Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መፍጠን እያለ ማዝገምን ምን አመጣው?

ሰላም!  ሰላም! ከዘመኑ ሰው አንዳንዱ ፍቅርን ንቆ፣ መተሳሰብን ትቶ፣ ሰውነትን አውርዶ አውሬነትን አግዝፎ አብዶ አሳበደን እኮ። ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነን መከራ በምናይባት አገር፣ ለፍቅር አንድ ቀን አለመመደቡ ያበሳጫቸው አጋጥመውኛል። አሁን ደግሞ ፀብ ቆስቁሶ የእኔ ቢጤውን ምስኪን እርስ በርሱ ለማባላት የሚደረገው ሽርጉድ ለጉድ ነው። የዘመናችንን ነገር ካነሳሁ አይቀር አንዱ ሾካካ፣ ‹‹አንበርብር ከአንዲት መጠጥ ያለች ሴት ጋር ቆሞ ስልክ ቁጥር ሲለዋወጥ አየሁት፤›› ብሎ ለማንጥግቦሽ መናገር። በለጠፈና ባለጠፈ መሀል ድርያ እኩል እንደማይሠራ እየታወቀ፣ የወሬው ቆርጦ ቀጥልነት ምን ያህል እንደናረ ልንገራችሁ ብዬ እኮ ነው። የትዳር ሰሌዳ አውጥታችሁ ስትከራርሙ ፍቅርና ነገር መሳ ለመሳ ይረማመዱባችኋል ለማለት ነው። ከዚያስ? ከዚያማ ማንጠግቦሽ አኮረፈች። ይታያችሁ እንግዲህ። እኔ ደላላ ነኝ። ስልክ ስሰጥና ስቀበል ነው የምውለው። ወሬ አነፍናፊ ግን የሚታየው ሌላ ነው። የአገሬ ጉዳይም እንዲህ እየሆነ እኮ ነው ለንፁኃን መከራው የተረፈው። እንደሠራ አይገድል አለ የአገራችን ሰው!

መቼ ዕለት ከባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራ በሰደድ ወሬ የደረሰብኝን ብነግረው፣ ‹‹ዓለም እኮ ዝም ብሎ ነው አልበርት አንስታይንን የተጋነነ ስም የሰጠው፤›› አለኝ። ‹‹እንዴት?›› እለዋለሁ፣ ‹‹ወሬን የመሰለ ኃይድሮጂን ቦምብ ፈልሳፊዎች እያሉ ምን ወደ ሌላ የኢነርጂ ቀመር ፈልሳፊ ያስኬደናል?›› አለኝ። የደረሰብኝ አንገብግቦኛልና ‘ኧረ ልክ ነህ ብዬ’ በልቤ አጨበጨብኩለት። በልቡ የሚያማን ሳትናገሩ በልብ እንዴት ይጨበጨባል የምትሉት እናንተስ ብትሆኑ ምን ለማለት ነው? ጉዳዩ እኮ ‘ሲሪየስ’ ነው።  የታላቁ የፍቅር ፀር ነገር መነሻው ሐሰተኛ ወሬ እንደሆነ አጣችሁትና ነው? የነገር አምራቹ ደግሞ የወሬ ሊቅ ነው። ይኼው ታዲያ በወሬ ሱስ ምክንያት የስንቱ ቤት ሲፈርስ ዝም እየተባለ፣ የአገር ሰላም እየደፈረሰና ምንዱባን የጥቃት ሰለባ እየሆኑ እስከ መቼ ይሆን ወሬና ወሬኛ ተከብረው የሚኖሩት? አንዳንዴ እኮ አካፋን አካፋ አለማለት የወሬኛ መጫወቻ ያደርጋል፡፡ በተለይ ከድድ ማስጫ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ቦታዎች ያሉ ወሬኞችን ልክ ማስገባት ካልተቻለ ቤተሰብ ቀርቶ አገር ይፈርሳል፡፡ ለምድረ ወሬኛማ መድኃኒት ያስፈልገናል፡፡ ልክ እንደ ምች ማለት ነው!

የፍቅርን ነገር ካነሳሁ ታዲያ ያኔ በደጉ ጊዜ ይኼውላችሁ እኔና ማንጠግቦሽ ‹ስንጣበስ›፣ ‹‹ደብዳቤ ቢጽፉት እንደ ቃል አይሆንም፣ እንገናኝና ልንገርህ ሁሉንም፤›› ብላ ትልክብኝ ነበር። መቼም ፍቅረኛሞች ከተዋደዱ እኮ ሙሴ ቀይ ባህርን ከከፈለው በላይ ፓስፊክን ካላደረቅን ባዮች ናቸው። የደረሰበት ያውቀዋል። ሳይፈለግም ታዲያ የዚያኑ ያህል ነው። ‹‹ምነው ባደረገኝ የደጅሽን አፈር፣ አንቺ ስትረግጭኝ እኔ እንድንፈራፈር፤›› ያለው ሙሉቀን መለሰ ያለ ምክንያት አይመስለኝም። አሁን የእኔንና የማንጠግቦሽን ታሪክ ያነሳሁት ሰሞኑን ከምሰማው አጓጉል ነገር በተለይ ከትንኮሳና ከወንጀል ጋር ቅር ያለኝ ነገር ስለበዛ ነው። ማን አለኝ? ያው እናንተው ናችሁ ቅሬታዬን የምትሰሙ። የአገሪቱ ቅሬታ ሰሚ ቢሮዎች እንደሆኑ ባልሰሟቸው ቅሬታዎች ላይ ቅሬታ ሊያሰሙ፣ ሌላ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ለማቋቋም ስብሰባ እየያዙ አስቸግረዋል። ለነገሩ ቅሬታ ሰሚ በመጥፋቱ አይደለም እንዴ ሕግ ማስከበር ያቃተው? ተው አታስለፍልፉኝ!

‹‹እኔስ ይኼ የፖለቲከኞች ጭቅጭቅ የሚባል ነገር እስኪያልቅ ላልተወሰነ ጊዜ ለምን ‘ቫኬሽን’ ውጡ እንደማይሉን አይገባኝም?›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። የዘንድሮ ልጅ ታውቁት የለ ገና ሳያድግ እያረጀ ቶሎ ቶሎ ይደክመዋል። እኔማ አንዳንዴ ያረጁ መዝናኛዎቻችን እንደ አዲስ አበባ መንገዶችና ቤቶች መልሶ ማልማትና ማስፋፋት ዕቅድ ውስጥ ካልገቡ፣ ለ‘ቫኬሽን’ የሚዝተውን ሁሉ ለማስተናገድ የሚችሉ እየመሰለኝ አይደለም። ቀላል የሚዝተው በዝቷል እንዴ? እ . . .  ምን እያልኩ ነበር? ጉድ ፈላ እንደ አረጁ የአፍሪካ መሪዎች እያወራሁ እንቅልፍ ይዞኝ ይሄድ ጀመር? ‹‹የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽ›› አለ የአገራችን ሰው። ኧረ ይኼን የአገራችንን ሰው ምን አባቴ ላድርገው ዛሬ። እውነት የጉድ ቀንና የጉድ ዘመን እኮ ሲንዘላዘል ጥሩ ማሳያ እንደ እኛ የሚሆን የለም፡፡ ‹ምን ያለ ዘመን ነው ዘመነ ድሪቶ፣ አባቱን ያዘዋል ልጁ ተጎልቶ› ያለው ዘፋኝ ምን ታይቶ ይሆን? ጉድ እኮ ነው!

ስለፈቃድ ነበር የማወራው አይደል? የንግድ ፈቃድ አላልኩም። በፍቅር መፈቃቀድ፣ መፈላለግና መዋደድ ነው ያልኩት። ምንም እንኳን ዛሬ በፍቅር ስም ነጋዴው ቢበዛም። ዘመኑ የአጭበርባሪዎች ነው ብለን እንለፈው ተውት። እና ይገርማችኋል የእኔና የማንጠግቦሽ ፍቅር ልዩ ነበር። እንዳሁኑ የቅፅበታዊ ስሜት ጉጉት እየገባ አይበጠብጠው፣ የብሔር ወይም የእምነት ጣጣ ንፋስ ሆኖ አይገባብን፣ የታክሲ ችግር ከቀጠሮ አያስረፍደኝ አያስረፍዳት፣ ሁሉንም ችግር ጥለን ፍቅራችንን በአቅማችን እናጣጥም ነበር፡፡ ዛሬ ግን የምሰማው ነገር ያስደንቀኛል። ስንት መግባቢያ ቴክኒክና ታክቲክ ባለበት ዘመን፣ ቢቆራረጥና ቢዘገይም ኢንተርኔት እያለ፣ ስንት ወሬ ማስጀመሪያ ተናግሮ ማናገሪያ ርዕስ እያለ ለምሳሌ አንዳንዱ፣ ‹‹የቁጠባ ቤቶች ዕጣ እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚወጣልን ይመስልሃል/ሻል?›› ቢባል የሆዳቸውን አውግተው ቡና ካልጠጣን የሚባባሉ ፍቅረኞች በማይጠፉበት ዘመን፣ መጥለፍና ማስገደድን እንስሳት እንኳ ትተዋል። ከዚህም አልፎ አገርን ጠልፎ ለመጣል የሚደረገው የክፋት ሩጫም እንዲህ ማለት ነው! 

የምሬን ነው! የእኛን ዓይነት ክፉ ድርጊትን እንስሳት እንኳ ትተዋል! ካላመናችሁ እንግሊዝ ውስጥ አንድ ውሻ ዓይኑን የጣለባትን ቆንጂት ውሻ ለማግኘት የተጠቀመውን አማላይ ቴክኒክ ‘ሰርች’ አድርጉ። ምነው እናንተ የፖለቲካ ሸረኞችን ዜና ስትሸሹ ስንት ነገር እኮ እያመለጣችሁ ነው! ‹‹መቼም ሠልጥኖ የማይሠለጥን የሽብርተኛ ዜና ከመቁጠር፣ በደመ ነፍስ የሚመሩት እንስሳት የሚሠሩትን አስደማሚ ነገር ብሎ ማጨብጨብ ዕፎይ ማስባል ብቻ ሳይሆን ሳያፀድቅም አይቀር፤›› ይሉኛል ከባሻዬ ጋር ስናወራ። ‹‹ሰው ግን ሰው ነውና፣ ቢነግሩት ቢመክሩት እሺ ማለት ከቶ አይቻለውምና፣ አሁንም አለ ከሞት ከሽረቱ ጋራ!›› ያለው ማን ነበር እናንተ! ዳሩ ማንም ቢለው የሚፈለገው መባሉ ነው! በተለይ የዘመኑ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ለዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አልተፈጠሩም እያልኳችሁ? ይኼ እኮ ያፈጠጠ ሀቅ ነው!

ዛሬ እንዲህ ስለሥራ ውጣ ውረድ በየመሀሉ ጣልቃ ሳላስገባ የባጥ የቆጡን የምቀደው ለካ ምን ሆኜ እንደሰነበትኩ አልነገርኳችሁም? የእኔ ነገር! የሚያዝል፣ የሚያዞርና ከአልጋ ከወረዱ የሚጥል ወረርሽኝ ጉንፋን አሞኝ የሰነበትኩት አልጋዬ ላይ ነው። ያው ስልኩ ስላለ አንዳንዴ ሲሻለኝ በስልክ የምሸቅለው እንዳለ ነው። ታዲያ ልምከራችሁ? ምንም ቢሆን በዚህ ጊዜ መያዝ የለባችሁም። እኔ በፖሊስ አላልኩም በበሽታ ነው! ኧረ እባካችሁ እያጣራችሁ ስሙ። አጉል ምርጫዎቻችንን በማጣራት የዛሉት አንሷቸው የሰለቸ ወሬያችንን አጣሩልን ብለን የአውሮፓ ኅብረትን ማስቸገር እኮ ነው የቀረን። ታዲያላችሁ አንድ ወዳጄ ደውሎ፣ ‹‹ያንን ቤት ላሳይልህ ሰዎች አግኝቻለሁ፤›› አለኝ። ባለሁለት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ነው። ‹‹ጥሩ አሳያቸውና መልሰህ ደውል፤›› ብዬው እኔ በቴሌቪዥን የዓለምን ጉድ እኮመኩማለሁ።

ለካ በሠለጠኑት አገሮችም ሰው ይቆጣል። አይ ጊዜ። እነ አሜሪካም ወግ ደረሳቸውና ይኼው መከፋፈልን እየቀመሷት ነው። እሰይ ባይባልም መቼስ አንዳንዱን ነገር ካላዩት አይረዱትምና ሰሞኑን ያለ ቅጥ የትራምፕ ደጋፊ ሆኛለሁ። በሁለት አፍ ማውራትና የቋንቋ መደበላለቅ በእነ አሜሪካ እልፍኝ ተቀጣጥሎ ሳይ የአፍሪካ አምላክ እላለሁ። ለካ የእነሱም ዴሞክራሲ የጭንቅ ቀን ለገላጋይ ይከብዳል? እነዚህ ሰዎች በመረጡት ፕሬዚዳንት እንዲህ ከሆኑ እንደኛ ሳምንት ሁለት ሳምንት ውኃ ቢሄድባቸው፣ ዘረፋ ቢደቁሳቸው፣ በየሄዱበት ቢሮ ስብሰባ ላይ ናቸው ቢባሉ፣ ሕግ የሚያስከብር ቢጠፋ አሜሪካ የምትባል አገር ከዓለም ካርታ ላይ ልትጠፋ እንደምትችል አሰብኩ። ‹‹አወይ ሥልጣኔ! እውነት የምር የሆነችው ሥልጣኔ፣ ከግጭትና ከሁከት በላይ ክንፍ አውጥቶ የበረረ ሕዝብ ያዘለችው ሥልጣኔ መገኛዋ የት ይሆን?›› ስል ማንጠግቦሽ ሰማችኝ፡፡ ‹‹አርፈህ ጉንፋንህን አታስታምም? በሰው ጉዳይ ምን ጥልቅ አደረገህ?›› ብላ ተቆጣችኝ። ስልኬ አልጠራም። ወዲያው ጭልጥ አድርጎ እንቅልፍ ወሰደኝ። ማንጠግቦሽ ‘አያገባህም’ ብላ ዝም ብታስብለኝም በህልሜ ጭራሽ ‘ቪዛ’ ሳይመታልኝ ከየት የመጣ የማይታወቅ ብጥብጥ መሀል ድንጋይ እወረውራለሁ። መቼም ድንጋይ መወርወር ሲሳይ ነው እንዳትሉኝና እንዳንጣላ! በቅጡ ሙግት የማይችል ምድረ ድንጋይ ወርዋሪ ሁሉ!

በሉ እንሰነባበት። ሰሞነኛው ወሬ በዝቶብኝ ግራ ገብቶኛል። በተለይ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በሶሪያና በመሳሰሉት የፈረሱ አገሮች ወሬ አዕምሮዬ የዛለው ሳይበቃ፣ በዘመናችን የራሳችን ሁኔታ ጉልበቴ ከድቶኛል። ‹‹ከላይ እሳት ከታች እሳት ሆኖብን ምን ልንሆን ነው?›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ባሻዬ ደግሞ በበኩላቸው፣ ‹‹እንግዲህ ዘመኑ ቀርቧል። በልዩ ልዩ ሥፍራ ሁከትና የመሬት መናወጥ ይሆናል ይላል ቃሉ። አርፋችሁ በጊዜ ንስሐ ግቡ፤›› ይሉናል። ማንጠግቦሽ በፈንታዋ፣ ‹‹እሱ ካመጣው ምን ልናደርግ ነው? እሳት እንደ ውኃ አይገደብ?›› ትለኛለች። በየአቅጣጫው አስተያየቱ ሲበዛብኝ ብቻዬን ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ እሄድና እቆዝማለሁ። እዚያም አመሻሽቶ ሰው ሞቅ ሲለው የሚያወራው ስለዚህ ነው። አንዱ እንዲህ ይላል፣ ‹‹እኔ በጣም የማዝነው ግን ይህንን የመሰለ ታላቅ ክስተት እየተከናወነ፣ እኛ ግን ልባችን ያለው የአርሴናል ቀጣይ አሠልጣኝ ማን ይሆናል የሚለው ላይ ነው፤›› ይላል። ሌላው ቀጠል አድርጎ፣ ‹‹ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እንድናስብ ፈለግክ? በሰው አገር ቡድን በማያገባን እየተጋደልን የሰው አገር መሪ ምርጫ ላይ ልባችንን በማሳረፋችን መሰለኝ ከሥልጣኔ ርቀን መኖራችን የተጋለጠው፤›› ይለዋል። የአክራሪ ብሔርተኞችና ፖለቲካ ያልገባቸው ጭፍኖች ነገር ሲገርመኝ ደግሞ፣ በዚህ በኩል የመሰሪዎች ሴራ ሲታሰበኝ ሒሳቤን ከፍዬ ውልቅ አልኩ። ወዲያ ግራ ያጋባ ፍቅር፣ ወዲህ የነገር እሳተ ጎመራ፡፡ ጎበዝ ወደ ኋላ ስለቀረን አንጎተት፡፡ ስንጎተት ነው ሌሎቹ ጥለውን የጠፉት፡፡ መፍጠን እያለ ማዝገምን ምን አመጣው አትሉኝም ታዲያ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት