በንጉሥ ወዳጅነው
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብዝኃነት ከአገሮች ሁሉ የተለየ አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር የተፈጥሮ ፀጋዎቻችን፣ የምንገኝበት መልክዓ ምድርና የሕዝብ ብዛታችንም ቢሆን ከሁሉም የተነጠሉ የሚያስብለን አይደለም፡፡ ምናልባት ከሌላው ዓለም የተለየን የሚያስብሉን ድህነታችንና በቀደሙት ዘመናት በአስከፊነታቸው የሚጠቀሱ የድርቅና ችጋር ታሪኮቻችን ናቸው፡፡ በእርግጥ አትሌቶቻችንን በመሰሉ ድንቅ ዜጎቻችን አገራችን በበጎ መጠቀሷም አይቀር ይሆናል፡፡ ቀደምት የሥልጣኔና የጀግንነት ታሪካችንም ሊቀበር የማይችል ነው፡፡ እነዚህ መልካምም ይሁኑ መጥፎ ገጽታዎች ታዲያ እንደ አገር የምንታወቅባቸው እንጂ፣ የአንዳችን ወይም የሌላችን መልክ ሆነው አይቀርቡም፣ ሊቀርቡም አይችሉም፡፡ ታዲያ መለያየትንና መጠቃቃትን ምን አመጣው?
በእርግጥ ዓለም እንደ አንድ አገር ቆጥሮ በሁሉም ታሪኮቻችን በጋራ ቢገልጸንም፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድና በተመሳሳይ ታሪክ ያለፍን ነበር ማለት ግን አይደለም፡፡ እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ በአገራችን ፊውዳላዊ ገዥዎች ከአንዱ ማኅበረሰብ ወጥተው በየማኅበረሰቡ መደባቸውን የሚመስል ጨቋኝና በዝባዥ እየፈጠሩ ዜጎችን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በድለዋል፡፡ ዜጎች በማንነታቸው፣ በቋንቋቸውና በእምነታቸው እንዳይገለገሉም መገደዳቸው አይካድም፡፡ ይህ ግን በምንም ተዓምር ሕዝብ በሕዝብ ላይ የፈጸመው ድርጊት አልነበረም፡፡
እንዲያውም የአገዛዞች ጭቆና ዘርና ማንነት ሳይለይ ሁሉንም የበደለ ቢሆንም ድርብ ጭቆና የደረሰባቸው የአገራችን ሕዝቦች እንደነበሩ ሊካድ አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት አገራችን ለዘመናት በኋላቀርነትና በድህነት እንድትማቅቅ ተፈርዶባት ቆይታለች፡፡ የፀብ፣ የግድያ፣ የአሸናፊና ተሸናፊ ጨዋታ ነግሶ የጥላቻ ትርክት ገንግኖ ውስጥ ውስጡን ሥር መስደዱም ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡
በእርግጥ ካለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ በየአካባቢው ሕዝቡ ትግል አድርጎ፣ አምባገነናዊ ወታደራዊ ሥርዓትን በመቀየር ፌዴራላዊና ዴሞክራስያዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን በአፈፃፀሙ የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም በየመስኩ የመጡ መልካም ጅምሮች እንደነበሩም መካድ ያስቸግራል፡፡ በተለይ በማኅበረ ኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ዘርፍ አገሪቱ ከነበረችበት የጭራነት ደረጃ ቀና እንድትል መደረጉ የሕዝብና የመንግሥት ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በዚያው ልክ በአገሪቱ የተጀመረው ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ለሕዝቦች እኩልነት፣ ባህልና ታሪክ መተዋወቅ የሰጠውን ዕድል ያህል ለሕዝቦች አብሮነትና ቅርርብ የጎላ ሚና መጫወት ያልቻለ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በተለይ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ዕቅድ እንደሚመቻቸው ታሪክ እያዛቡ በፈጠሩትና ለዓመታት በረጩት የጥላቻ ትርክት መነሻ በሕዝቦች መካካል የተዘራው ቂምና የበቀል ስሜት በቀላሉ የሚነቀል አልሆነም፡፡ (እዚህ ላይ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የሆነውን ተከትሎ የቀድሞ የኢሕዲን መሥራች አቶ ያሬድ ጥበቡ ያነሳቸውን ተጨባጭ ነጥቦች መመርመር ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡)
