Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመቋጫ ያጣው የቀድሞ ጦር ጥያቄ

መቋጫ ያጣው የቀድሞ ጦር ጥያቄ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ28 ዓመት በፊት በተካሄደው የመንግሥት ለውጥ ሳቢያ ከመከላከያ ሠራዊት የተሰናበቱት የቀድሞ ምድር ጦር ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች እስካሁን ድረስ የታገዱባቸው ልዩ ልዩ ዓይነት መብቶቻቸውና ንብረቶቻቸው  እንዲመለሱላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች ማኅበር ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ስብሰባ፣ የማኅበሩ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን ክፍሌ እንደገለጹት፣ የታገዱባቸው መብቶች የጡረታና የሕክምና ሲሆን፣ ንብረቶቻቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገኘው ብር 7,000,000 የዕድራቸው ገንዘብና ከየግል ሀብታቸው አዋጥተው ያቋቋሙት የጦር ሠራዊት መኮንኖች ክበብ ናቸው፡፡

አባላቱና ሲቪል ሠራተኞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ ያነሳሳቸው፣ ከ1984 ዓ.ም. ኅዳር ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከታቸው 11 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አመልክተው ሰሚ በማጣታቸው የተነሳ መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህም ሌላ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጥያቄያቸውን በወቅቱ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ለነበሩት ዓይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) እንዳቀረቡ፣ ሚኒስትሯም በጉዳዩ ዙሪያ ከማኅበሩ አመራሮች ጋር እንደተወያዩ፣ በውይይቱም ወቅት በተለይ የጡረታና የሕክምና መብቶቻቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲፈጽሙ ንብረቶቻቸውን በተመለከተ ከአመራሮች ጋር በቅርቡ እየተገናኙ መፍትሔ በሚያስይዙ እንቅስቃሴዎች ላይ አብረው ለመሥራት የሚያስችል መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ለዚህም የሚያስፈልገንን ሰነዶች ተጠይቀን በእጃችን የነበሩትን ፎቶ ኮፒ አድርገን ሰጥተናል፡፡ የጎደለውንም መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥር ቀም/መሠ/ሲ.ሠ/መእ/02/101/አ 28 ገጽ ልከንላቸዋል፡፡ መግባባት የተደረሰበትም ጉዳይ ከምን ደረሰ? ብለን የጽሕፈት ቤቱን ኃላፊ እየደወልን ስንጠይቅ በፕሮጀክት ደረጃ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ሲገልፁልን ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም የባለሥልጣናትን ለውጥ ሰምተን  ተሰናባቿ ሚኒስትር ጉዳያችንን ለተረካቢያቸው ሚኒስትር አቅርበው እንዲያስረዱልን ቀርበን ለማነጋገር እንዲፈቀድልን በተደጋጋሚ ኃላፊውን ጠይቀናቸው ሳያስተናግዱን ቀርተዋል፤›› ብለዋል ብርጋዴር ጄኔራል ጥላሁን፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትር ለማ መገርሳ አዲሱ ሥራቸውን ከጀመሩ በኋላ ቀርበው ለማነጋገር እንዲፈቀድላቸው የጽሕፈት ቤቱን ኃላፊና የሕግ አማካሪያቸውን በየጊዜው ቢጠይቁም ‹‹አይገኙም፣ አይገቡም›› በማለት ሊያቀርቧቸው ፈቃደኛ እንዳልሆኑ፤ ይህም ሆኖ ግን እስከ ሐምሌ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ጠብቀው ምንም ዓይነት መልስ እንዳላገኙ፣ በዚህም የተነሳ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁጥር ቀምጠሠአ.ሲሠማ/02/104/አ33 በተጻፈ ደብዳቤ ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ፣ ይህንንም ለአገር መከላከያ ሚኒስቴርና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግልባጭ እንዳሳወቁ አክለዋል፡፡

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ኮሎኔል ጋረደው ለውጤ፣ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን የተቆናጠጠው መንግሥት በአገር ሀብት የሠለጠነውን የቀድሞ ጦር ሠራዊት እንደ ጥፋተኛ በመቁጠር ሙሉ ለሙሉ መበተኑ፣ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ አገርን ከመበደል ባሻገር የግልና የጋራ መብቶችንም እንደጣሰ፣ በአዛውንት ዕድሜያቸው ያለጡረታና ያለሕክምና ከእነ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንደዳረጓቸው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀማጭ የሆነውን የሠራዊቱን ዕድር ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ያገደ ሲሆን፣ አባላቱ በግል ገንዘባቸው ያቋቋሙትንም የመኮንኖች ክበብ ከእነ ውስጥ ንብረት ጭምር መነጠቁንም ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ሕፃናት አምባና አዲስ አበባ የሚገኘውን ወታደራዊ እጓለማውታን ታዳጊ ሕፃናት፣ ለአገር ዳር ድንበር መከበር ከጠላት ጋር ጉሮሮ ሲተናነቁ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በጀግኖች አምባ ይደገፉ የነበሩትን ጀግኖች አውጥቶ መበተኑ ታሪክ የማይዘነጋው ስህተት መሆኑንም አክለዋል፡፡

እንደ ኮሎኔል ጋረደው ማብራሪያ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የቀድሞ ታጋዮች የጡረታ መዋጮ ባይኖራቸውም፣ ከመንግሥት ካዝና ወጥቶ ጡረታቸውን እንዲያገኙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በአንፃሩ ግን ሕግ፣ ደንብና ሥርዓትን በተከተለ መንገድና ከደመወዛቸው መዋጮውን ሲያስቀምጡ የቆዩት የቀድሞ የምድር ጦር አባላትና ሲቪል ሠራተኞች ጡረታቸውን ተነፍገዋል፡፡ ይህም ኢፍትሐዊ አካሄድ ነው፡፡

‹‹አቤቱታችን በእያንዳንዱ አመራር ክፉ ሐሳብ፣ ጭቆናና የንቀት መንፈስ ሰሚ በማጣቱ ያለ ውጤት እስካሁን ድረስ ቢቆይም በዳዮቻችን የነገ ዕዳቸውን እንዳስቀመጡ አስበን በሥነ ምግባር የታነፀና ከፍተኛ የአንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት በውስጣችን የጎለበተ በመሆኑ፣ ዛሬም ቢሆን እየተበደልን ባለን አቅም ሁሉ ለአገራችን አንድነት፣ ለሕዝብ ሰላምና ነፃነት ሲባል የአጋርነት ቃሉን ያደሰ መንፈሰ ጠንካራ ሠራዊት ነን፤›› ብለዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ፍሥሐ ዘውዴን የቀድሞ ምድር ጦር ሠራዊት አባልና ሲቪል ሠራተኞች ለመከላከያ ሚኒስቴር ያቀረቡት ጥያቄ ከምን ደረሰ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የአቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳይ እየታየና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ጋር እየተነጋገርንበት ስለሆነ እንደተጠናቀቀ የተደረሰበትን ድምዳሜ እናሳውቃቸዋለን፤ እስከዛው በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...