ባለፈው ሳምንት ከቦሌ ወደ ሜክሲኮ የሚሄድ ታክሲ ላይ ተጭኛለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም አሉ፡፡ ዞር ብዬ ስቆጥር ስምንት ተሳፋሪዎች ወንበራችንን ይዘናል፡፡ አራት ተሳፋሪዎች ለመጨመር ወያላው ጥሪውን ቀጥሏል፡፡ በዚህ መሀል ሦስት ጎረምሶች እርስ በርስ እየተገፋፉ ገቡና ኋላ መቀመጫ ላይ ተቀመጡ፡፡ ታክሲዋ በአንድ ጊዜ የመጠጥ ግሮሰሪ መሰለች፡፡ ሦስቱም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በመጠጥ ጥንቅቅ ብለዋል፡፡ የመጠጡ ሽታ ያልተስማማቸው ሁለት ሰዎች ወርደው ሌላ ታክሲ ሲፈልጉ፣ ሌሎቻችን የታክሲውን መስታወት ከፋፍተን ንፋስ ማስገባት ጀመርን፡፡ ይኼኔ ነገር ተጀመረ፡፡
‹‹ስማ ሾፌር መስኮት አዘጋልን፡፡ በዚህ ንፋስ በበዛበት ጊዜ በብርድ ተመተን በሽተኛ መሆን የለብንም . . .›› በማለት አንዱ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲጮህ ሁለቱ ጓደኞቹ በከፍተኛ ድምፅ አጀቡት፡፡ ከዚያም አልፈው ተርፈው እየተንጠራሩና በሰዎች ጀርባ ላይ እየተንጠላጠሉ መስኮቶችን መዝጋት ጀመሩ፡፡ በጓደኛሞቹ ሁኔታ የተበሳጩ ድርጊቱን ለማስቆም ሲሞክሩ ከአፍ እላፊ ወደ ቡጢ ሽግግር ተደረገ፡፡ በተፈጠረው ትርምስ ምክንያት ጉዞአችን ተስተጓጎለ፡፡ ከዚህ በላይ ይህንን ትዕይንት ለመታደም የሚያስችል በቂ ጊዜ ስላልነረበኝ እኔም ሌላ ታክሲ ፍለጋ አመራሁ፡፡
የሚቀጥለውን ታክሲ ይዤ ለመንቀሳቀስ ስንዘጋጅ የአንድ ሰው ቦታ ስለነበር አንዲት ወጣት በወያላው አጋፋሪነት ገብታ ተቀመጠች፡፡ ጉዞው ተጀመረ፡፡ በአጋጣሚ አጠገቤ ተቀምጣ ስለነበር፣ ‹‹ወይ ጉድ? ሰው እንዲህ ትዕግሥት አጥቶ እርስ በርሱ ይባላል?›› ስትል፣ ‹‹ምን ገጠመሽ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ከአንድ የተረገመ ታክሲ ላይ ወርጄ ነው እዚህ የተሳፈርኩት . . .›› ብላኝ እኔ ተሳፍሬበት ስለነበረው ታክሲ ገጠመኟን ስትነግረኝ፣ እኔም እዚያ እንደነበርኩ ነገርኳት፡፡ በመጠጥ በናወዙት ጎረምሶች የተነሳ የተፈጠረው የጉዞ መስተጓጎል እንዳናደዳት ነግራኝ፣ ከዚህ ይልቅ ያለንበት ዘመን አጓጉል ነገር እንደሚያበሳጫት ወግ ጀመረች፡፡
