Tuesday, November 28, 2023

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በወንጀል ለመቅጣት የተረቀቀው ሕግ ፋይዳና ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዋናነት በማኅበራዊ የትስስር ድረ ገጾች እንዲሁም በመደበኛ የመገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም የብሔር ማንነት ላይ መሠረት ያደረጉ የሚዲያ ተቋማት አማካይነት የሚሠራጩ ያልተገሩ ንግግሮች በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በማሳደር የሕዝቦችን መስተጋብር በመሸርሸርና የግጭቶች ምንጭ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ችግሩን ለመከላከል ያስችላል ያለውን የጥላቻ ንግግር አዋጅ በ2011 ዓ.ም. የመጀመሪያ መንፈቅ በማርቀቅ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ከባለድርሻ አካላት የነበረው ግብረ መልስ በሁለት ተገዳዳሪ ፍላጎቶች የተከፈለ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የአዋጁን አስፈላጊነት ሲደግፉ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና የፖለቲካ አክቲቪስቶች በበኩላቸው የሚዲያና ሐሳብን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ ነፃነትን ይገድባል ሲሉ ተቃውመውት ነበር፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕጉን አስፈላጊነት ከሚያምኑ ባለድርሻ አካላት ያገኘውን ግብዓት፣ እንዲሁም ከመንግሥት የወረደውን አቅጣጫ በመቀበል የጥላቻ ንግግር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የነበረውን የመጀመሪያ ረቂቅ በማሻሻል ከጥላቻ ንግግር በተጨማሪ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሠራጨትም ክልከላ የሚደረግበት የወንጀል ድንጋጌ በማድረግ የረቂቅ ሕጉ አካል እንዲሆን አድርጓል፡፡

 በዚህ መሠረት የተቃኘው ረቂቅ ሕግ በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል በፍጥነት ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ በወቅቱ ሲገልጽ የነበረው አርቃቂው አካል፣ ሕጉን የመቅረፅ ኃላፊነቱን አጠናቆ ሰነዱ እንዲፀድቅ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ላይ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ልኳል፡፡

ይሁንና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ሕጉን ሳያፀድቅ ከስድስት ወራት በላይ መቆጠራቸው፣ መንግሥት በሕጉ አስፈላጊነት ላይ የነበረውን አቋም እንደቀየረ በርካቶች እንዲገምቱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶችንና ግጭቶችን በማባባስ የመገናኛ ብዙኃንን የወቀሱ ሲሆን፣ ሁለት ዜግነት ያላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ግጭት ከመቀስቀስ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ካልሆነ ግን መንግሥታቸው ምሕረት እንደማያደርግ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ በመንግሥት ጥበቃ የሚደረግለት የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ባለቤትና አክትቪስት ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች በእኩለ ሌሊት እንዲነሱ መደረጋቸው የፈጠረው ሁከት ይታወሳል፡፡

ተፈጸመ የተባለው ድርጊትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር ተዳምረው ሥጋት የፈጠሩበት ጃዋር መሐመድ የተፈጸመው ተግባር “የግድያ ሙከራ” እንደሆነ አድርጎ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ መግለጹ፣ ይህንንም ተከትሎ ደጋፊዎቹ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ለተቃውሞ መውጣታቸውና ተቃውሞውም ወደ አስከፊ ግጭት በመቀየሩ፣ በሁለት ቀናት ብቻ ከ80 በላይ የሰው ሕይወትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል፡፡

ይህ ክስተት ቀጥታ ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ባይታወቅም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከገባ በኋላ ተዘንግቶ የነበረው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት የወንጀል ተጠያቂነት እንዲጣልባቸው የተረቀቀው አዋጅ የአገሪቱ አመራሮችን ትኩረት በድጋሚ አግኝቷል፡፡

በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ረቂቅ ሕጉን በማፅደቅ ለሕግ አውጭው ፓርላማ መርቶታል፡፡

የረቂቁ ዓላማና ይዘት ምንድነው?

