ሠናይት ፍሥሐ (ፕሮፌሰር) በአሜሪካ ሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋኩልቲ የጽንስና ማኅፀን ሐኪምና የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ የመጀመርያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ አቅንተው በባዮ ኬምስትሪ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በጽንስና በማኅፀን ሕክምና ስፔሻላይዝ ከማድረጋቸው አስቀድሞም የሕግና ሕክምና ትምህርቶችንም ተከታትለዋል፡፡ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍም ተመርቀዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የጤና ዘርፍና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አሜሪካ ትምህርት ላይ እያሉ ወደ ኢትዮጵያ በመመላለስ ዕገዛ ለማድረግ እንደሞከሩ፣ ተመርቀውም ሥራ ከያዙ በኋላ ሙከራዎትን አጠናክረው በመቀጠል በጤናው ዘርፍ ላቅ ያለ አገልግሎት እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡ ለዚህ ምን አነሳሳዎት?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- የትም እንኑር የትም ሁላችንም አንድ ቤትና አንድ አገር ነው ያለን፡፡ ወደ አሜሪካ የሄድኩት አገሬን ጠልቼ ወይም ሸሽቼ ሳይሆን ለትምህርት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አሜሪካ ገና በትምህርት ላይ እያለሁ በሐሳቤ ሁልጊዜ የማጠነጥነው ወደ አገሬ ተመልሼ ወገኖቼን በምን መልኩ ነው የምረዳው? የሚለውን ነበር፡፡ በተለይ ባለሁበት አገር ያየሁት የትምህርትና የሕክምና ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የሚሸጋገረው እንዴትና መቼ ነው የሚለውን ማሳካት የዘወትር ምኞቴ፣ ፍላጎቴና ዕቅዴ ነበር፡፡ ተማሪ እያለሁ ወደ አገሬ እየመጣሁ ሐሳቤንና ዕቅዴን ዕውን የማደርግበትን ሁኔታ ማጠንጠን ጀመርኩ፡፡ በዚህም አንድም ሐሳቤን የሚቀበልና ለጥረቴ መሳካት ዕገዛ የሚያደርግልኝ አካል አጣሁ፡፡ በዚህም ተስፋ ሳልቆርጥ ትምህርቴን ጨርሼ ሥራ እንደጀመርኩ ወደ ኢትዮጵያ ስመላለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ሚሊያርድ ደርበው (ዶ/ር) ጋር አብሬ መሥራትን ተያያዝኩት፡፡ እሳቸውም አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል ተገቢውን ዕገዛና ድጋፍ በስፋት ዘሩጉልኝ፡፡ ቀጥሎም በአሁኑ ጊዜ የዓለም ባንክ ዋና ዳይሬክተርና የቀድሞ ጤና ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ጋር ተዋወቅኩ፡፡ ሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ የተወሰኑ ሐኪሞች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ እየመጣን አልፎ፣ አልፎ ሌክቸር በማድረግ፣ በማስተማርና የቀዶ ሕክምናን በማገዝ እንድንሠራ ተባበሩን፡፡
ሪፖርተር፡- አገልግሎታችሁ በዚህ ብቻ ተወሰነ? ወይስ ቀጠለ?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- ለአንድ ሳምንት ያህል እያስተማርን የዕውቀት ሽግግር ካከናወንን በኋላ እንመለስ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱን ዕገዛ ለዘለቄታው መሬት ለማውረድ አሰብኩ፡፡ ‹ዶ/ር ቴድሮስ ጠቅላላ ሐኪሞችን በብዛት እናስመርቃለን፣ ስፔሻላይዝ የሚያደርግ ግን የለም፡፡ ስለሆነም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ ለማቋቋም አስበናል፡፡ በዚህ ዙሪያ ልትረጅን ትችያለሽ ወይ?› ብለው ጠየቁኝ ተጨባጭ የሆነና መሬት ላይ የወረደ ሥራ መሥራት አለብን የሚል ሐሳብ እያለኝ ከቀድሞው ጤና ሚኒስትር ይህ ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብልኝ ደግሞ ሐሳቤን ተግባራዊ የማደርግበት መንገድ እንደተከፈተልኝ በመረዳት ለጥያቄያቸው የአዎንታ መልስ ሰጠሁ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ሄደው በጉዳዩ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ጋር እንዲወያዩበት ጠየኳቸው፡፡ ይህ ዓይነቱም ውይይት እኔ ያለምንም ችግር እየመጣሁ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚያስችለኝ ነገርኳቸው፡፡ እርሳቸውም ከዚህ መሠረተ ሐሳብ በመነሳት ወደ ዩኒርሲቲው ሄደው ከኃላፊዎቹ ጋር በመወያየት ለሥራውና ለአገልግሎቱ ስኬታማነት ምቹ መደላድሎችን ፈጠሩ፡፡ በተፈጠረውም ምቹ መደላድል በመጠቀም ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በየወሩ ለ15 ቀናት ያህል ወደ አገሬ እየተመላለስኩ ማገልገሌን ተያያዝኩት፡፡ በዚህም አገልግሎቴ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅን በማቋቋም እንዲሁም የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምናን በማጠናከርና የስፔሻላይዜሽን ፕሮግራም እንዲጀመር፣ ተማሪዎቹም የሕዝባቸውን ችግር እንዲረዱት ለማድረግ የሚያስችል የሥነ ምግባር ትምህርት በመስጠትና በሕክምና ዓለም ውስጥ እስከቆዩም ድረስ ታካሚዎችን ከመንከባከብ አልፎ ርኅራኄ እንዲያድርባቸው ለማድረግ በተከናወነው ሥራ ላይ የበኩሌን አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹ምቹ›› በሚል መጠሪያ የሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራም የሚከናወንባቸው 12 ክሊኒኮችና አንድ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል በማቋቋም እንቅስቃሴ ላይ የሚጠበቅብኝን ግዴታና ኃላፊነት ተወጥቼያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ምቹ›› ክሊኒኮች የት ነው የተቋቋሙት? ‹‹ምቹ›› የተባሉበትም ምክንያት ምንድነው?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- የመጀመርያው ‹‹ምቹ›› ክሊኒክ የተቋቋመው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ 22 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ በጋንዲና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ውስጥ አንዳንድ ‹‹ምቹ›› ክሊኒኮች ተቋቁመዋል፡፡ የቀሩት ስምንት ‹‹ምቹ›› ክሊኒኮች የተቋቋሙት ደግሞ ሐሮሚያ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ደብረታቦርና አሰላ ዩኒቨርሲቲዎች ነው፡፡ አመሠራረታቸውም የአገሪቱን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በመመልከትና ፍትሐዊነትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ‹‹ምቹ›› የተባሉበትም ምክንያት ቃሉ በአማርኛና በኦሮሚኛ የተመቸ የሚልና አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ፍቺ ስላለው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ምቹ›› ክሊኒኮችን ለማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ቢገለጽልን?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- አንዲት ሴት ልጅ የወር አበባዋ መምጣት ወይም መታየት ከጀመረበት ቀን አንስቶ እስከ ምታቆም ድረስ የተለያዩ ችግሮች ይፈራረቁበታል፡፡ ከችግሮቿም መካከል የወር አበባዋ መምጣቱ በራሱ አንድ ችግር ሲሆን፣ ማርገዝና አለማርገዝ፣ መውለድና አለመውለድ ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፍ ችግሮቿ ናቸው፡፡ የውስጥ ደዌም አንደኛው ችግር ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ በሕክምና ለመከላከል የሚቻሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የተዘረዘሩት ክሊኒኮች ችግሮቹ በሕክምና ሊቆሙ ወይም ሊገቱ የሚችሉባቸውን የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም ለእናቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ 22 አካባቢ ያለው ‹‹ምቹ›› ክሊኒክ ከተጠቀሱት አገልግቶች በተጨማሪ መውለድ ለተሳናቸው ጥንዶች የሚወልዱበትን ሁኔታ የሚያመቻች ብቸኛ ክሊኒክ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሥነ ተዋልዶ ጤና ሥልጠና ከሌሎች ለየት የሚደርገው ምንድነው?