Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የቸገራት መፍትሔ እንጂ ወሬ አይደለም!

ኢትዮጵያ አሁንም በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ የትኛው መንገድ ከየትኛው ይሻላል? አቋራጩ ወይስ ዙሪያ ጥምጥሙ? ገደላ ገደል የበዛበት ወይስ ቀጥተኛው? በመሰናክሎች የታጠረው ወይስ ጥርጊያው የተመቻቸው? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ የለም፡፡ ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት ፈቃደኝነት አይታይም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀናውን ጎዳና ለመምረጥ ንግግር፣ ውይይት፣ ክርክር ወይም ድርድር ለማድረግ የሚረዳ መድረክ አይፈለግም፡፡ እንዲያው በደፈናው ስለመጪው ምርጫ ይወራል፡፡ ወደዚያ ስለሚወስድው አመቺ መንገድ ግን ለመነጋገር ወገቤን ይባላል፡፡ በአደባባይ ወጉ ሁሉ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ስለፍትሐዊነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለነፃነት፣ ወዘተ ነው፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ ግን ሴራ ደርቷል፡፡ በተልካሻ ምክንያቶች ግጭቶች ይቀሰቀሳሉ፡፡ ግጭቶቹ በሞትና በውድመት ይጠናቀቃሉ፡፡ ተጠያቂዎች ግን የሉም፡፡ ዑደቱ በዚህ አያበቃም፡፡ ሌላ አጀንዳ ይፈለግና ባልታሰበ ጊዜና ሥፍራ ሌላ ግጭት ይነሳል፡፡ ከዚያም ሞትና ውድመት ይቀጥላል፡፡ መፍትሔው ላይ ከማተኮር ይልቅ የማይረቡ ንትርኮች ይጀመራሉ፡፡ መነጋገር የለ፣ መተማመን የለ፡፡ በሐሰተኛ ዜና የታጀቡ ብሽሽቆች የበላይነቱን ይይዛሉ፡፡ በተለይ ለዚህ ሲባል የተከፈቱ ማኅበራዊ ትስስሮች አገርን ከቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ የሚያንደረድሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን እያሻኮቱ፣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ያውካሉ፡፡ ንፁኃን ተገድለው ሐዘን የሚገለጸው በብሔራቸው ከሆነ፣ ሐሰተኛ ምሥሎችንና ወሬዎችን በማቀናበር ለተጨማሪ ውድመት ጥድፊያው ከበዛ የሚፈለገው ምንድነው? ከዚህስ የሚገኘው ጥቅም ወይም እርካታ ምን ይሆን? በዚህ ሁኔታስ እስከ መቼ ይቀጠላል? መፍትሔው ጠፋ ወይ?

ኢሕአዴግ አገር የማስተዳደር ኃላፊነቱን መወጣት አቅቶት የእርስ በርስ ሽኩቻው አላላውስ ብሎታል፡፡ በሌላ በኩል አጋሮቹን ጨምሮ ውህድ ፓርቲ ለመመሥረት ተፍ ተፍ እያለ ነው፡፡ በውህደቱ ጉዳይ ላይ ከውስጥም ከውጭም የሚቃወሙት አሉ፡፡ የሚደግፉትም እንደዚሁ፡፡ ይህ የውስጠ ፓርቲ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ እንለፈው፡፡ ነገር ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕግ ማስከበር አቅቶትና ራሱም ሕግ ማስከበር ተስኖት፣ ኢትዮጵያን መስቀለኛ መንገድ ላይ ገትሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥጋት ውስጥ ሲሆን እንዴት ዝም ይባላል? በከተማ ውስጥ ሕዝቡን ተደራጅተው ከሚዘርፉ ወረበሎች ጀምሮ፣ ሕግን ንቀውና ተፀይፈው እንዳሻን መሆን እንችላለን እስከሚሉ ጉልበተኞች ድረስ በአደባባይ ሲፈነጩ እንዴት ነው ነገሩ አይባልም እንዴ? በተለያዩ ፋይዳ ቢስ ምክንያቶች ንፁኃን ሲገደሉና ሰላም ሲደፈርስ ማቆሚያው መቼ ነው? ሞትና ውድመት እየተለመደ የየዕለቱ ክስተት ሲሆን፣ እንደ እነ ሶሪያና የመን ዓይነት መከራ እየመጣ እንደሆነ ለምን አይታሰብም? የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገና ትምህርት ከመጀመራቸው የሞት መርዶ በአቋራጭ ሲመጣ፣ የከፋው ነገር እየተቃረበ መሆኑን ለምን መገንዘብ ያቅታል? በየቀኑ ችግሮችን ከመፈብረክ ለምን መፍትሔው ላይ አይተኮርም?

