በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ ተገደለ
ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በተፈጠረ ግጭት፣ ሕይወታቸው ባለፈው ሁለት ተማሪዎችና የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል በገቡ 13 ተማሪዎች ጉዳት የተጠረጠሩ አሥር ተማሪዎችና ሦስት የተማሪዎች መኝታ ክፍሎች ተቆጣጣሪዎች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡
ግጭቱ የተቀሰቀሰው ቅዳሜ ምሽት ላይ የተካሄደው የእንግሊዝ እግር ኳስ ቡድኖች አርሰናልና ሌስተር ሲቲ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ተማሪዎች ወደ ማደሪያ ክፍላቸው እየሄዱ ባለበት ወቅት ከነባር ተማሪዎች ማደሪያ የተጀመረ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጀማሪ ተማሪዎች ማደሪያ እንደተዳረሰ ተጠቁሟል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ አስናቀ እንደገለጹት፣ በተፈጠረው ሁኔታ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ተማሪዎች ጥልቅ ሐዘን ተስምቷቸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ትምህርት ለመጀመር ከተለያዩ ክልሎች ወደ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ፣ ከዘጠና በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ያደረጉላቸው አቀባበል እጅግ በጣም የሚያምርና ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ምሳሌ ከመሆን ባለፈ እጅግ አስደሳች እንደነበር አስታውሰው፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ በሰላም በቀጠለበት ሁኔታ ይኼ ችግር እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
ግጭቱ የተፈጠረው ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ መሆኑን ያረጋገጡት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎች የኳስ ጨዋታ የሚያዩበት ቦታ ከመኝታ ክፍላቸው ራቅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሌላም ጊዜ ተማሪዎች የኳስ ጨዋታ ካዩ በኋላ ወደ መኝታ ክፍሎቻቸው ሲመለሱ፣ ጨዋታው በሚተላለፍበት ቦታና በመኝታ ክፍሎቻቸው መካከል ርቀት ስላለውና አካባቢው ጨለማ ስለሚሆን ድንጋይ መወራወር እንደነበር አክለዋል፡፡
ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የተፈጠረው ድርጊት ግን ሌላ ጊዜ ከሚደረገው የተለየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተረፈ፣ ድንጋይ ተወረወረ ተብሎ ወዲያው ወደ መኝታ ክፍሎች በመዛመት በዋናነት ሕንፃ ቁጥር ሰባት በሚባለው ከዓመት በፊት በገቡ ተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ግጭቱ ተጀምሮ፣ ወደ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በመዛመት ያልተጠበቀ ጉዳት ሊደርስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ሲደርስ ግጭቱ ቆሞ እንደነበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በአጭር ደቂቃዎች ውስጥ በደረሰው ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋቱንና 13 ተማሪዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል እንደገቡ ገልጸዋል፡፡
ግጭቱን በማስነሳት ወይም በመሳተፍ የተጠረጠሩ አሥር ተማሪዎችና ሦስት የተማሪዎች መኝታ ክፍሎች የሚቆጣጠሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የድርጊቱን መነሻና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ተረፈ፣ ሁለቱ ተማሪዎች የተገደሉት በመሣሪያ እንደሆነ የሚነገረው ሐሰት መሆኑን አክለዋል፡፡ የሞቱትም ሆኑ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በድንጋይ፣ በዱላና በግንባታ ቁርጥራጭ ብረቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎችና ሚዲዎች ግጭቱን የብሔር ለማድረግ የሆነ ያልሆነውን እየተናገሩና እያስተላለፉ ቢሆንም፣ ከእውነት የራቀና አሁንም ቢሆን በተማሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ባለማየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ያልሆነው እንደሆነና ያልታሰበውን አሳስቦ በተማሪዎች መካከል ያልተፈለገ ነገር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ቀናት ተማሪዎች በቡድን በቡድን ሆነው ከተመካከሩ በኋላ፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከዞንና ከወረዳ አስተዳዳሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራር አቶ አህመድ ቱሳ፣ ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፣ ከዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አስረስ ንጉሥ (ዶ/ር) እና ከሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳዔ መኮንን ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ውይይቱ እየተካሄደ በመሆኑ ለጊዜው የመማር ማስተማር ሒደቱ አለመጀመሩን ጠቁመው፣ የተማሪዎች የካፌ አገልግሎት መቀጠሉንና በአሁኑ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላም መውረዱን ተናግረዋል፡፡ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ተኝተው የነበሩት 11 ተማሪዎች ሕክምናቸውን ጨርሰው መውጣታቸውንና አንድ ተማሪ ለተጨማሪ ሕክምና ደሴ አጠቃላይ ሆስፒታል በሪፈር መላኩንም ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎቹ በሰላም ትምህርታቸውን ጀምረው በጥሩ ሒደት ላይ እንደነበሩ፣ በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከዩኒቨርሲቲው በኅብረት በመውጣት እየተባበሩ እንደነበር አቶ ተረፈ ገልጸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የሚያሳየው ምን ያህል ተማሪዎቹ ተግባብተውና አንድ ሆነው ትምህርታቸው ላይ ማተኮራቸውን እንደነበር አክለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በምግብ አዳራሽ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት፣ አንድ ተማሪ መገደሉን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡ ድንገት በተፈጠረው ግጭት በተገደለው የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ምክንያት በተፈጠረው ድንጋጤ ትምህርት የተቋረጠ ሲሆን፣ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