ሪፖርተር ያገኘው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ረቂቅ አዋጅና አባሪ ማብራያ ሰነድ፣ መንግሥት የጥላቻ ንግግርና አደገኛ የሐሰተኛ መረጃዎች ሥርጭትን ወንጀል በማድረግ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለምን እንዳስፈለገው ያስረዳል፡፡

የጥላቻ ንግግር ተስፋፍቶ በጠረገው መንገድ እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ፣ እንዲሁም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በጀርመንና በመላው አውሮፓ የደረሰው የከፋ ዕልቂት ምክንያት የጥላቻ ንግግር ስለመሆኑ የሚያትተው ማብራያ ሰነዱ፣ በኢትዮጵያ በተለይም አሁን ካለው ፖለቲካዊ ነፃነት ጋር እየተበራከተ የመጣው የጥላቻ ንግግርና የአደገኛ ሐሰተኛ ንግግር ሥርጭት መፍትሔ ካልተበጀለት ለአገራዊ ሰላምና ደኅንነት፣ እንዲሁም ለለውጥ እንቅስቃሴው ዘላቂነት ትልቅ አደጋ እንደሆነ ያብራራል፡፡

ከዚሁ ከጥላቻ ንግግር ጋር በተመሳሳይ ደረጃ እክል የሆነው ሌላው ጉዳይ፣ አደገኛ የሆነና ሆን ተብሎ የሚደረግ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋትንና ከዚህ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን በመጠቀም ሐሰተኛ የሆኑና ሆን ተብሎ የተዛቡ መረጃዎችን ማሠራጨት፣ በተለያዩ አገሮች የፖለቲካ ቀውስ ከማስከተል አልፎ ለግጭትና ለጉዳት መንስዔ እየሆነ መምጣቱን ያስረዳል፡፡ ይህ ችግር ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እየተስፋፋ የመጣና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ የተለያዩ አገሮች ችግሩን ለመቅረፍ ሕጐችን በማውጣት በመከላከል ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ አገሮቹን ለአብነት ያነሳል፡፡ ሕጉን አውጥተው ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ አገሮች መካከልም ፈረንሣይ፣ ጀርመንና ኬንያን ይጠቅሳል፡፡ በዓለም ትልቋ ዴሞክራሲ በሆነችው ህንድም አደገኛ የሆነ የሐሰት መረጃ ሥርጭት ያስከተለውን ጦስ ለመከላከል የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ ሒደት መጀመሩን ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት የተነሳ የተቀሰቀሱ ግጭቶችና ጥቃቶች የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ሌላም ጉዳት እንዲደርስ መንስዔ መሆናቸውን የሚጠቁመው የማብራሪያ ሰነዱ፣ በአገሪቱ ይህንን ጉዳይ በቀጥታና በበቂ ሁኔታ ሊሸፍን የሚችል ሕግ አለመኖሩ የፈጠረው ክፍተት ችግሩ እንዲባባስና ከፍተኛ አገራዊ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በሥጋትነት ያወሳል፡፡

በመሆኑም ይህንን ክፍተት የሚሞላና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ፈጽሞ አግባብነት በሌለውና ከመብቱ መነሻና ዓላማ በተቃረነ መንገድ በመጠቀም፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ ፀድቆ በፍጥነት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት ይገልጻል፡፡

የጥላቻ ንግግርንና አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመግታት ሕግ የሚወጣው መሠረታዊ የሆኑ የዜጐችን መብቶች፣ የአገርና የሕዝብ ደኅንነትንና ሰላምን ለመጠበቅ፣ ዴሞክራሲንና ነፃነትን ከጥላቻና ከሐሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብቻ መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ ያሳሳስባል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ገደብ የሚጥል ቢሆንም፣ የሚጣለው ገደብ ተመጣጣኝና በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚደረግ እስከሆነ ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እክል እንደማይሆን፣ ይልቁንም በዴሞክራሲ ሥርዓት ተቀባይነት የሚኖረው ደጋፊ ሕግ እንደሚሆን ያትታል፡፡

 በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዕውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ አንቀጽ 29 ላይ የተደነገገው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቢሆንም፣ ይህ መብት በሕገ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን ለመተርጐም እንደ አጋዥ ተደርገው በሚቆጠሩና የአገሪቱ የሕግ ሥርዓት አካል በሆኑት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም ጭምር ገደብ የሚጣልበት እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለችው የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 19(3) ላይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከኃላፊነት ጋር እንደሚመጣና አስፈላጊ የሆኑ ገደቦች በተለይም የሌሎችን መብት፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ሰላም ለመጠበቅ ሲባል በሕግ ሊገደቡ እንደሚችሉ በግልጽ መደንገጉን ያመለክታል፡፡

