Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሩብ ዓመቱ አትራፊ ከተባሉ የልማት ድርጅቶች ሜቴክ 42 ሚሊዮን ብር በማትረፍ ከዋናዎቹ ተርታ ተመደበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አምና ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስመዝግቦ ነበር

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በሥሩ ከሚያስዳድራቸው መካከል በማኑፋክቸሪንግ መስክ ከአምስቱ ድርጅቶች፣ በሩብ በጀት ዓመቱ 41.76 ሚሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብ አትራፊ ከተባሉ ድርጅቶች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደተሠለፈ ኤጀንሲው ይፋ ተደረገ፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ከታክስ በፊት 174 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝገበዋል ካላቸው አምስት ተቋማት መካከል፣ ሜቴክ በ42 ሚሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብና ከፍተኛ አፈጻጸም በማሳየት ሁለተኛው አትራፊ ድርጅት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ትልቁን ትርፍ በማስመዝገብ ቀዳሚ የተባለው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋሪካ ሲሆን፣ ከ174 ሚሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 89 ሚሊዮን ብር በማትረፍ ከተቀሩት አምስት ድርጅቶች የ30 በመቶውን ድርሻ ወስዷል፡፡

ሜቴክ የ24 በመቶ ገደማ የትርፍ ድርሻውን በመያዝ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ከኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማኅበር የተሻለ ትርፍ ከታክስ በፊት በማስመዝገብ ሩብ ዓመቱን እንዳጠናቀቀ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ሜቴክ በሥሩ በርካታ ተቋማት እንደ መኖራቸው፣ የትኞቹ እንዳተረፉ፣ የትኞቹ እንደከሰሩ፣ በየትኛዎቹ ሥራዎቹ የተጠቀሰውን ትርፍ እንዳስመዘገበ፣ በተለያዩ ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንቶች፣ እንዲሁም የባንክ ዕዳዎችና ሌሎችም ተከፋይ የዕዳ ጫናዎች በምን አግባብ ታይተውና ተስተናግድው አትራፊ ወደ መሆን ተሸጋገረ ለሚሉት ዝርዝር የሪፖርተር ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ከሜቴክ ቀጠሮ ቢሰጥበትም፣ ከልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለመገንዘብ እንደተቻለው በዚህ ዓመት ሜቴክ ለማከናወን ካቀዳቸው ሥራዎች ያስመዘገበው ውጤት ነው፡፡ በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው በርካታ ተቋማት የተገኘው አጠቃላይ የትርፍ መጠን እንጂ፣ አንዳንዱ ድርጅት ኪሳራ እንዳስመዘገበም አቶ ወንዳፍራሽ አስረድተዋል፡፡

ከ13 ያላነሱ ድርጅቶችን በሥሩ የሚያስተዳድረው ሜቴክ፣ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ዕዳ ውስጥ 57 ቢሊዮን ብር በዕዳ መያዙ ቀርቶ ወይም ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞርለት ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ እንደተደረገበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በተቋሙ የተሳሳተ አካሄድ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንደተመዘገበበት ለመገናኛ ብዙኃን የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሀምዛ መግለጻቸው ተዘግቦ ነበር፡፡

ይህንን ዕዳም በ15 ዓመታት ውስጥ ለመክፈል ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጉምሩክ ኮሚሽን የሚፈለግበት 12 ቢሊዮን ብር ዕዳ እንዲሰረዝለትም ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ ዕዳ እያለበት በሩብ ዓመቱ የ42 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ይፋ ሆኗል፡፡

ሜቴክን ጨምሮ አምስቱ የልማት ድርጅቶች በሩብ ዓመቱ በጠቅላላው 2.27 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የፋብሪካ ምርቶችን በማቅረብ፣ የሽያጭ ገቢ ማስመዝገባቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡ ይህም የዕቅዳቸውን 75.5 በመቶ ሲሆን፣ ለሩብ ዓመቱ የታቀደው የሽያጭ ገቢ መጠን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በሩብ ዓመቱ ከታክስ በፊት አምስቱ ድርጅቶች ያተርፋሉ ተብሎ የታቀደው መጠን 234 ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች