የፈቃድ አሰጣጥ ማዕቀፉን በሚደነግገው ሰነድ ላይ ሕዝባዊ ምክክር ተደረገ
መንግሥት የቴሌኮሙዩኔኬሽን ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ በወሰነው መሠረት፣ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሁለት ኩባንያዎች ለ15 ዓመታት አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉበት ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ታወቀ፡፡ ኩባንያዎቹ በግልጽ ጨረታ የሚገቡበት የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ባልቻ ሬባ ከገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ጋር ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት፣ ወደ ኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ እንዲገቡ ፈቃድ የሚሰጣቸው ኦፕሬተሮች ለ15 ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ የፈቃድ ጊዜው ሲያበቃም እንደ ሁኔታው እየታደሰ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን የቴሌኮምና የፖስታ አገልግሎቶች ለመቆጣጠር ባለፈው ዓመት በአዋጅ የተቋቋመውና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ተመሥርቷል፡፡ በእነዚህ የአገልግሎት መስኮች የሚሰማሩ ኩባንያዎች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች፣ የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች፣ ገበያውንና የአገልግሎት ዋጋን ወይም ታሪፍን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ባለሥልጣኑ፣ ከአምስት ወራት በኋላ ወደ ቴሌኮም ኢንዱስትሪው እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ሁለት ኩባንያዎችን ጨምሮ፣ ዘርፉን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል፡፡
ከአምስት ወራት በኋላ በሚካሄድና በውድድር ላይ በሚመሠረት ግልጽ ጨረታ ወደ ቴሌኮም አገልግሎት እንዲገቡ የሚደረጉ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እያሳወቁ እንደሚገኙ ቢታወቅም፣ መንግሥት ከወዲሁ መርጦ የያዛቸው ተጫራቾች እንደሌሉና ጨረታውም በመጪው መጋቢት ወር እንደሚካሄድ ብሩክ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡ የውጭ መገናኛ ብዙኃን እስካሁን ስምንት ኩባንያዎች መመረጣቸውንና ከእነዚህም ውስጥ የመጨረሻዎቹ ተጫራቾች እንደሚለዩ መጻፋቸው ስህተት እንደሆነ ያስታወሱት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ይልቁንም ስምንቱ ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል የማዛወር ሒደት እንዲያማክሩ ጥሪ በተደረገው መሠረት የቀረቡ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡
የጨረታውን ሒደትና ኩባንያዎቹ ፈቃድ የሚያገኙበትን ጨምሮ የውድድር ሥርዓቱን ለመቆጣጠር የሚረዳ ረቂቅ ሰነድ በድረ ገጽ ይፋ መደረጉን፣ ይህንኑ መነሻ በማድረግም ለአንድ ወር የሚቆይ የሕዝብ ሐሳብ ማሰባሰቢያ ሥራ በድረ ገጽና በሌሎችም መንገዶች እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው የሕዝብ ምክክር መድረክም ከባለሀብቶችና ከዘርፉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለድርሻዎች ጋር ማክሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የሪፎርም እንቅስቃሴና በቴሌኮም መስክ እየተደረገ ስለሚገኘው የፕራይቬታይዜሽን ሒደት አብራርተዋል፡፡