‹‹ምን መሰለህ? እኛ ሰዎች ስንባል በተፈጥሮ የተለያዩ ፍላጎቶች አሉን፡፡ እኔ ለምሳሌ የቀለም ምርጫዬ፣ የዜማ ፍላጎቴ፣ የውበት ምልከታዬ ለብዙዎች አይስማማም፡፡ ከቀለም ምን ትመርጫለሽ ብትለኝ ጥቁር በጣም ያስደስተኛል፡፡ ከዜማ ብትለኝ ደግሞ ብሉዝ ነፍሴ ነው፡፡ ውበት ላይ ደግሞ አስገራሚ ልትለው ትችላለህ አጠርና ፈርጠም ያለ ምርጫዬ ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ ብትቀበለውም ባትቀበለውም የእኔ ምርጫ ነው፡፡ አንተም የራስህ ይኖርሃል፡፡ ጓደኞቼ ግን በምርጫዎቼ ደስተኛ ካለመሆናቸውም በላይ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይተቹኛል፡፡ አልፎ ተርፎም ስለምርጫዬ ባልናገር ይወዳሉ . . .›› በማለት ከት ብላ ሳቀች፡፡ አሳሳቋ ግን እልህ አለበት፡፡
ወጣቷ ቀጠለች፡፡ እኔም ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡ ‹‹ይገርምሃል እኔ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ሥራ ከጀመርኩ ሁለት ዓመት ሊሞላኝ ነው፡፡ ሁለት ቦታዎች ተቀጥሬ ሠርቻለሁ፡፡ ያየሁት ግን ያበሳጨኛል፡፡ ረዥም ዓመት ሠርቻለሁ ብሎ የሚውረገረግ አንዱ ይመጣና ‹የምን እዩኝ እዩኝ ነው? እዚህ አገር ጉልበትሽን የሚበዘብዝ እንጂ፣ ልፋትሽን የሚያይ የለም› ብሎ ተስፋ ያስቆርጥሃል፡፡ አለቃ ፊት ትጉህ ሠራተኛ ለመምሰል የሚሞክረው፣ ከሥራ ይልቅ የግል ጉዳዩን ሲያሯሩጥ ታየዋለህ፡፡ እኔ በተቻለ መጠን ልምድ ለማግኘት ተፍ ተፍ እያልኩ ለነገው የተሻለ ሕይወቴ ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀም ላይ ታች ስል፣ የግል ጥቅሜን የማባርር አስመስለው ይስሉኛል፡፡ በዚህ የተነሳ ትቼላቸው የግል ሥራዬን እየተሯሯጥኩ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ይመሥገነው ውጤት ማግኘት ጀምሬያለሁ፡፡ ግን አስመሳዮችና አጭበርባሪዎች በመብዛታቸው ሥራዬን የማከናውነው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው . . .›› እያለች ቀጠለች፡፡ ግልጽነቷና አስተሳሰቧ ደስ ይላል፡፡
‹‹በቅርቡ አንድ በንግድ ሥራው የተዋጣለት ከተባለ ሰው ጋር አንድ ሥራ አገናኘኝ፡፡ ሰውየው ብዙ የሚወራለትና ዝና የተደረደረለት ስለሆነ የታዘዝኩትን ሥራ በአግባቡ አከናውኜ በተባለው ጊዜ አስረከብኩት፡፡ በመጀመርያ ከወሰድኩት ቀብድ በኋላ ሥራውን ሳስረክብ ክፍያዬ ወዲያው ገቢ ሊደረግልኝ ይገባል፡፡ በስልኬ አማካይነት የባንክ አካውንቴን በተደጋጋሚ ብፈትሽ ምንም ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ቀናት አልፈው ሳምንት ሞላ፡፡ ኧይ! ገንዘቤን መጠየቅ አለብኝ ብዬ ስልክ ደወልኩለት፡፡ በጣም በሚያማልሉ ቃላት ሰላምታ ካቀረበልኝ በኋላ የሒሳብ ሠራተኞች ስህተት መሆኑን ነግሮኝ ቢሮው በአስቸኳይ እንድገኝ ነገረኝ፡፡ እንደ ተቀጣጠርነው ቢሮው ደርሼ በጸሐፊው አማካይነት እሱ ዘንድ ቀረብኩ፡፡ ለራሱ ከሰጠው ግዝፈት አንፃር ቢሮው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው . . .›› ብላ በረዥሙ ሳቀች፡፡ ደነገጥኩ፡፡