ኢትዮጵያ ሊያመልጣት የማይገባ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ብትገኝም፣ ይህንን ወርቃማ ዕድል ለማበላሸት የሚባዝኑ መብዛታቸው በእጅጉ ያስከፋል፡፡ ከአገር ጥቅምና ህልውና በላይ የራሳቸውን ብቻ ለማስቀደም የሚሯሯጡ ኃይሎች ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ፣ ከወጣም በማንኛውም መንገድ ለማስመለስ፣ የማይቻልም ከሆነ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› እንዳለችው እንስሳ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፡፡ ከዚህ ቀደም ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር የተሳናቸው ዛሬ ተጣሰ እያሉ ሲደነፉ መስማት ያስገርማል፡፡ እነዚህን ኃይሎች በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በተለያዩ ወንጀሎች ሲከሱ የነበሩ ደግሞ፣ መልሰው በጓሮ በር ገጥመው ሲዶልቱ ሲታዩ ግራ ያጋባል፡፡ ልዩነቱ ከመርህ ሳይሆን ከጊዜያዊ ጉድኝት አንፃር እየተለካ ሕዝብ ይደቆሳል፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚባለው የደካሞች ፈሊጥ የአገሪቱ ፖለቲካ ሲበላሽ እንደማየት የሚያስከፋ ነገር የለም፡፡ ‹‹ዘለቄታዊ ጥቅም እንጂ ዘለቄታዊ ወዳጅ›› የለም የሚለው አባባል የሚሠራው እኮ፣ ለእንዲህ ዓይነቱ ዓይን አውጣነት አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ የተጣሉ ነገ መታረቃቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ጠላትነትና ወዳጅነት በአግባቡ ከተያዙ አንድ ቀን ወደ ንግግርና ድርድር ማምራታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን በመርህ የማይገዛና ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› የሚለው መደዴነት ከብልህ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ያልበሰሉ ፖለቲከኞች አገርንና ሕዝብን የሚያምሱት በእዚህ ዓይነቱ የወረደ ዕይታና ግንዛቤ ነው፡፡ ለዚህም ነው በማይረቡ ምክንያቶች ይህንን የታሪክ መልካም አጋጣሚ አታበላሹ የሚባለው፡፡ ብስለት መፍትሔ ነው የሚያመነጨው እንጂ ችግር አይፈለፍልም፡፡

ሌላው ችግር የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ከመንደር ወሬ ተለይቶ አለመታየቱ ነው፡፡ አንድ በሕዝብ ድምፅ እዳኛለሁ የሚል  የፖለቲካ ፓርቲ የመጀመርያ ሥራው ሕግ ማክበር ነው፡፡ ሕግ ሲከበር የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ፖለቲካዊ ዓላማን የማስፈጸም መብቶች ይረጋገጣሉ፡፡ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ምቹ ሁኔታ ይለመዳል፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት በሚገባ ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ የውይይትና የክርክር ባህል ይፈጠራል፡፡ ሐሳቦች በነፃነት እንዲተላለፉ በርካታ መድረኮች ይፈጠራሉ፡፡ መከባበርና በእኩልነት መነጋገር ባህል ይሆናል፡፡ ለሴራና ለሸፍጥ ሥፍራ አይኖርም፡፡ መብትን ለመጠየቅ ግዴታን ማወቅ ይቀድማል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና ከበሬታ ስለሚኖር ጉልበት ይናቃል፡፡ አጭበርባሪነት፣ አስመሳይነት፣ ሌብነት፣ ውሸታምነት፣ አድሎአዊነትና የመሳሰሉት ዝቅጠቶች የተናቁ ይሆናሉ፡፡ በሕዝብ ስም መነገድና መቆመር ጊዜው ያለፈበት ይሆናል፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል ይወገዳሉ፡፡ በአጠቃላይ በእንዲህ ዓይነት መርህ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ማከናወን ሲለመድ የወጣቶች ንቃተ ህሊና ይጎለምሳል፡፡ በአጉል ቅስቀሳ በመነሳሳት ድንጋይ ከመወርወር፣ የገዛ ወገንን ከማጥቃትና ንብረት ከማውደም ይልቅ ድርጊቶችን መመርመር ይለመዳል፡፡ ማሰላሰል፣ መጠየቅና መሞገት ባህል ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ትውልድ ወደፊት ማምጣት ሲቻል ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህንን ማየት የማይሹ ግን ትውልዱን ዓይኑን ጋርደው ሊጋልቡት ስለሚፈልጉ፣ አገሪቱን የግጭት አረንቋ ውስጥ በመክተት ሕዝቡን ሰላም ይነሳሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ነው የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ ለዘለቄታዊ መፍትሔ በአንድነት መነሳት ያለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከሰላማዊና ከሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ውጪ የአመፅ መንገድ አያዋጣትም፡፡ ኢትዮጵያ የታሪኳ አብዛኛው ክፍል የጦርነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከዚህ ቀደም የውጭ ወራሪዎችን ለመመከትም ሆነ በእርስ በርስ የሥልጣን ትግል በርካታ ጦርነቶች ተደርገዋል፡፡ ዘመነ መሣፍንትን እንዲያበቃ ካደረጉት አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ መንግሥት ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች በርካቶች አልቀዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ጦርነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያተረፈው ነገር ቢኖር ከመጠን ያለፈ የመረረ ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ የአሁኑን የታሪክ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከግጭትም ሆነ ከጦርነት አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይበጃል፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበትን የዕብሪት መንገድ መተው ይሻላል፡፡ ማንም በማንም ላይ የበላይ መሆን አይቻለውም፡፡ ይህ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ሥሩ ተነቅሎ መጣል አለበት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር እንዴት እንደምትገነባ የበሰሉ ሐሳቦችን ማቅረብ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብቻ አየሩን ተቆጣጥረው አገር ስትታመስና ሕዝብ ተስፋው ሲደበዝዝ፣ ለምን ብሎ የሚነሳ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ማፍራትም ሌላው የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተንቆ፣ ተገፍቶና ለሥቃይ ተዳርጎ መቀጠል አይቻልም፡፡ በሕዝብ ስም የሚቀልዱና የሚቆምሩ አስመሳዮች በቃችሁ መባል አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ የቸገራት መፍትሔ እንጂ ወሬ አይደለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...