በመቼውም ጊዜ ቢሆን ገዥዎችና አምባገነን መሪዎች የወጡበትን ማኅበረሰብ እንደማይወክሉ እየታወቀ፣ ለዘመናት በድህነትና በተቀራራቢ የኑሮ መደብ ማዕቀፍ ውስጥ የኖረን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲባላ ማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግፍ ተፈጸመ፣ ስህተት ተሠራ ከተባለበት ጊዜ አልፎ አራትና አምስት ትውልድ ካለፈ በኋላ (በትንሹ ከ125 ዓመት በኋላ) በእውነቱም በሐሰቱም ትርክት እየተቀባባ በሚነዛ ጥላቻ፣ ትውልድ በትውልድ ላይ ካራ ማንሳቱ የመጨረሻው ኋላቀርነት ነው፡፡
የዘር ፖለቲካው ጡዘት ‹‹የሞት ፍሬ›› ሲያሳፍስ!
ያለ ይሉኝታ እንነጋገር ከተባለ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም በአንድ አገር በአንድነት ለመኖር ሳይሆን፣ በብሔር ስም ‹‹ነፃ ለመውጣት›› የተቀነባበረ ሥርዓት ነው የሚሉ ወገኖች ትንሽ አይደሉም፡፡ በእርግጥ ትናንትም ሆነ ዛሬ ይህን አስተሳሳብ ያለ ምንም ዓይነት ማሻሻያ እንዲቀጥል የሚፈልጉት እነማን መሆናቸው ሲታወቅ፣ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሀቅ ይታያል፡፡ አሁን የለውጥ ንፋስ ሲነፍስ፣ አገር ወደ መደላድልና ብዙኃኑ ሕዝብ የሚጠቀምበት ጥርጊያ ከምትሄድ ተተራምሳ እስከማለት ፅልመት ውስጥ የሚገቡ የሚመስሉትም የዚሁ አስተሳሳብ ተጋሪዎች ናቸው፡፡
በመሠረቱ የኢትዮጵያ የአራት አሥርት ዓመታት የፖለቲካ ትግል ጉዞው ከመደብ ይልቅ በብሔር የመብት ጥያቄ ላይ ተጠንስሶ፣ በልዩነት መዘውርና በነጣጣይ ፖለቲካ ትርክት ተረግዞ የወለደልን አክራሪ ብሔርተኝነትን፣ የፖለቲካ ጥላቻና መገፋፋትን ነው፡፡ ሥርዓቱ በተለይ ደግሞ ከተለያዩ ብሔረሰቦች ተወልደው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ወገኖችን እንደ ባዕድ የሚገፋ ነው፡፡
ያም ሆኖ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ይነስም ይብዛ በኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ በመቆየቷ፣ መንግሥትም ሲፈልግ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ካባውን ስለሚደርብ፣ ቁርሾውና የብሔር ግጭቱ የተሸረበውን ሴራ ያህል የከፋ አልነበረም፡፡ የመዳፈን ሁኔታም ታይቶበት ነበር፡፡ አሁን ግን ‹‹ለውጥ መጣ!›› ሲባል እንደ እንጉዳይ በየቦታው የፈላው መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ አሰቃቂ ግድያና የዘር ጥቃት ነው፡፡ የተዳፈነው የዘረኝነትና የጥላቻ እሳት በፅንፈኛ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ተንቀልቅሏል፡፡ ሰደድም እየሆነ አገር ማጋየት ጀምሯል፡፡
የብሔር ቀውሱ ከዚህ ቀደም በጋምቤላ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በጉራፈርዳና… መሰል አካባቢዎች የተፈጸመውን እንኳን ብናሰላው፣ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ተባብሶ ያደረሰው ጠባሳ ግን በጥቁር ታሪክ የሚመዘገብ ነው፡፡ በየክልሉ ‹‹መጤ›› የተባለው የሌላ አካባቢ ዜጋ በተለይ ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌና ከአማራ ክልሎች መግቢያ መውጫ እስኪያጣ ሲሳደድ ከማየት በላይ አስፋሪ ጊዜ አይገኝም፡፡