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- ሥልጠናው ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ በቅድሚያ የሕክምናው ትምህርት ይጨረሳል፡፡ ከዚያም ሬዚደንታል ስፔሻላይዜሽን በጽንስና ማኅፀን ዙሪያ የመስጠት ሥራ ይቀጥላል፡፡ ይህም እንዳበቃ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት/ሥልጠና ይቀጥላል፡፡ ይህ ዓይነቱንም የሥልጠና ሒደት ለማገዝ በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ያላቸው የሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት እየመጡ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፣ እያበረከቱም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ውስጥ በሴቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያስቀመጠውን ዕቅድ በጥሩ ሁኔታ በማሳካት ከፍተኛ ለውጥ እንዳስመዘገበ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ከ100,000 ወላዶች መካከል 1,000 የሚደርሱት ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ቁጥር ቀንሶ ወደ 300 ተጠግቷል፡፡ ይህም ቢሆን አሁንም ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ጅምር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በጤና ኤክስቴንሽን አማካይነት በተከናወነው ሥራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር እንደሚኖር ተነግሮናል፡፡ ገጠሩ ደግሞ በየአቅራቢያው የጤና ተቋም የለም፡፡ ተቋም ቢኖር እንኳን የሠለጠነ ባለሙያ አይገኝም፡፡ ባለሙያው ቢኖር ደግሞ ለሥራ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችና ግብዓቶች አለመኖር ችግሩን ያወሳስቡታል፡፡ መንግሥት የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑንም መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከሚካሂዱትም እንቅስቃሴዎች መካከል አቅም በፈቀደ መጠን የጤና ኬላዎችን መገንባት፣ ባለሙያዎችን ማሠልጠን፣ ተፈላጊ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎቹን ወይም ዕቃዎችን ማቅረብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች በማሳካት፣ በወሊድ ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጉ የነበሩ እናቶችን በመታደግና ሞትን በመቀነስ፣ የቤተሰብ ምጣኔን በማበልፀግና ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና መመርያዎች ሲወጡ ይስተዋላሉ፡፡ አብዛኛዎቹ መሬት ላይ ሲወርዱ እምብዛም አይታዩም፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?
ፕሮፌሰር ሠናይት፡- ሴት ልጆችን የሚጎዱ አጉል ልማዶች አሉ፡፡ እነዚህን አጉል ልማዶች የሚቃወሙ ሕጎችም ሲወጡ እናስተውላለን፡፡ ከእነዚሀም መካከል አንደኛው ከ18 ዓመት በታች የሆነች ሴት ልጅ እንዳትዳር የሚከለክል ሕግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕግ ቢወጣም በየገጠሩ ያሉት የ12 እና የ18 ዓመት ሴት ልጆች ሲዳሩና ሲውለዱ ይስተዋላል፡፡ እነዚህም ሴት ልጆች ሰውነታቸው ለመውለድ ያልደረሰ ከመሆኑ የተነሳ ለልዩ ልዩ የጤና ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ ከጤና ችግሮቹም ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰውነቷን የሚጎዳና ለሞት የሚዳርገው የፌስቱላ ችግር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከትምህርት ገበታዋ ማቋረጥ ነው፡፡ 98 ከመቶ ያህል ሴት ልጆች በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቢታዩም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ያቋርጣሉ፡፡ በጣም እየተስፋፋ የመጣው ደግሞ የሴት ልጅ መደፈር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሴት ልጅ ያለፍላጎቷ፣ ያለ ጊዜዋና ያለ ዕቅዷ ከመውለዷ በተጨማሪ ለሥነ ልቦና ጉዳት ትዳረጋለች፡፡ እነዚህን መቅረፍ የሚቻለው መንግሥት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡ ትብብር ሲታከልበትም ነው፡፡