ከዚህም ባለፈ የስምምነቱ አንቀጽ 20 ላይ የስምምነቱ ፈራሚ አገሮች በብሔር፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ በመመሥረት ጥላቻን፣ ጥቃትና መድልኦን የሚያራግቡ ንግግሮችን በሕግ እንዲከለክሉ ግዴታ እንደሚጥልባቸው ማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም የአዋጁ መውጣት ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ለማስቻል፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖር፣ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ለማድረግ እንደሆነ በረቂቁ አዋጁ በዓላማነት ተደንግጓል፡፡

ይህንን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያስችሉና አሁን እየተፈጸሙ ካሉ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት የሚያስከትሉትን አደጋዎች በሚፈለገው ደረጃ መፍታት የሚያስችሉ ነባር ሕጎች ባለመኖራቸው፣ አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ እንዳደረገውም ይገልጻል፡፡

ዓላማውን ከሚያስቀምጠው ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ በመቀጠል ለአዋጁ አጠቃቀም የሚያስፈልጉ ቃላትና ሐረጎች ትርጉም የተሰጣቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካካል ዋነኞቹ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የተሰጠው ትርጉም ይገኝበታል፡፡

 በዚህም መሠረት የጥላቻ ንግግር ማለት “ሆን ብሎ የሌላን ሰው፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማኅበረሰብን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን፣ ስደተኝነትን ወይም ቋንቋን መሠረት በማድረግ እኩይ አድርጎ የሚስል፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልኦ እንዲፈጸም፣ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክቶች” እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በመሆኑም የጥላቻ ንግግርን በአደባባይ ወይም ለሕዝብ በሚደረግ ንግግር፣ በኪነጥበብ ሥራ፣ በጽሑፍ፣ በምሥል፣ በድምፅ ቅጂ ወይም በቪድዮ፣ በብሮድካስት፣ በየጊዜው በሚወጣ የኅትመት ውጤት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ፣ ወይም በሌሎች ማናቸውም የመገናኛ መንገዶች ለሕዝብ መልዕክቱ እንዲደርስ ማድረግ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ይደነግጋል፡፡

አደገኛ የሐሰት መረጃ ማለት ደግሞ “የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይ ማወቅ ሲገባው ሁከት ወይም ግጭት የማነሳሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ግልጽ በሆነ መንገድ ከፍ ያለ መረጃን በማናቸውም መንገድ ማሠራጨት፤” እንደሆነ በረቂቁ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

ይሁን እንጂ አንድ መረጃ ሐሰተኛ በመሆኑ ብቻ በወንጀል የሚያስጠይቅ አለመሆኑን፣ ይልቁንም መረጃው አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ሆኖ ግጭት፣ ሁከትና ጥቃት የማነሳሳት ዕድሉ ግልጽና ከፍ ያለ ከሆነ ብቻ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጥላቻ ንግግርም ሆነ አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በተመለከተ፣ በልዩ ምክንያት ክልከላ የማይደረግባቸውን ሁኔታዎችም ይደነግጋል፡፡

በዚህም መሠረት አንድን ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ ማሠራጨት የማይከለከለው ድርጊቱ ለትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ ሲሆን፣ እንዲሁም ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፣ የማስታወቂያ ወይም የማስጠንቀቂያ አካል ከሆነ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደማያስከትል ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም በቅን ልቦና የሚደረግ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወይም አተረጓጎም የጥላቻ ንግግር ተደርጎ እንደማይቆጠር ያስቀምጣል፡፡

በተመሳሳይ ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨትን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ እንደ ወንጀል ድርጊት የማይቆጠረው፣ “መረጃው የጥሬ ሀቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣ ንግግሩ ቀልድ፣ ስላቅ ወይም ልብወለድ መሆኑ ግልጽ ከሆነ፣ እንዲሁም ንግግሩን ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በእሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው፤” ሲል ይደነግጋል፡፡