ሲቀጥል በክልል ደረጃ ተደራጅተው የነበሩት ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በፀጥታ አካላት ጭምር ተጋጩ፣ ብዙዎች ሞቱ፣ ቆሰሉ፣ ንብረት ወደመ፡፡ አልፎ ተርፎ ሚሊዮኖች ለመፈናቀልና ለመበተን ተዳረጉ፡፡ የትግራይ ተወላጆቾችም በየአካባቢው የደረሰባቸው ጫና እንደነበርና ለመፈናቀል መጋለጣቸው አይዘነጋም፡፡
በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች የሆነውንም እናስታውሰዋለን፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መሀል ከመለስተኛ ግጭቶችና ውዝግቦች ባሽገር ያረገዘው ፍጥጫ ለትውልድም የሚተርፍ እየመሰለ ነው፡፡ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካካልም የይገባኛል ውዝግብ ግጭት አስነስቶ ዓይተናል፡፡ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን፣ በአማራና በጉምዝ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም በመሀል አገር አዲስ አበባ ፊንፊኔ እየተባለ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ረግፈዋል፡፡ ዋነኛው ግጭት፣ የንፁኃን ጭንቀትና ጉዳት ሁሉ መነሻውም መድረሻውም የዘር ፖለቲካ መሆኑን መካድ ፈጽሞ ከማይቻልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የጥላቻ ትርክትና ስግብግብነት ያመጣው ዳፋም ነው፡፡
ግጭቱ በአንድ መንደር ለዘመናት እየኖረ፣ ‹‹እኔ የራሴ ማንነት አለኝ/የለህም›› የሚለውንም ሳይቀር እያባላው ነው፡፡ አማራና ቅማንት፣ ሲዳማና ሌላው ደቡብ፣ አፋርና ኢሳ፣ የወልቃይት ማኅበረሰብ… ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አሁን ማን ይሙት ለበርካታ መቶ ዓመታትና ለዘመናት አብሮ ከመኖር አልፎ በአንድ ዓይነት ታሪክና ማንነት ውስጥ የዘለቀው፣ ከመጋባትና ከመዋለድም በላይ መከራና ሐዘኑን ለዘመናት በጋራ ያስተናገደው ሁሉ፣ እንዲህ ጦር እየተማዘዘ ይገዳደላል ብሎ የሚገምት ነበር? ጠባብ ብሔርተኝነትና የጎሳ ፌደራሊዝም ግን ውጤቱ ይኼው ብቻ ነው፡፡
ከሰሞኑ እንደታዘብነው ደግሞ መነሻው ምንም ይሁን ምን በኦሮሚያ ክልል ከብሔርም አልፎ ወደ እምነት ግጭት የቀረበ፣ 86 ንፁኃንን በጭካኔና በአረመኔነት የረገፉበት ትራጄዲ ተፈጽሟል፡፡ ቀላል ግምት የማይሰጠው የሕዝብና የግለሰቦች ሀብት ወደሟል፡፡ ከዚያም አልፎ ብዙዎች በማንነታቸውና በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ተፈናቅለዋል፡፡ ከመቼውም በባሰ ደረጃ በፀጥታ ኃይሉ እንኳን ሳይተማማኑ ተስፋ ቆርጠው ተቀምጠዋል፡፡ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ የማይመጥን ወራዳና አሳዛኝ ተግባርም በፅንፈኞች ለመፈጸም በቅቷል፡፡
እንግዲህ ይህ ሲታይ ነው ያለ ይሉኝታ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ ብሎም በሐሳብ ትግል ዘረኝነትና ጠባብነትን መጋፈጥ ግድ ይላል መባሉ፡፡ ሥርዓቱም የሕዝቦች መብትና እኩልነትን ያክብር እንጂ፣ የአገር መበተንን አያበረታታ የሚባለው፡፡ አሁንም በአክራሪ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም መንገድ የሚነዱንን የብተና አርክቴክቶችም ሕዝቡ ታግሎ ማስቆም ግድ የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ አሁን አገር ከገባችበት የዚህ ዓይነቱ የውድቀት ምዕራፍ ለማላቀቅ ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና መፍትሔዎችን በዚህ ጽሑፍ ለማመላከት ተሞክሯል፡፡
አንደኛው አንድነትን ሳያወላውሉ ማጠናከር!
ፌደራሊዝም ለአገራችን ብዝኃነት ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ ነገር ግን ብሔር ተኮርና ነጣጣይ መሆኑ ለማንም ጠቃሚ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሕዝቡን ፖለቲከኞች እያሳሳቱት እንጂ፣ አብዛኛው በዚህ መንገድ ጥቅሙ እንዳልተከበረ የታወቀ ነው፡፡ በእርግጥ ለጥቂት አናሳ ዘራፊዎችና የፖለቲካ ነጋዴዎች አገልግሎ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ውስጥ ብርቱ የሆነ አንድነትና አብሮነትን መፍጠር፣ ዜጎች ከማንነታቸውም በላይ በዜግነታቸው መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ወሳኝና አስፈላጊ ዕርምጃ ነው፡፡
በመሠረቱ ሥልጡን በምንላቸው ወይም በዕድገት ግስጋሴ ምኅዋር ውስጥ ባሉ አገሮች የዜግነት ፖለቲካን መሠረት ያደረገ አገራዊ አንድነት እንጂ፣ አክራሪ ብሔርተኝነት የተደፈቀ አጀንዳ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የብዙ ጉዳዮች አርዓያ የምትባለው አሜሪካ ሕዝብን ልምድ ብንወስድ የመጀመርያ መርህ ‹‹አንድ ከሆንን እንቆማለን፣ ከተከፋፈልን እንወድቃለን!›› (United We Stand, Divided We Fall!) የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አሜሪካውያን በአንድነታቸውና በሕገ መንግሥታቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውም በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላው ይቅር ብዝኃነት ያለው ሕዝብ በአንድ ሉዓላዊ ምድር እንደ መገኘቱ የአሜሪካ ሕዝቦች ሳይሆን ‹‹ሕዝብ›› የሚል የአንድነት ብያኔን መቅረፃቸው ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡
እነሱ በታሪክ እንደሚታወቀው ከዚያና እዚህ ተቀላቅለው (ስፓኒሽ አሜሪካ፣ ፖርቱጊዝ አሜሪካ፣ አፍሪካን አሜሪካ፣ ሞንጎላይድ፣ ኔግሮይድ፣… ያውም በከፍተኛ ግጭትና በቁርቁስ) የገነቧትን አገር በአንድነት ገመድ እያስተሳሰሩ ለእኛ ግን፣ ነጣጣይና ዘረኛ መና ከመመገብ ወደ ኋላ እንደማይሉ የታወቀ ነው፡፡
በእኛ በኩል ግን ሌላው ገፋንም ደገፈን በራሳችን አገራዊ የአንድነት ታሪክ ላይ ስህተትን አርመን፣ ጥንካሬን አስቀጥለን አለመቆማችን የሚያስቆጭ ነው፡፡ በተለይ ለዘመናት በአንድነት የኖርን ሕዝቦች እንደ መሆናችን ጎዶሎውን ሞልተን ከመጠናከር ይልቅ፣ መሰነካከላችን በታሪክ የማይረሳ የትውልዱ ውድቀት ነው፡፡
አሁን ለውጡ ሲጀማምርም በዴሞክራሲያዊነትና በአንድነት መንፈስ መቀጠል ሲገባን፣ መልሰን በዘር ፖለቲካና በአክራሪ ብሔርተኝነት ውስጥ መዘፈቃችን እያስከፈለን ያለው ውድ ዋጋ እየሆነ ነው፡፡ ሁሉም ተባብሮና ልብ ገዝቶ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱንና የሕዝቦች እኩልነትን ያጠናክር፡፡ ያለበለዚያ መጪው ጊዜ ይበልጥ ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው መባሉም ለዚሁ ነው፡፡
ሁለተኛው የአገር ሰላምን መጠበቅ!
በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ የአገር ደኅንነትና የሕዝቦች መተማማን ወሳኝ እንጂ፣ ትንሽ ተግባር አይደለም፡፡ እኳንስ ለሺሕ ዘመናት አገረ መንግሥት ገንብተው፣ ተጋብተውና ተዋልደው ለዘመናት ተሳስረው ለኖሩ እኛን መሰል ሕዝቦች ይቅርና ለማንም ቢሆን ሰላም የዕድገትና የዴሞክራሲ መሠረት ነው፡፡ ሰላምና አገራዊ ደኅንነት ዕውን የሚሆነው ደግሞ በዋናነት በሕዝቡና በአገር ወዳዱ ዜጋ የነቃ ተሳትፎ እንጂ፣ በመከላከያ ወይም በደኅንነቱና የፀጥታ ኃይሉ መጠናከር ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን የፀጥታና የአገር መከላከያ ኃይሉ ብቃት፣ ቅንጅት፣ ሥነ ምግባርና ሕዝባዊ ባህሪ ወሳኝ አይደለም ማለት አይቻልም፡፡
እስካሁን ባሳለፍናቸው የዘመናዊ አገር ታሪክ ግንባታ ውስጥ (በተለይም ባለፉት ስድስትና አምስት አሠርት ዓመታት) ይህን አገራዊ ሰላም ለአፍታም ሳያንቀላፋ፣ ወትሮ ዝግጁ ሆኖ የሚጠብቀውም፣ በየደረጃው ያለው የፀጥታ ኃይልና ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ነው፡፡ በተለይ መከላከያው ከአገሩ ድንበር ተሻግሮ የዓለምን ወይም የአፍሪካን ሰላም በማስከበር ድንቅ ታሪኩ የሚታወቅ፣ የአፍሪካ ሕዝቦች አለኝታ በመሆን ዝናን ያተረፈ ጠንካራ ኃይል ነው፡፡
ይህ ኃይል ምንም እንኳን በውስጥ ፖለቲካ ብልሽትና በሥርዓት አገልጋይነት ተፈርጆ ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት የመበተን ዕጣ ፋንታ ቢገጥመውም፣ ከዚያም በኋላ የተዋቀረው በዓለም ሕዝብ ፊት ጅግንነቱን ደጋግሞ ያረጋገጠ፣ በወታደራዊ ሥነ ምግባሩ ምሥጉን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ሠራዊቱ በሕዝባዊ ባህርይ የታነፀ የአገር መከታ ሆኖ የሚታየው፣ ነፃነቱን ሳያስደፍር ፀንቶ የመኖር አኩሪ ገድል ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ ያፈራው ስለሆነ ነው፡፡
ይሁንና ይህ ኃይል በአገር ውስጥ የሕዝቦችን ደኅንነትና አንድነትን የሚፈታተኑ ችግሮችን በማስቆምና በመታገል ረገድ ይበልጥ ሕዝባዊነቱ ማረጋጋጥ ይኖርበታል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች እምነትና ከበሬታ እንዲኖረው የማድረግ ጉዳይም ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ በውጭው ዓለም ሰላም ለማስከበር በተሰማራበት አካባቢ ሁሉ ጥልቅ የሕዝብ ፍቅር እያተረፈ የሚመለሰው፣ በሰላም ዕጦት ለተቸገሩ ሕዝቦች ፈጥኖ የመድረስ ድንቅ ታሪክ የገነባው ይህ ሠራዊት በፖለቲካ ብልሽት ምክንያት ለአገሩ ሕዝቦች ይህን ሚናውን መወጣት ካልቻለ አዲስ ውድቀት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ግን ክፍተት እየታየበት ነው፡፡ ሠራዊቱ የአገር ውስጥ ሰላምና የሕዝቦች ደኅንነትን ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በማስከበር ረገድ ክፍተቶች እየታዩበት ነው፡፡ እርግጥ ዓለማው ደም መፋሰስና ግጭትን ለመቀነስ ቢመስልም፣ በሁሉም ክልሎች ወጥ አሠራር ከታየበትና በየክልሉ ካለው ፖሊስና የፀጥታ ኃይል ጋር መተማመንና ቅንጅት መፍጠር ካልቻለ አደጋው መክፋቱ አይቀርም፡፡ አገርንም ያለ ዋስትና ለአደጋ ማጋለጥ ያጋጥማል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በአገሪቱ የለውጥ ጅምር ከመተያየቱ ጋር በተያያዘ፣ የተለያዩ ግጭቶችና አመፃዎች ሲካሄዱ ተስተውሏል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ራሱ መከላከያው ካምፑን ሲያነሳና ከባድ መሣሪያ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ሲሞክር ሊቃወሙ የሞከሩ ወጣቶች ታይተዋል፡፡ በሌላ አካባቢ ደግሞ ዜጎች በእምነታቸውና በማንነታቸው ብቻ በመንጋ ፍርድ ሲገደሉ፣ ሀብታቸው ሲወድምና ሲፈናቀሉ ታይቷል፡፡ መንግሥትና ባለሀብቶች ውድ የሆነውን ሀብት እያፈሰሱ በአመፀኞች ሲወድም መዋል ማደሩም እጅግ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡
ከሁሉ በላይ በአንዳንድ ክልሎች ያለው የፖሊስና የልዩ ኃይል አዝማሚያ፣ ወገንተኝነት የሚስተዋልበትና ዜጎችን ከጉዳት የማይታደግ ሆኖ ሲታይ ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ይህ አዝማሚያ ደግሞ በአገር ውስጥ የታጠቀና የተደራጀ ኃይል ቢያጋጥም አደጋውን ያከፋዋል የሚል ሥጋት ያጭራል፡፡ ስለዚህ ችግር ሊፈጠርባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን ለይቶ፣ ሕዝብን ከጥፋት ቀድሞ በመከላከል ረገድ ገና መጠናከር ያለበት በርካታ ተግባራት መኖራቸው ሊካድ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡
ሠራዊቱ በአገር ውስጥ በሚካሄድ የፀረ ሽብር ዘመቻ፣ በሕዝቦች የእርስ በርስ ግጭትም ሆነ የልማት አውታሮች ላይ በሚፈጸም ጉዳቶች መከላከል ረገድ አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ወይም በቂ ሥምሪት ካልተሰጠው፣ አገርን ለባሰ ችግር የሚዳርግ ነው፡፡ ከምንም በላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና አገራዊ ህልውናን ለተጨማሪ አደጋ የማጋለጥ ፈተናም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ የልማትና የኢንቨስትመንት ጉዳይም ቢሆን ሰላም ሳይኖር ሊታሰብ አይችልም፡፡ ስለዚህ ከሁሉ ቅድሚያ ለአገር አንድነትና ሰላም የሚሉ ጭብጦች ቀዳሚ ሆነው ሊመጡ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