Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሳምንቱ መጨረሻ በውህደት ላይ ለመወሰን ይሰበሰባል

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሳምንቱ መጨረሻ በውህደት ላይ ለመወሰን ይሰበሰባል

ቀን:

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደሚሰበሰብና በግንባሩ ውህደት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍ ዋነኛው አጀንዳ እንደሚሆን ከግንባሩ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ እንዲካሄድ የሚጠበቀው በሳምንቱ መጨረሻ እንደሆነ ጊዜያዊ ፕሮግራም መያዙን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመወያያ አጀንዳ ከሚሆኑት ወሳኝ ጉዳዮች መካከል የግንባሩን ቀጣይ አደረጃጃት መወሰን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ግንባሩን አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፓርቲ ለማድረግ ሲካሄድ የነበረውን ጥናት መነሻ በማድረግ ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ ማሳለፍ አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በግንባሩ ሦስት ፓርቲዎች በውህደቱ ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዙ የተሰማ ሲሆን፣ የግንባሩ መሥራች የሆነው ሕወሓት ግን በግንባሩ አባል ፓርቲዎች መካከል የሐሳብ አንድነት የሌለ በመሆኑ ውህደትን በአሁኑ ወቅት ለመቀበል ፍላጎት እንደሌለው አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢሕዴን በግልጽ ወደ አገር አቀፍ ፓርቲ ለማምራት የሚያስችለውን ውህደት ደግፈዋል፡፡

የአዴፓ፣ የኦዴፓና የደኢሕዴን አመራሮች እስካሁን ያለው የኢሕአዴግ አደረጃጀት አጋር ፓርቲዎች የሚመሯቸውን ክልሎች ያገለለና በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ለመወከል የማያስችለው በመሆኑ፣ ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት መሸጋገሩ የግድ መሆኑ እንደታመነበትና ይህም በጠቅላላ ጉባዔ ተወስኖ ጥናት ሲደረግበት እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ በጥናቱ ላይም ውይይቶች መደረጋቸውንና ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

የኢሕአዴግ ውህደት ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ከማንነት ጋር በማስተሳሰር ማስኬድ እንደሚቻል፣ ውህደት ለመፍጠርም በብሔራዊ ድርጅቶችና በኢሕአዴግ ደረጃም ውይይቶች መደረጋቸውንና ቀጣይ ውይይቶች እንደሚኖሩም አስረድተዋል፡፡

የውህደት ሐሳቡ አስፈላጊነትን በተመለከተ ግንባር ቀደም ሚና የሚያራምዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ በአዲስ አበባ አድርጎት የነበረውን ስብሰባ አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ አሁን ያለው የኢሕአዴግ አደረጃጀት የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ የማያስችል እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው በዚህ መግለጫ የኢሕአዴግ አደረጃጀትን በማዘመን በዘመናዊ አሠራር የሚመራ ፓርቲ ለመመሥረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሐሳብን በመደመር ሐሳብ ለመተካት ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን ገልጾ፣ የመደመር ሐሳብ ከዚህ ቀደም የነበሩት ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና የአዲሱን ትውልድ መብትና ጥቅም ያስከብራል ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡

በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ባሉበት አገር ውስጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አማራጭ የሌለው ስለሆነ፣ ኦዴፓ ብዝኃነትን ማዕከል ያደረገ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲገነባና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት እንዲከበር የማያወላዳ አቋም እንዳለው ገልጿል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የሚሰበሰበው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በግንባሩ ውህደት ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ግንባር የፈጠሩት ፓርቲዎች እንዲዋሀዱ የሚፈቅድ የውሳኔ ሐሳብ የሚያሳልፍ ከሆነ፣ የውሳኔ ሐሳቡ በቀጣይ ለኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡

ይህንን ሒደት ማጠናቀቅ ከቻለ ኢሕአዴግ ግንባርነቱን አፍርሶ ለመዋሀድ መወሰኑን የሚገልጹ ማስረጃዎችን በማቅረብ፣ አዲሱን ውህድ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብ ያደርጋል፡፡

በአዲሱ የምርጫና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሠረት ውህድ ፓርቲውን ለማስመዝገብ ከሚቀርቡ ሰነዶች መካከል፣ የሚዋሀዱት ፓርቲዎች በተናጠል ጠቅላላ ጉባዔያቸው ውህደቱን ተቀብለው መወሰናቸውንና የግንባሩ ጠቅላላ ጉባዔ ውህደቱን ፈቅዶ ስለመወሰኑ የሚያስረዱ ሰነዶች ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

በውህደቱ ያልተስማማ የግንባሩ አባል ፓርቲ የራሱን ሕጋዊ ሰውነት ይዞ መቀጠል የሚችል ሲሆን፣ ውህደቱን ከተቀበሉ ፓርቲዎች ውስጥ በውህደቱ የማይስማሙ የፓርላማ ተመራጭ የሆኑ አባላት ቀሪ የምርጫ ዘመናቸውን የግል ተመራጭ እንደሚሆኑ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ምርጫ በሚደረግበት ወቅት ውህደት የሚፈጽሙ ፓርቲዎች ውህደቱን በማስመዝገብ ዕውቅና ለማግኘት ማመልከት የሚጠበቅባቸው፣ የዕጩዎች ምዝገባ ከመጀመሩ ከ90 ቀናት በፊት መሆን እንዳለበትም አዋጁ ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...