በሶማሌ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ ዝርፊያና የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሥቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የ18 ሚሊዮን ብር የፍትሐ ብሔር ክስ ቀረበባቸው፡፡
ክሱ የተመሠረተው ባለፈው ዓመት ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ቀጥተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሲሆን፣ ክሱን የመሠረቱት ፋልኮልኮች ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና አቶ አብዱራህማን መሐሙድ የተባሉ ባለሀብት ሲሆኑ፣ ተከሳሽ የነበረው የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡
የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲ ኢሌ) በሰጡት ሕገወጥ ትዕዛዝ መነሻነት የከሳሾች የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና የነዳጅ ማደያ እንዳይሠሩ መደረጋቸውን፣ የከሳሾች ጠበቃ አቶ ብሩክ ዘሪሁን ያቀረቡት የክስ ሰነድ ያመለክታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ሕገወጥ ትዕዛዝ ተሽከርካሪዎቹና የነዳጅ ማደያው ሥራ በማቆማቸው፣ በከሳሾች ላይ በደረሰው የጥቅም መቋረጥ፣ ከሕጋዊ ወለድና የጠበቃ አበል ጋር 18 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተጠይቋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባቀረበው የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ፣ ከሳሾች በፌዴራል የተመዘገቡ የንግድ ድርጅቶች መሆናቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ አለማቅረባቸውን፣ የአቶ አብዱራህማን የንግድ ድርጅት የሚገኘው በሶማሌ ክልል በመሆኑ፣ ክሱ በፌዴራል ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደማይችል፣ ጉዳዩ በአስተዳደር አካል ታይቶ እንዲወሰን ክልሉ በሒደት ላይ መሆኑንና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠው በመሆኑ የተጀመረው አስተዳደራዊ ሒደት ሳይጠናቀቅ በመደበኛ ፍርድ ቤት መክሰስ እንደማይችሉ በመጥቀስ፣ የመጀመርያ መቃወሚያውን የክልሉ ዓቃቤ ሕግ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ጥፋቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በመሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊነት እንደሌለበትና እንደማይመለከተው፣ የአቶ አብዱራህማን የክስ መነሻ ሀብት የራሳቸው ቢሆንም እንኳን፣ ክስ ሊያቀርቡ የሚችሉት በክልሉ ሥልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት መሆኑን በመግለጽ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ የመቃወሚያ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡
የከሳሾች ጠበቃ ባቀረቡት ለመጀመርያ መቃወሚያ መልስ፣ መንግሥት ተከሳሽ በሆነበት ጉዳይ ከሳሽ በፈለገበት ፍርድ ቤት ክስ የማቅረብ አማራጭ እንዳለውና ይኼም በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉም ተደንግጎ እንደሚገኝ በማስረዳት፣ የክልሉን ዓቃቤ ሕግ መቃወሚያ በመቃወም ውድቅ እንዲደረግላቸው ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙን የክርክር ሐሳብ የመረመረው ፍርድ ቤት ተከሳሽ ያቀረበውን የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ፣ ወደ ፍሬ ነገር ክርክር እንዲገቡ ብይን ሰጥቷል፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ከውል ውጪ ኃላፊነት ስላለባቸውና ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ስለሚረዳ ወይም ኃላፊነት ቢመጣ እንኳን በፍትሐ ብሔር ሕጉ 2155 ድንጋጌ፣ ሕጉን ለማስፈጸም ወደ ክርክሩ ሁለተኛ ተከሳሽ ሆነው እንዲገቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በመሆኑም አቶ አብዲ መሐመድ በቀረበባቸው የ18 ሚሊዮን ብር ፍትሐ ብሔር ክስ ላይ ክርክር ለማድረግ፣ ከታኅሳስ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