውድድሩ ተደርጓል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከሁለት ጊዜ በላይ የተከናወነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነን ነው፣ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡ ሰውም ከፍና ዝቁን አብሮ ያለፈበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በታላቁ ሩጫ የሚሳተፈው ከአዋቂ እስከ ሕጻን፣ ከቤተሰብ እስከ አርቲስት፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ትልልቅ አምባሳደሮች የሚሳተፉበት በመሆኑ ለአብሮነታችን የተሻለ አጋጣሚ ፈጥሯል ብለን ነው የምወስደው፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሕዝብ ንቅናቄ” በሚል በቅርቡ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት የጎዳና ላይ ውድድር ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ስለ ሩጫው የዝግጅት ምዕራፍ እንደተገለጸው የበጎ አድራጎት ሥራውንም ሆነ የጽዳት እንቅስቃሴውን የተሟላ ለማድረግና በቅንጅት ለመሥራት ያቀረባችሁላቸው ጥያቄ የለም?
አቶ ኤርምያስ፡- በዚህ ዓመት አልጠየቅንም፣ ምክንያቱም ለሩጫ የምንዘጋጀው ሙሉ ዓመቱን ነው፡፡ እንደተባለው ለወደፊቱ ተቀራርቦ ለመሥራት ችግር የለብንም፣ የምንሠራበት ዕድል እንደሚኖርም እምነቱ አለኝ፡፡ በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት መስቀል አደባባይ ላይ የታየው በጣም የሚበረታታና የሚደነቅ ነው፣ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ወደፊት ተቀናጅተን ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ ምክትል ከንቲባው ከሳምንት በኋላ የምናደርገውን ሩጫ በክብር እንግድነት ተገኝተው እንዲያስጀምሩ ጋብዘናል፣ እንደሚገኙም እንጠብቃለን፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ አሥር ኪሎ ሜትር ሩጫ በአሜሪካ አትላንታ ውስጥ ይደረጋል፡፡ እስከ 60,000 ሰው ይተሳተፍበታል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቦታው ተገኝቼ ውድድሩን አይቼዋለሁ፡፡ ተሞክሮው በአገራችን እንዲለመድ ብቻ ሳይሆን፣ ከንቲባው የሩጫው ባለቤት እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ከንቲባው ባለፈው ዓመት እንደ ተመረጡ ስለ ዝግጅቱ አነጋግረናቸዋል፣ ደስተኛ ስለመሆናቸው ነግረውናል፡፡ በወቅቱ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት የምንሠራበት ሁኔታ እንደሚኖር አውርተውንም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሩጫው በአዲስ አበባ ሲካሄድ ለከተማው ገጽታ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ ግልጽ ነው፡፡ ኒውዮርክ ማራቶን ሲካሄድ በከተማው ውስጥ የሚገኝ “ማን ሐተን” ተብሎ የሚታወቀው ትልቁ የቢዝነስ ቦታ እንዲዘጋ ተደርጎ ነው፡፡ ከተማው ይህን ሲያደርግ በሩጫው የሚመጣውን ቱሪስት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ዓመት ሩጫው የሚደረግበት መንገድ ተቀይሯል፣ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ኤርምያስ፡- በቀድሞ መንገድ ሩጫውን ማድረግ እንችል ዘንድ ፈቃድ የጠየቅነው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ይሁንና የቀድሞ መንገድ በቅርቡ እንደተመለከትነው ከሆነ ግንባታ እየተደረገበት መሆኑ አረጋግጠናል፡፡ ውድድሩ ለአገር ገጽታ ግንባታ ካለው ፋይዳ ፍርስራሽ ከምናሳይ ለምን ተለዋጭ አንጠቀምም በሚል ድሮ እንደነበረው ከመነሻው መስቀል አደባባይ ወደ ሜክሲኮ እስከ ባልቻ ሆስፒታል በር ወደ መርካቶ ካቀና በኋላ በአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተመልሶ ወደ ዲ አፍሪክ ሆቴል፣ ሜክሲኮ በሸበሌ፣ ብሔራዊ ቴአትር በኩል በፊንፊኔ ወደ ቤተ መንግሥት፣ በካዛንችስ ወደ ዑራኤል፣ አደባባዩን ዞሮ በባምቢስ መስቀል አደባባይ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ውድድሩ የሚደረግበት መንገድ ልኬት የተረጋገጠውም ከዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በመጡ ሙያተኞች አማካይነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዘንድሮ ሩጫ 400 የውጪ አገር ዜጎች ለመሳተፍ ምዝገባ ማድረጋቸው ይነገራል፣ ትክክለኛው ቁጥር ምን ያህል ነው?