መደንገጤን ተገንዝባ፣ ‹‹የሰውየው ቢሮ በጣም ከመተለቁ የተነሳ ከራሱ ጠረጴዛና ወንበር በተጨማሪ የስብሰባ ጠረጴዛና ወንበሮች፣ ሰፊ ቦታ ላይ የተንጣለለ ሶፋ፣ የመጻሕፍት መደርደሪያ አሉት፡፡ በአንድ ጥግ ወደተለያዩ ክፍሎች (መፀዳጃ ቤትና ማረፊያ) የሚወስዱ በሮች አሉት፡፡ በቢሮው አጠቃላይ ሁኔታ ግር ብሎኝ መሀል ላይ እንደቆምኩ ሰውየው ተንደርድሮ መጥቶ እጄን ይዞ ሶፋው ላይ አስቀመጠኝ፡፡ ያዘጋጀውን ቼክ በፖስታ አድርጎ እጄ ላይ እያስቀመጠ፣ ‹ዋው አንቺን የመሰለች ቆንጆ . . .› እያለ ሊተሻሸኝ ሲሞክር ራቅ አልኩት፡፡ ይኼኔ ሳቅ እያለ ጠጋ ብሎኝ፣ ‹የበለጠ መጠቀም ከፈለግሽ በፍቅር ብንቀራረብ ምን ይመስልሻል? ሲለኝ፣ ‹ይቅርታ የእኔ ዓላማ ይኼ አይደለም› ብዬው ተነሳሁ፡፡ በጣም እየሳቀ፣ ‹ድሮም እኮ አትብይ ያለሽ ዕድልሽ ነው የሚያንከራትትሽ፣ ስንቶቹ እንዴት እንደሚለማመጡኝ ቢገባሽ ኖሮ . . .›› ሲለኝ የተቀመጠበት ጥዬው ወጣሁ፤›› አለችና ትክዝ አለች፡፡
‹‹ይህንን ሰውዬ በዝና የሚክቡት ሰዎች ወይ የጥቅም ቁርኝት አላቸው፣ አለበለዚያም አያውቁትም፡፡ ሥራውን በሰጠኝ ሰሞን በተለያዩ አጋጣሚዎች በስልክ ስናወራ ከፍተኛ የሆነ የአገር ፍቅር እንዳለው፣ ዴሞክራት መሆኑን፣ ሰብዓዊነት እንደሚሰማውና የተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ የተለያዩ ጉዳዮችን እያስታከከ ሲያወራ ሰምቸዋለሁ፡፡ ያንን ሁሉ ሲዘበዝብ የነበረውና በኋላም ገንዘቤ እንዲዘገይ ያደረገው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ የገባኝ የመጨረሻ ድርጊቱን ሳይ ነው፡፡ አሁን አሁን በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያው ‹ከእኛ በላይ ላሳር› የሚሉ አክቲቪስት ተብዬዎችን ስሰማ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ አስመሳዮችና አጭበርባሪዎች ናቸው የሚታዩኝ፡፡ ነፃነትህን ገፈው አሽከር ለማድረግ የሚፈልጉ ሥውር ሌቦች ናቸው፡፡ በተደበቀ ማንነታቸው ውስጥ ያደፈጠው አውሬነት ግን ሳያጋልጣቸው አይቀርም፤›› ብላኝ ሜክሲኮ ደርሰን ተለያየን፡፡ የእዚህች ወጣት ገጠመኝ እኔ ዘንድ ከሚቀር ብዬ ነው ለእናንተም ያካፈልኩት፡፡ ምክንያቱም በንፁኃን ደም የሚነግዱ ሥርዓተ አልበኞች በዝተዋልና፡፡
(ወሰንሰገድ ታፈሰ፣ ከልደታ)