የወንጀል ተጠያቂነት፣ የተቋማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ኃላፊነትን በሚያስቀምጠው የረቂቅ አዋጁ ክፍል የጥላቻ ንግግርና አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨት ወንጀሎች ቅጣቶችን ይደነግጋል፡፡

የጥላቻ ንግግርን የተመለከቱ ወንጀሎችን መፈጸም እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከመቶ ሺሕ ብር ያልበለጠ መቀጮ እደሚያስቀጣ፣ በጥላቻ ንግግሩ የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ቅጣቱ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚሆን ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨትን በተመለከተ የተደነገገውን ድርጊት የተላለፈ፣ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ50 ሺሕ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺሕ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የኅትመት ውጤት ከሆነ ሦስት ዓመት በሚደርስ በቀላል እስራት፣ ወይም ከ100,000 ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

በሐሰተኛ መረጃው ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ፣ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፍርድ ቤት በዚህ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂ የሆነ ሰውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምንና የተከለከለው ተግባር በመፈጸሙ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ፣ ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ተመሳሳይነት ያለውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 486 ድንጋጌዎች ሙሉ በሙሉ የሚሻሩ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

የተሻረ መሆኑን፣ እንዲሁም በአንቀጽ 10 ላይ አዋጁ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 486 መሻር አስፈላጊ ከሚደርጉ ምክንያቶች አንዱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሐሰት ወሬና ሐሜቶች የሚጠብቅ በመሆኑ፣ ይህንን ዓይነት ጥበቃ ለባለሥልጣናት ማድረግ በዴሞክራሲያዊ ዓውድ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

“በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለሥልጣናትና መንግሥት ከተራ ዜጎች በተለየ ሁኔታ ከሐሰት ወሬና ከጥርጣሬ ወይም ከሐሜት ጥበቃ አይደረግላቸውም። ባለሥልጣናትና መንግሥት ከተራ ዜጋ በተሻለ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎችን የመጠቀምና የተወራባቸውን የማስተባበል ዕድልና አቅም አላቸው ተብሎ ይገመታል። በተጨማሪም የመንግሥት ኃላፊነትን የያዘ ሰው ከኃላፊነቱ ጋር ምክንያታዊ የሆኑም ሆነ ያልሆኑ፣ በሀቅ ላይ የተመሠረቱም ሆነ ከሀቅ የራቁ ትችቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ እያወቀ ኃላፊነቱን የሚረከብ እንደሆነ ስለሚቆጠር ነው፤” ሲል ምክንያቱን አባሪ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

በመሆኑም የተጋነኑና በእውነታ ላይ ያልተመሠረቱ ትችቶችን ማድረግ ወንጀል ሆኖ እንዲያስቀጣ ቢደረግ፣ የፖለቲካ ትችትና ክርክር ላይ እጅግ የከፋ ጥላ ስለሚያሳድር በዴሞክራሲያዊ ዓውድና ሥርዓት እንዲህ ዓይነት ንግግሮች ወንጀል ሊደረጉ እንደማይገባ፣ በተጨማሪም የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 486 በበቂ ሁኔታ ዝርዝር ሆኖ የአደገኛ ሐሰት መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚያስችል ስላልሆነ፣ በዚህ አዋጅ መተካቱ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ፋይዳና ሥጋቶች

በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃን ማሠራጨት የወንጀል ድርጊት አድርጎ መደንገግ ፋይዳና ሥጋታችን በተመለከተ ክርክሮች አሉ፡፡ በአንድ ወገን የመናገርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ እንዲሁም የሚዲያ ነፃነትን ይጎዳል የሚል ክርክር ሲነሳ፣ አገሪቱ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ይህንን አዋጅ የግድ እንደሚጠይቅ የሚገልጹ ደግሞ በሌላ በኩል ተቃራኒ ክርክር ያነሳሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሚዲያ ሕግ ተመራማሪና ባለሙያ የመናገርም ሆነ የሚዲያ ነፃነት ገደብ ባይጣልበት የሚመረጥ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ብዝኃነት ባለበት አገር፣ ብዝኃነትን አቻችሎና ተቀብሎ እሴቶቹን ለማስቀጠል የሚያስችል የዴሞክራሲ ሥርዓትም ሆነ ባህል በሌለበት ገደብ አለመጣሉ፣ የማኅረሰቦችን አብሮ የመኖር ዕድል ሸርሽሮ አገርን የመነቅነቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያስረዳሉ፡፡