አቶ ኤርምያስ፡- እውነት ነው ይህን ቃለ መጠይቅ እስካደረግኩበት ታላቁ ሩጫ ከ20 አገሮች የተውጣጡ 400 ተሳታፊዎች ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የመሮጫ ቲ ሸርቱ ፎርጅድ ተሠርቶ ገበያ ላይ መዋሉ የሚናገሩ አሉ፣ ችግሩን ለመከላከል ምን እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ኤርምያስ፡- ታላቁ ሩጫ ያዘጋጀው ቲ ሸርት የራሱ የሆነ መለያ ኮድ ያለው ነው፣ ምናልባት አመሳስለው የሚያትሙ ካሉ፣ ለአታሚዎቹ ሳይሆን አገልግሎቱን ለሚያገኙ ሰዎች ምክራችን ይቅርባችሁ ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ቲ ሸርት ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የራሱ መለያ ኮድ አለው፡፡ ተሳታፊዎች ቲ ሸርቶቻቸውን እየወሰዱ ነው፡፡ ሌላው የዘንድሮውን ለየት እንዲል በሚል በምዝገባችን የተካተቱ ከ100,000 በላይ ተከታይ ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎች እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡ ሜዳሊያ የምናሳትመው በተመዘገበው ቁጥር ስለሆነ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውም ለዚያ ሲባል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የውጪ አገር ዜጎችን በተመለከተ የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጥናት እንዳስደረጋችሁ ተነግሯል፡፡ ጥናቱ በዋናነት ያስፈለገው ለምንድነው?
አቶ ኤርምያስ፡- ትክክል ነው፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጪ አገር ተሳታፊዎችን ያስመዘገበው እ.ኤ.አ 2015 “700” ነበር፡፡ ጥናቱን ያደረጉት ሙያተኞች ከእንግሊዝ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ፣ የጥናቱ ግኝት እንደሚያስረዳው ከሆነ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሆነና ከዚህ ውስጥ ትልቁ ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በወቅቱ እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዕቅድ የተሳታፊውን ቁጥር ወደ አንድ ሺሕ ማሳደግ የሚል ነበር፡፡ በ2016 በአገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ቁጥሩ በአንድ ጊዜ ወደ 300 ወረደ፣ እንደምንም ብለን በዓመቱ ወደ 400 ለማሳደግ ሞክረናል፡፡ በዚህ ዓመት ምዝገባው እንደቀጠለ ነው እስከ 500 ይደርሳል ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለበጎ አድራጎት ሥራ 1.8 ሚሊዮን ብር አሰባስቧል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ይነገራል፣ በዚህ ዓመት ትምህርት ቤት ግንባታ ያካትታል ተብሏል?
አቶ ኤርምያስ፡- ትክክል ነው፣ ሁለቱንም የበጎ አድራጎት ሥራችንን ለማሳካት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ እንደሚታወቀው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በዋናነት በአማራ ክልል ዋግህምራ አንድ ትምህርት ቤት አስገንብቶ ማስረከቡ ይታወቃል፡፡ የታላቁ ሩጫም በቅርቡ ዕውን ይሆናል፡፡ ሌላው የዘንድሮ ሩጫ ካለፉት ዓመታት ለየት ለማድረግ በሚል ሩጫው ከመጀመሩ በፊት በማሟሟቂያ መሣሪያ የታጀበ የማዕበል አጀማመር ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡ የማዕበሉ ትርጉም በሩጫው ከአንድ ሰዓት በታች የሚገቡ ቁጥራቸው ወደ ሰባት ሺሕ ይደርሳሉ ቲ ሸርታቸው አረንጓዴ፣ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚገቡ ደግሞ ቀይ ቲ ሸርት ሆኖ ቁጥራቸው 38,000 ነው፣ መነሻ ሰዓት ለአትሌቶች ለሦስት አሥር ጉዳይ (ወንዶችና ሴቶች የሚለቀቁት በሁለት ደቂቃ ልዩነት ነው)፣ ለሦስት አምስት ጉዳይ አረንጓዴ ማዕበል፣ ሦስት ሰዓት ላይ ቀይ ለባሾች ይለቀቃሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ተወዳዳሪዎች መነሻ ሰዓታቸውን አውቀው ውድድራቸውን ቢጀምሩ ከአላስፈለጊ ድካም ይድናሉ፡፡ በሌሎች አገሮች የሚደረጉ ተመሳሳይ ሩጫዎች መነሻ ሰዓታቸው ከ “A” እስከ “Z” ስለሆነ ተሳታፊዎች የሚሮጡት ሰዓታቸውን ጠብቀው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከኢቢሲ የነበራችሁ የቀጥታ ሥርጭት ውል ተቋርጧል፣ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ኤርምያስ፡- ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከኢቢሲ ጋር ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በዚህ ዓመት ሊቀጥል ባለመቻሉ፣ ፊታችንን ወደ ፋና አዙረናል፡፡ ምክንያቱ በጣም ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት ስለሆነ ነው፡፡ እኛም ከኢቢሲ ጋር የነበረው ግንኙነት በነበረው እንዲቀጥል ብዙ ጥረናል፣ ግን አልሆነም፡፡ ይባስ ብሎ ስፖንሰር ቆጠራ ሲጀምሩ አብረን መቀጠል እንደማንችል ስለገባን ውላችንን ለማቋረጥ ተገደናል፡፡ ውድድሩን በቀጥታ ሥርጭት የምናስተላልፈው በፋና ቴሌቪዥን ነው፡፡ ፋና ኤፍኤም የረጅም ዓመት ግንኙነት ስላለን ቀጣይነታችን ጥሩ እንደሚሆን እናምናለን፡፡ ሲሆን የሚዲያ መብቱን ገዝቶ መሸጥ ሲቻል አለመሆኑ እንድናዝን አድርጎናል፡፡