Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኢትዮጵያውያን ቁንጮ የሆኑበት አህጉራዊው የፈጠራ ሳምንት

ኢትዮጵያውያን ቁንጮ የሆኑበት አህጉራዊው የፈጠራ ሳምንት

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

መሰንበቻውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተመረጡ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት (አፍሪካን ኢኖቬሽን ዊክ) በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በዚህም የፈጠራ ሳምንት ለመጨረሻ ውድድር ካለፉት 55 ተወዳዳሪዎች አምስት ምርጥ የፈጠራ ባለሙያዎች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ዶላርና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከምርጦቹ ውስጥ ሦስት ኢትዮጵያውያን አንድ ሩዋንዳዊ፣ አንድ የቶጎ ዜግነት ያላቸው የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎች ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከተሸላሚዎቹ መካከል አቶ መክብብ ታደሰና ጓደኞቹ ይገኙበታል፡፡ እነርሱን ያሸለማቸው የፈጠራ ሥራ የሥነ ልቦና ችግርን ሊፈታ የሚችል መተግበሪያ ይዘው መምጣታቸው ነው፡፡

እንደ አቶ መክብብ አገላለጽ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሥነ ልቦና ችግር ያለበት ግለሰብ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ የሥነ ልቦና ሐኪምን ማናገር እምብዛም ባለመለመዱ ችግሩን ለመፍታት ከጓደኞቻቸው ጋር ቻት ዶት ኢቲ (Chat.Et) የሥነ ልቦናን ችግርን ሊፈታ የሚችል መተግበሪያ ዕውን አድርገዋል፡፡

ቻት ዶት ኢቲ መተግበሪያ በኦንላይንና በኦፍላይን አማራጭ ሲኖሩት የግለሰቡ ስም፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ የሚኖርበት አካባቢና ማንነት ሳይታወቅ የፈለገውን ጥያቄ መጠየቅ የሚችልበት ነው፡፡

ግለሰቡ የጠየቀውን ጥያቄ ኦንላይን ላይ ያለ ባለሙያ እንዲመለስ የሚያስችል ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ባለሙያ ኦንላይን ላይ ከሌለ አማራጩ መንገድ በኢሜይል አድራሻቸው ለጥያቄው መልስ ያገኙበታል፡፡

በቴክኖሎጂ የበለፀጉ አገሮች ላይ መተግበሪያ እየሠራ ቢሆንም ለኢትዮጵያውያን በሚያመች መልኩ አሻሽለው በአማርኛ ቋንቋ ለተጠቃሚ ማቅረባቸውንና በቀላሉ ግለሰቦች ሐሳባቸውን ያንፀባርቁበታል፡፡ መተግበሪያው ሥራ ላይ ከዋለ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን፣ በአሁን ጊዜ ከ1,000 በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ተገልጿል፡፡

አንዳንድ የሥራ ፈጠራዎች ትርፍ ላይ ነው የሚያመዝኑት ያለው አቶ መክብብ፣ ከመተግበሪያው ምንም ዓይነት ገቢ እንደማያገኙ አስረድቷል፡፡ እንደ ምክንያት ያነሳው ይህ መተግበሪያ ማኅበራዊ ችግርን የሚፈታ እንደሆነ ብቻ አስበው መሥራታቸውንና መተግበሪያው ብዙ ተጠቃሚ ሲያፈራ በጎን በሚደረገው የማስተዋወቂያ ቦታ የሚገኘው ገቢ ምናልባት ከእሱ ሊያገኙ የሚችሉት ጥቅም ሊኖር እንደሚችል ተናግሯል፡፡

በዚህ ቴክኖሎጂ አሥር የሥነ ልቦና ሐኪሞች ሲኖሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊጨምር እንደሚችል፣ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚወስደው የገንዘብ መጠን ልክም ሌሎች መተግበሪያ ሲጠቀሙ የሚወስደውን ያህል መሆኑን አስረድቷል፡፡

ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መተግበሪያው ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲውል መታሰቡንም ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያሉት ተማሪዎችም ከሌሎች ማኅበረሰቦች የኢንተርኔት አገልግሎት በቀላሉ ስለሚያገኙና በተለያዩ ምክንያቶች የሥነ ልቦና ችግር ይኖራል ተብሎ ስለሚጠበቅ በቀላሉ ተቀባይነት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ሌላው በዚህ የፈጠራ ሳምንት የፈጠራ ሥራውን ይዞ ብቅ ያለው አቶ አንተነህ ታዬ (ኢንጂነር) ነው፡፡ በዓይነ ሥውራን በትርና መነጽር ላይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮበት ምርጥ አምስት ውስጥ ገብቷል፡፡ ለማሸነፍ ያበቃው በትሩና መነጽሩ ተናጋሪ በመሆኑና ከተለያዩ ችግሮች ይታደጋል ተብሎ በመታመኑ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በዚህ አዲስ ፈጠራ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲኖር፣ እንቅፋትና እርጥብ መሬት ሲከሰት በቀላሉ መረዳት እንዲቻል፣ እንዲሁም የተቀረውን ነገር ከመነፅሩ ጋር በተያያዘው ኤርፎን ያለውን ችግር እንዲያዳምጡ ተደርጎ ተሠርቷል፡፡  የተገጠመው ኤርፎን ከአደጋው ጥበቃ ባሻገር ሙዚቃም ሆነ የራዲዮ ፕሮግራምን ለማዳመጥ ይችሉበታል፡፡ ተናካሽ ውሻ ጨምሮ ድመትና አይጥ በትሩ በሚያወጣው ድምፅ ምክንያት ይሸሻሉ፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ቋንቋዎች መተግበሪያ ስላለው ግለሰቡ በፈለገው ቋንቋ መጠቀምም ያስችለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ዱላው እንደ ፓወር ባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ከተሞላ ለአሥር ተከታታይ ቀናት እንደሚያገለግል፣ ቴክኖሎጂው ማታ ማታ ማየት ለማይችሉም ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ አመቺ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዚህ ዓይነት (Version) የዓይነ ሥውራን በትርና መነፅር 80 በመቶ ያህሉ እያለቀ መሆኑና ከመጀመሪያው የፈጠራ ሥራ ሻል ያለ መሆኑን ኢንጂነሩ አብራርቷል፡፡

ሁለተኛው ማሻሻያ የተደረገበት የዓይነ ሥውራን ቴክኖሎጂ ይበልጥኑ እነሱን የሚደግፍና ለተለያዩ ችግሮች በራሳቸው እንዲወጡ እንደሚረዳ አውስቷል፡፡ ይህን ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ለማምረት ደረጃው ስለማይፈቅድ በቻይና በማምረት ለገበያ ለማዋል ዝግጅቱን መጨረሱንም አስረድቷል፡፡

አቶ አንተነህ ከዚህ ፈጠራ በተጨማሪ በቀላሉ በስልክ ቤት ውስጥ ወይም የፈለጉበት ቦታ ሆነው በመክፈት ክፍያ የሚያደርጉበት ቴክኖሎጂ መሥራቱንና ሥራውም ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ከመመዝገብ ባለፈ ዕውን አልሆነም ብሏል፡፡

ተወዳዳሪዎቹ በአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት ከመሳተፋቸው በፊት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሳምንት ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ ሽልማት ወይም ውድድር ሲኖር ብቻ ሳይሆን የተሻለ አገር ለመፍጠር ሥልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አምስቱ ምርጥ የአፍሪካ የፈጠራ ባለሙያ ሆነው ያሸነፉት ኢትዮጵያውያኑ አንተነህ ታዬ፣ ዳዊት ጌታቸው፣ መክብበ ታደሰ፣ እንዲሁም ሞሴስ ካታላ ከሩዋንዳ እና ኮፊ ታክፓህ ከቶጎ ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ዶላር ተሸልመዋል፡፡   

በተካሄደው የፈጠራ ውድድር ከተሳተፉት 200 የፈጠራ ባለሙያዎች ውስጥ 150ዎቹ ኢትዮጵያውያን፣ 50ዎቹ ደግሞ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ናቸው፡፡ ለመጨረሻው ማጣሪያ የደረሱት 50 ተወዳዳሪዎች  እያንዳንዳቸው አንድ ሺሕ ዶላር መሸለማቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...