የሕጉ አስፈላጊነት የጥላቻ ንግግርን ወይም ጉዳት ያለው ሐሰተኛ መረጃን መሸከም የሚችል ማኅበረሰብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አለ ወይ በሚል መመዘኛ ተመዝኖ ቢታይ፣ ውጤቱ በየዕለቱ በየአካባቢውና የልሂቃን መፍለቂያ በሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጭምር የሚታየው የሕይወት መጠፋፋት ከበቂ በላይ መልስ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡

አሁን ባለው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥሪት ብሔረሰቦች ወይም ማኅበረሰቦች ልሂቃን ያሉባቸውን የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ጥቄዎች ለመፍታት ወደ ውስጥ ከመመልከት ይልቅ የቀደሙ ታሪካዊ በደሎችን፣ አፈናና ጭቆናዎችን በመጥቀስ ለሚገኙበት ሁኔታ ሌላ ማኅበረሰብን ተጠያቂ በሚያደርጉ የጥላቻ ወቀሳዎችን መሰንዘር ቀላል ተግባር ሆኖላቸዋል ይላሉ፡፡

ይህ አባዜ ማኅበረሰቦች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ውስጣቸውን ከመመልከት እንዲቦዝኑ ከማድረጉም በላይ፣ የሕዝቦችን አብሮነትና የአገርን ህልውና ወደ መፈተን እየተሸጋገር በመሆኑ አዋጁን በማውጣት መከላከል ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን አዋጅ ተግባራዊ የማድረግ ሒደት የመብት ጥሰቶችን ይዞ እንዳይመጣ ሥጋት ያላቸው መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት አለመፈጠርና በአምባገነን መንግሥት መዋቅር ውስጥ ተፈጥረው ያለፉት የሕግ አስከባሪ ተቋማት፣ እንዲሁም አቃቢያነ ሕጎች አሁንም ከባህሪያቸው ተላቀዋል ማለት የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡

ሕግ ተርጓሚ የሆኑት ፍርድ ቤቶችም አዋጁን የመተርጎም አቅማቸውን በነፃነት፣ እንዲሁም ያለ አድልኦ የሚወጡበት ደረጃ ላይ አለመድረሳቸው እንደሚያሳስባቸው ያስረዳሉ፡፡

አዋጁ በተመለከተ በተሞክሮነት የተገለጹት እንደ ጀርመንና ፈረንሣይ ያሉ አገሮች የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ ያፀደቋቸው ሕጎች የሚጥሉት ክልከላ በዜጎቻቸው ላይ ሳይሆን፣ ንግግሮቹ በአብዛኛው በሚተላለፉባቸው እንደ ትዊተርና ፌስቡክ በተሰኙት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲሆን፣ የትስስር ገጾቹን የፈጠሩ ኩባንያዎች የጥላቻ ንግግሮችን በ24 ሰዓት ውስጥ ካላነሱ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት የሚጣልባቸው እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ለማድርግ የምትችልበት ነበራዊ ሁኔታ ባለመፈጠሩ አፈጻጸሙን በተመለከተ ልምድ መውሰድ የሚገባት እንደ ኬንያ ካሉት አገሮች ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን የሚከለክለውን አዋጅ ማፅደቁን ተከትሎ፣ ሕጉን በተመለከተ አስተያየታቸውን በትዊተር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ካሰፈሩት መካከል፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች  ኮሚሽነር ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡

“ሕጉ መፅደቁ በኢትዮጵያ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መጥፎ አይደለም፡፡ ለጥላቻ ንግግሮቹ ምንጭ የሆነውን ፖለቲካ መፍትሔ መፈለግ አብሮ መታየት ያለበት ሲሆን፣ የሕጉ ስኬት የሚለካውም በጠባቡ ሲተረጎምና አግባብነት ላላቸው ጉዳዮች ብቻ ተግባር ላይ እንዲውል ሲደረግ ነው፤” ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -