Sunday, April 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር ማረጋጋት ይቅደም!

የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ሰላማዊ ሐዲዱን ስቶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሲነጉድ፣ በሴራ ትንተናዎች እየታጀበ ሁከት ቅስቀሳ ውስጥ ይሰማራል፡፡ ሁከቱ ያገኘውን እያዳረሰ ወደ ግጭት ሲቀየር፣ ሃይማኖትና ብሔር እያጣቀሰ ባገኘው አቅጣጫ ይፈሳል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ከምንም ነገር በላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ስምምነቱ የሚመነጨው ደግሞ ለልዩነት ዕውቅና በመስጠትና የጋራ አማካይ በመፈለግ ነው፡፡ ይህንን አማካይ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ካልተቻለ ግን ከመቀራረብ ይልቅ መለያየት፣ ከመነጋገር ይልቅ መተናነቅ፣ ከመተባበር ይልቅ ጠላትነትን ማጠናከር የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች እያጋጠሙ ያሉ ሁከቶችና ግጭቶች፣ ለሰላማዊ ፖለቲካ ዕድል ለመስጠት ካለመፈለግ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የግጭት ሰለባ እየሆኑ ተማሪዎች እየተገደሉ ነው፡፡ የፖለቲካው ቁማር ሒሳብ የሚወራረደው በንፁኃን ደም ነው፡፡ አንዳች ችግር ሲያጋጥም ተቀምጦ በሥርዓት መነጋገር አይፈለግም፡፡ ማስፈራሪያው መንገዶችን መዝጋት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን መበጥበጥ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የጦር ቀጣና ማድረግ፣ የንፁኃንን ሕይወት መቅጠፍና የሕዝብና የአገር ንብረት ማውደም ነው፡፡ የሥልጣኔ ጮራ ያልፈነጠቀበት የአገሪቱ ፖለቲካ ለዴሞክራሲ ባህል ባዕድ በመሆኑ፣ ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ተስፋ እየደበዘዘ የቀውስ ሥጋት አገሩን ተቆጣጥሮታል፡፡ አገርን ማረጋጋት አለመቻል መዘዙ የከፋ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውንና ዓላማቸውን እንደያዙ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ስምምነት ግን በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማካተት አለበት፡፡ በተለይ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራቸው በደም አፋሳሽ ግጭቶች ችግር ውስጥ በወደቀበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ ማስፈራሪያዎች በግልጽ ሲለፈፉና የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት እነዚህን አደገኛ ድርጊቶች ለማስቆም በአንድነት ካልተነሱ ፋይዳቸው ምንድነው? ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ሥርዓት በማስያዝ ከግጭት ቀስቃሽነትም ሆነ አስተጋቢነት ካልገቷቸው ምን ይጠቅማሉ? ሌላው ቀርቶ የአገር ህልውናና የሕዝብ ደኅንነት ካላሳሰባቸው ምን ይሠራሉ? ልዩነቶቻቸው ላይ ብቻ አተኩረው የአገር አንድነት አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ዝም የሚሉ ከሆነ ምን ይረባሉ? የአገር ሰላም፣ አንድነትና የሕዝብ ዘለቄታዊ ደኅንነት አሳስቧቸው በኅብረት ካልሠሩ እንደሌሉ ይቁጠሩት፡፡ አገር ካልተረጋጋች እነሱም ዋጋ የላቸውም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት ሲኖርበት፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅነነት የማስጠበቅ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አለው፡፡ በዚህ ሥልጣኑ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ግዴታው ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት ብልኃትና ጥበብ ቢያስፈልገውም፣ ሕግ የማስከበር ተግባሩ ግን ፈጽሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡ የዜጎችን መብቶችና ነፃነት የማክበር ሥራው ሳይዘነጋ፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ በተለይ የአገርን ሰላም የሚያናውፅ፣ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚከት ድርጊት ሲያጋጥም ኃላፊነትን መዘንጋት ያስጠይቃል፡፡ በዚህ ጊዜ በርካቶች መንግሥት ለምን ሕግ አያስከብርም ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥት ሕግ ማስከበር ተስኖት ተከታታይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ንፁኃን ሲገደሉ፣ ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ ሲፈናቀሉና ሲዘረፉ፣ እንዲሁም የአገር ንብረት ሲወድም በስፋት ተስተውሏል፡፡ ጥቃቶቹ አድማሳቸውን እያሰፉ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እያመሩ ነው፡፡ የተማሪዎች ሕይወት ጠፍቶ የመማር ማስተማር ሒደቱ ችግር ውስጥ እየገባ ነው፡፡ የተማሪዎች ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ችግር ያሳሰባቸው የሃይማኖቶች መሪዎች ሳይቀሩ የመንግሥት ትዕግሥት ገደብ ይኑረው እያሉ ነው፡፡ የአገር ሰላም ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የመንግሥት ያለህ ሲባል፣ መንግሥት ደግሞ በሙሉ አቅሙ መኖሩን ማሳየት አለበት፡፡ ከአገር ህልውና የሚቀድም የለም፡፡

የአገርን ሰላም በማደፍረስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ኃይሎች ስለመኖራቸው ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሐሰተኛ መረጃዎችንና ምሥሎችን ከሚያሰራጩ ጀምሮ፣ እጃቸውን በማስረዘም ግጭቶችን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች የሚያበረታቱ አሉ፡፡ እነዚህ የራሳቸው ጥቅም እንዳይጓደል ተግተው የሚሠሩ ኃይሎች፣ የእነሱ ዓላማ እንዲሳካ ማንኛውንም ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር ከፋፍለው ከማጋጨት አልፈው፣ ቤተ እምነቶችን እያቃጠሉ የሃይማኖት ጦርነት ለማስነሳት ሰይጣናዊ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበሩ መልካም እሴቶችን በመሸርሸር ጥርጣሬና አለመተማን እየፈጠሩ ነው፡፡ የብዙኃኑን ዝምታና ችላ ባይነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አጥፊ ቅስቀሳዎችን ያደርጋሉ፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ ይነዛሉ፡፡ ማመዛዘን የማይችሉ ግለሰቦችን እየተጠቀሙ ሁከት ያስነሳሉ፡፡ በስሜት እየኮረኮሩ ለውድመት ያሰማራሉ፡፡ ለዘመናት ተሳስሮ የኖረውን ሕዝብ ለማለያየት አስፀያፊ ስድቦችን ያሰራጫሉ፡፡ ቁጡዎችንና በስሜት የሚነዱትን ለአፀፋ እያዘጋጁ ግጭት ያስነሳሉ፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እነዚህ ኃይሎች ይታወቃሉ፡፡ ምን እንደሚፈልጉም ይታወቃል፡፡ አገርን ማረጋጋት ከተፈለገ እነዚህን በሕግ አደብ ማስገዛት ይቻላል፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ አሁን እንደሚታየው በሁከትና በግጭት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምትነግዱ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አፈንግጣችሁ የማንን ዓላማ ነው የምታሳኩት? ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ያለው ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አይደለም፡፡ ስለትናንቱ አይረቤ ሥርዓት ከመነታረክ ነገ የሚፈጠረውን የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማለም ነው የሚበጀው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡  ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ፀባይ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ዓይንና እጅን በሕገወጥ መንገድ የሚገኝ ሥልጣንና ገንዘብ ላይ አድርጎ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ሥልጣንና ገንዘብ አያማልላቸውም፡፡ የእነሱ ፍላጎት ከአገር ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በታች እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እያነሳሱ አያጋድሉም፡፡ የአገርን ሰላም እያደፈረሱ ቀውስ አይፈጥሩም፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ በመሆናቸው ተግባራቸው ግልጽ ነው፡፡ ጨለማ ውስጥ መሽገው አገር አይበጠብጡም፡፡ ከእንዲህ ዓይነት የማይረባ ድርጊት ነፃ ነን የምትሉ አገር አረጋጉ፡፡ ከአገር መረጋጋት በላይ የሚቀድም ነገር የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...

በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ኢንተርፕራይዞች የመክሰም አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ

ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ 40 ባለሙያዎች ወደ ጀርመን ሊላኩ ነው በመላ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጽንፈኝነት መጨረሻው ተያይዞ መውደቅ ነው!

ዓለም ከዕለት ወደ ዕለት እጅግ በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ዕውቀቶች በከባድ ፍጥነት ወደፊት መግፋቱን እየቀጠለ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ዘመኑን በማይመጥኑና በታሪክ ተጠያቂ በሚያደርጉ...

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...